1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በማ/አፍሪቃ ሬ.የፈረንሳውያን ወታደሮች አሳፋሪ ድርጊት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 25 2007

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተሠማሩ ፈረንሳውያን ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ብዙ ሕፃናትን በወሲብ መድፈራቸው ከአንድ ወር ገደማ በፊት ይፋ ቢወጣም፣ የተመድ ስለዚሁ ወቀሳ ከዚያን ጊዜ አስቀድሞ መረጃ እንደደረሰው እና ተገቢውን ርምጃ እንዳልወሰደዱን የአንድ ግብረ ሠናይ ድርጅት ባልደረባ በማጋለጥ ወቀሳ ሰነዘሩ።

https://p.dw.com/p/1Fajl
Französische Soldaten in der Zentralafrikanischen Republik
ምስል AFP/Getty Images/P. Pabandji

[No title]

ልክ እንደ ተመድ ስለወቀሳው መረጃ የደረሰው የፈረንሳይ መንግሥትም በደሉን ፈፅመዋል በተባሉት ሰላም አስከባሪዎች ላይ እስካሁን ርምጃ አለመውሰዱ ብዙ እያነጋገረ ይገኛል።
በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ስር የተሠማሩ ፈረንሳውያን የሰላም አስከባሪ ወታደሮች በብዙ ሕፃናት ላይ የወሲብ ድፍረት ፈፅመዋል በሚል የተሰነዘረው ወቀሳ ባስቸኳይ እንዲጣራ የተመድ ጠየቀ። ይህ ወቀሳ መስሪያ ቤታቸውን እጅግ እንዳሳሰበው የተመድ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተመልካች ኮሚሽን ኃላፊ ሰይድ ራድ ትናንት በዠኔቭ አስታውቀዋል። የተመድ ባለሥልጣናት መስሪያ ቤታቸው ስለ ወቀሳው መረጃ ከደረሰው በኋላ ወደ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በመሄድ እና ሕፃናቱን በማነጋገር ባካሄዱት ምርመራቸው ስለወሲባዊው ድፍረት ዝርዝር መረጃ መሰብሰብ መቻሉን «ኤድስ ፍሪ ዎርልድ» የተባለው ግብረ ሠናይ ድርጅት ባልደረባ ፓውላ ዶኖቫን አስታውቀዋል። በዚሁ መረጃ መሠረት፣ እንደ ዶኖቫን ገለጻ፣ ሕዝቡን ከተቀናቃኞቹ ሴሌካ እና ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች ጥቃት እንዲከላከሉ እአአ በ2013 ዓም በሀገሪቱ ከተሠማሩት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መካከል ወደ 16 የሚጠጉ ፈረንሳውያን ወታደሮች በስምንት እና በ13 ዓመት መካከል የሚገኙ ብዙ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሕፃናትን በገንዘብ ወይም በምግብ እየሸነገሉ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ አስገድደዋል።
« ከተመለከትናቸው አንዳንድ ዘገባዎች ለመረዳት እንደቻልነው አንዱ ወታደር ሕፃኑን ሲደፍር ሌላው ቆሞ ይጠብቃል። »
ከተመድ የምርመራ ውጤት በኋላ በደሉን ፈፀሙ በተባሉት ፈረንሳውያን ወታደሮች ላይ አንዳችም ርምጃ ሳይወሰድ በመቅረቱ፣ የምርመራው ውጤት የደረሳቸው ያለሙ መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተመልካች ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሥልጣን ፣ ስዊድናዊው አንደርስ ኮምፓስ ፈረንሳውያኑ ሰላም አስከባሪዎች በሕፃናቱ ላይ የሚፈፅሙትን በደል ለማስቆም በማሰብ ወዲያውኑ ስለ ጉዳዩ ለፈረንሳይ መንግሥት በጽሑፍ መረጃ አቅርበዋል። ይህን ተከትሎም የፈረንሳይ የፍትሕ አካል የቀረበውን ወቀሳ ማጣራት ቢጀምርም፣ እስካሁን ወቀሳው የሚመለከታቸውን ወታደሮች በኃላፊነት አልጠየቀም። በአንፃሩ፣ መረጃውን ያቀረቡት ኮምፓስ በመረጃ አቀራረብ ጊዜ ስህተት ፈፀመዋል በሚል ሰበብ የተመድ ፍርድ ቤት ከስራቸው ለጊዜው ማገዱን የተመድ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተመልካች ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሩፐርት ኮልቪል ገልጸዋል።

« የወሲብ ድፍረት ሰለባዎቹን እና የምስክሮችን ስም፣ ካለነርሱ ስምምነት ይፋ አለማድረግ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ነው። ሕፃናት ደግሞ ስምምነታቸውን ለምን እንደሚሰጡም በግልጽ ሊያውቁት አይችሉም። »
ይሁናና፣ ዶኖቫን የተመድ ኮምፓስን ያገደበት ውሳኔ የራሱን ስህተት ለመሸፋፈን ነው በሚል ወቅሰዋል።
« የተመድ ወቀሳውን የማጣራት ግዴታ ቢኖርበትም ለብዙ ወራት አንዳችም ርምጃ አልወሰደም። ይህ ስህተቱ ግልጽ በሆነበት ጊዜ ፣ ጥፋቱን በሕፃናቱ ላይ ተፈፀሙ ስለተባሉት በደሎች የፈረንሳይን መንግሥት ባስጠነቀቁት ኮምፓስ ላይ አላከዋል። »
የብሪታንያውያኑ ዕለታዊ ጋዜጣ « ዘ ጋርዲያን» ከ«ኤድስ ፍሪ ዎርልድ» የተባለው ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋ በመተባበር እአአ ሚያዝያ 29፣ 2015 ዓም ስለ ወቀሳው በይፋ ዘገባ ካወጣ በኋላ ብቻ ነበር የተመድ ፍርድ ቤት ኮምፓስን ያገደበትን ውሳኔ የሰረዘው።
ፈረንሳይም ከዚህ በኋላ ነበር ስለወቀሳው ከአንደርስ ኮምፓስ መረጃ እአአ በ2014ዓም የአውሮጳውያኑ የበጋ ወራት እንደደረሳት ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተናገረችው። የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ኦሎንድም የቀረበው ወቀሳ ከተረጋገጠ በተወቃሾቹ ላይ አስፈላጊው ርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። ወቀሳ የበዛበት የተመ የተለያዩ ድርጅቶችም ጉዳዩን እየተከታተሉ ነው።

Französische Soldaten in der Zentralafrikanischen Republik
ምስል AFP/Getty Images/M.Medina
Paula Donovan, AIDS-Free World Co-Director
ፓውላ ዶኖቫንምስል Alexis MacDonald