1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቅሌት፣ ክስና ኪሳራ-ፎልክስ ቫገን

ረቡዕ፣ መጋቢት 7 2008

ፎልክስ ቫገን የገባበት የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ማጭበርበር በኋላ የአክሲዮን ዋጋውም ይሁን በደንበኞቹ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እጅጉን አሽቆልቁሏል። የቀድሞውን የኩባንያዉን ሥራ አስፈጻሚ አሰናብቶ በአዲስ ቢተካም ኩባንያው ማንሠራራት ተስኖታል። በዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል እና የግዛት መንግሥታትም በርካታ የክስ ዶሴዎች ተከፍተውበታል።

https://p.dw.com/p/1IECw
VW Skandal Symbolbild Logo Eis
ምስል picture-alliance/dpa/F. May

'ቅሌት፣ ክስና ኪሳራ-ፎልክስ ቫገን

ፎልክስ ቫገን እንዲህ እንደ ዛሬ በበርካታ ክሶች ከመጥለቅለቁ በፊት የከበረ ስሙን ይዞ በዩናይትድ ስቴትስ የተሽከርካሪ ገበያ ለመግባት ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ይሁንና በዩናይትድ ስቴትስ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የፎልክስ ቫገን ለተሽከርካሪዎች የተቀመጠውን የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ማጭበርበሩን ይፋ ካደረገ በኋላ ተቀባይነቱም ሆነ የገበያ ድርሻው አሽቆልቁሏል። የአገሪቱ የፍትሕ ሚኒስቴር በፎልክስ ቫገን ላይ ክስ ከመሠረተ በኋላ የገበያ ድርሻው በ9.1 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የጀርመኑ መኪና አምራች ፎልክስ ቫገን በገባበት የበካይ ጋዝ ልቀት ቅሌት በዩናይትድ ስቴትስ ገበያ ለሸጣቸው መኪኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ የክስ መጥሪያዎች ደርሰውታል። የኒው ጀርሲ፤ ኒው ሜክሲኮ፤ ቴክሳስ እና ዌስት ቨርጂኒያ ግዛቶች አቃብያነ-ሕግ በኩባንያው ላይ ክስ መሥርተዋል። ግን ጉዳዩ በዚህ የሚያበቃ አይመስልም። ስመ-ጥሩውን የጀርመን የመኪና አምራች ለመታደግ ውጥረት ውስጥ የገባው አዲስ አመራር ከዩናይትድ ስቴትስ ሌሎች ግዛቶች ተጨማሪ የክስ መጥሪያዎች ይደርሱታል ተብሎ ይጠበቃል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፍትሕ ሚኒስቴር በፎልክስ ቫገን ኩባንያ ላይ አዲስ ክስ የከፈተ ሲሆን ጉዳዩን ከፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ደብዳቤ ጽፏል። ኩባንያው የተከፈተበት ክስ በባንክ ማጭበርበር የሚዳኝበት መሆኑን ዎል ስትሪት ጆርናል እና ሬውተርስ ዘግበዋል።
ፎልክስ ቫገን በዩናይትድ ስቴትስ ለተሽከርካሪዎች የተቀመጠውን የተሽከርካሪዎች የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን በመተላለፍ እና ፍተሻውን በማጭበርበር በቀረቡበት ክሶች የሚጠብቀው ቅጣት 48 ቢሊዮን ዶላር (42 ቢሊዮን ዩሮ) ደርሷል። የፎልክስ ቫገን የዩናይትድ ስቴትስ ቢሮ ዋና አስፈጻሚ ሚሼል ሆርን የኩባንያቸው የበካይ ጋዝ ልቀት ቀውስ ውስጥ በገባ በስድስተኛ ወሩ ባለፈው ሳምንት ከኃላፊነታቸው ለቀዋል። ሚሼል ሆርን ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ፎልክስ ቫገን እና እሳቸዉ በጋራ በደረሱበት ስምምነት መሠረት መሆኑን ኩባንያው ቢያስታውቅም እስካሁን ትክክለኛው ምክንያት ግን አልታወቀም። ከጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ ቢሮ ኃላፊነትን የተረከቡት ሆርን ሥራቸውን የለቀቁት ፎልክስ ቫገን ኩባንያ ከካሊፎርኒያ ግዛት፤ የአገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር እና የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ጋር ድርድር ከመጀመሩ ነው። እርሳቸውም ኃፊነታቸውን ከመልቀቃቸው ቀደም ብለው ኩባንያቸው በዩናይትድ ስቴትስ ገበያ ስህተት መፈጸሙን አምነው ነበር።
«ስለዚህ ጉዳይ ግልጽ እንሁን። ኩባንያችን ለአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ እና ለካሊፎርኒያ ግዛት ተዓማኒ አልነበረም። በሁላችሁም ፊት አንድ ነገር ልናገር። በጀርመን አባባላችን ሁሉንም ነገር አበለሻሽተንዋል።»
ፎልክስ ቫገን በዩናይትድ ስቴትስ ለ580,000 የናፍጣ መኪኖች የበካይ ጋዝ ልቀት ቁጥጥርን ማጭበርበር የሚችል ሶፍትዌር መግጠሙን ካመነ በኋላ የተከሰሰባቸው የሕግ አንቀጾች እጅጉን ጠንካራ የሚባሉት ናቸው። የከሳሾቹም ማንነት ተበራክቷል። በዩናይትድ ስቴትስ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ኮፌ የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ጠባይ በእንዲህ አይነት የቀውስ ወቅቶች በደል ደርሶብኛል የሚል ማንኛውም ሰው ክስ ለመመስረት እንደሚፈቅድ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ አውጪዎች ፊት ቀርበው ኩባንያቸው ስለ ገባበት ቅሌት ምላሽ የሰጡት ፊሊፕ ሆርን የፎልክስ ቫገን ኩባንያ አመራር የበካይ ጋዝ ልቀትን ለማጭበርበር የታቀዱት ሶፍትዌሮች በመኪኖቹ ላይ እንዲገጠም አንዳች ውሳኔ አላስተላለፈም ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
«ይህ የሥራ አሰፈጻሚው ውሳኔ አይደለም። በእኔ አተያይ እና እስከ ዛሬ ድረስ ባለኝ መረጃ የሥራ አስፈጻሚው፤ ቦርዱም ይሁን የሥራ ተቆጣጣሪው ውይይት አድርጎ ፍቃድ አልሰጠም። ይህ የተወሰኑ የሶፍትዌር ኢንጂኔሮች በራሳቸው እና እኛ በማናውቀው ምክንያት ያደረጉት ነው። ምክንያቱን እኔም ማወቅ እፈልጋለሁ።»

USA Volkswagen Michael Horn
ምስል Reuters/D. Ornitz

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ይኸው ኩባንያ በአክሲዮን ባለ ድርሻዎች የ3.7 ቢሊዮን ዶላር (3.3 ቢሊዮን ዩሮ) ክስ ገጥሞታል። የኩባንያው የአክሲዮን ባለ ድርሻዎች ኩባንያውን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት የናፍጣ መኪኖቹን የአየር ብክለት ቅሌት በመደበቁ መሆኑን ብሎምበርግ ዘግቧል። በኒደር-ዛክሰን የፌዴራል ግዛት በምትገኘው የብሩንስዊክ ከተማ የተከፈተው የክስ መዝገብ ለፎልክስ ቫገን ተጨማሪ የራስ ምታት መሆኑን የዶይቸ ቬለ የኢኮኖሚ ዘጋቢ የሆነው ሐቪየር አጌዳ ይናገራል።
«በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከሳሾቹ በፋይናንሱ ዘርፍ ባላቸው ጠንካራ አቅም ምክንያት ፎልክስ ቫገን የገጠመው የአሁኑ ክስ አስቸጋሪ ያደርግበታል። ከእነዚህ መካከል በጀርመን መዋዕለ ንዋይ ግዙፍ የሆነው ዴካ ይገኝበታል። አሁን የምናወራው ከፍተኛ ገንዘብ፤ ኃይል እና እጅግ የሰሉ ጠበቆች ስላሏቸው እና ክሳቸውን ማሸነፍ ስለሚችሉ ድርጅቶች ነው። ስለዚህ ይህ የፎልክስ ቫገንን መጻዒ እጣ ፈንታ እጅጉን አስቸጋሪ ያደርገዋል። የእነዚህ ኩባንያዎች ክስ ሌሎችም ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉም ያደርጋቸዋል። ይህ ክስ የፎልክስ ቫገን ኩባንያ ላይ በፋይናንስ በኩል ተጨማሪ ተጽዕኖ ያሳድራል።»
ፊሊፕ ሆርንም ይሁኑ የፎልክስ ቫገን ኩባንያ አዲስ ሥራ አመራር ኩባንያው በመኪኖቹ ላይ ስለገጠማቸው የበካይ ጋዝ ልቀት ማጭበርበሪያ ሶፍትዌር የምናውቀው ነገር የለም ይበሉ እንጂ አዲስ የሚወጡ ዘገባዎች የሚጠቁሙት ሌላ ነው። እንደ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ ከሆነ ኩባንያው የገባበትን ቅሌት ለመሸፋፈን እና ከቅሌቱ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን ለማጥፋት ሞክሯል። ፎልክስ ቫገን ለሶስት ቀናት ከቅሌቱ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን ከተቋሙ የሰነድ ማጠራቀሚያ ሰንዱቅ ለመሰረዝ ሞክሯል የሚል ወንጀል ይዞ ብቅ ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ቢሮ ተቀጣሪ የነበረ ሠራተኛ በግሉ ክስ መሥርቷል። ውንጀላዎቹ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው??? የሚስማማው ሐቪየር አጌዳ እስካሁን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ግን ይናገራል።
«ማረጋገጥ ባንችልም ፎልክስ ቫገን በኩባንያው ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ እያወቀ እንደሸፋፈነ ሰምተናል። ኩባንያው መረጃውን የሸፋፈነው ከመንግስት ተቆጣጣሪዎች ብቻ ሳይሆን ኢንቨስተሮቹ ጭምር ነው ተብሏል። ኩባንያዎቹ በአክሲዮን ገበያ ያላቸውን ዋጋ የሚቀንስ አንዳች ነገር ሲፈጠር ለአክሲዮን ባለድርሻዎች የማሳወቅ የሕግ ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ ይህ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። የፎልክስ ቫገን የአክሲዮን ዋጋ ሲቀንስ በቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ የከሰሩ ባለድርሻዎች ገንዘባቸውን ለማስመለስ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳሉ። የምናወራው በአክሲዮን ገበያው በሚሊዮን የሚቆጠር ዩሮ ኪሳራ ስለገጠማቸው ባለ አክሲዮኖች ነው።»
የፎልክስ ቫገን ኩባንያ ከዩናይትድ ስቴትስ መንግስት፤ ከግዛቶች እና የአክሲዮን ባለድርሻዎች ብቻ ሳይሆን ከባንኮች ጭምር ክስ ሊመሠረትበት ይችላል። የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ከፎልክስ ቫገን መዋዕለ ንዋይ እና የመኪና ሽያጭ ጋር በተገናኘ ብድር ያቀረቡ የገንዘብ ተቋማት የደረሰባቸውን ጉዳት በመመርመር ላይ ይገኛል። የዩናይትድ ስቴትስ ሸማቾች ከበካይ ጋዝ ልቀት ነጻ የሆነ መኪና ለመግዛት በገበያው ከፍተኛውን ክፍያ ቢፈጽሙም በምላሹ የተረከቧቸው ተሽከርካሪዎች ከተቀመጠው ገደብ እስከ 40 በመቶ ከፍ ያለ በካይ ጋዝ የሚለቁ ናቸው። በዱክ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ሳሙዔል ቡዔል የዩናይትድ ስቴትስ ፍትህ ሚኒስቴር የደንበኞች መብት ጥበቃ ድንጋጌን እስከ መጠቀም ሊደርስ እንደሚችል ያምናሉ። የሕግ ፕሮፌሰሩ ፎልክስ ቫገን በዚህ ድንጋጌ ጥፋተኛ ከተባለ መቀጮው እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
የፎልክስ ቫገን የአንድ አክሲዮን ዋጋ ማሽቆልቆሉን ዛሬም አላቆመም። የኩባንያውን የአክሲዮን ዋጋ ለማረጋጋት የየዕለት ሥራውን ማሻሻል እንደሚጠበቅበት የሚናገረው ጋዜጠኛ ሐቪየር አጌዳ ይህን ለማድረግ ብዙ ሥራ እንደሚፈልግ ይናገራል።
«ይህን ማቆም የሚችለው ፎልክስ ቫገን በየዕለቱ የሚሠራውን ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ሲችል ብቻ ነው። ይህ ግን የኩባንያው ተቀባይነት በቅሌቱ ክፉኛ በመጎዳቱ አስቸጋሪ ይሆናል። ኩባንያው በአክሲዮን ገበያ ያለውን ዋጋ ስንመለከት ከደረሰበት ኪሳራ ለማገገም ብዙ መሥራት እንዳለበት እንረዳለን። ፎልክስ ቫገን በአክሲዮን ገበያው ከፍተኛ ዋጋ ካገኘ አንድ አመት አስቆጥሯል። አሁን ያለውን የአክሲዮን ዋጋ ስንመለከት በ53% ቅናሽ አሳይቷል። ስለዚህ ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ዋጋ ላይ ለመድረስ ብዙ መንገድ መሄድ ያስፈልገዋል።»
ፎልክስ ቫገን ኩባንያ ከገባበት ቀውስ ለመውጣት ባለፈው ታህሳስ ወር ከ13 ዓለም አቀፍ ተቋማት የ29 ቢሊዮን ዩሮ (30 ቢሊዮን ዶላር) ብድር ሳያገኝ እንዳልቀረ ተሰምቶ ነበር። የአበዳሪ ተቋማቱ ማንነትም ይሁን የብድር ስምምነቱ አይነት እስካሁን በምስጢር ቢያዝም ኩባንያውን ከገባበት ቀውስ ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ሁነኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሏል። የጀርመን መንግስት እና የአክሲዮን ባለ ድርሻዎቹ ኩባንያው ለገባበት ቀውስ መፍትሔ እንዲያበጅ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ማቲያስ ሙለር ላይ ጫና እያሳደሩ ነው። ይሁንና ፎልክስ ቫገን በአበዳሪ ተቋማት ዘንድ ያለው ተዓማኒነት ዝቅ ብሏል። የኩባንያውን አመራር ብቃት አጥብቀ የተቹም ይገኙበታል። የአንድሪያስ ሙለር አመራር ኩባንያውን መታደግ ይችል ይሆን? አንድሪያስ ብሪመር የተሽከርካሪዎች የገበያ ጥናት ተቋም የሆነው ኢፋ ዋና ኃላፊ ናቸው።
«ይህ በአንድሪያስ ሙለር ላይ ብቻ ያተኮረ ነው ብዬ አላስብም። ጉዳዩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መኪኖች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የሞተር ንድፎች የሚመለከት ቀውስ ነው። ስለዚህ መፍትሔ ለማበጀት ጊዜ ይወስዳል። የብድር ተቋማቱ ጉዳይ አንድሪያስ ሙለር ከመምጣታቸው በፊት የተከሰተ ነው። እነ ዊንተርኮርን በስልጣን በነበሩበት ጊዜ ማለቴ ነው። ሙለር ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። ይሁንና ከዚህ በበለጠ ፍጥነት መከናወን ይኖርበታል። ሁሉም ነገር በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል። የብድር ተቋማቱም ይሁኑ እኛም ይህንን ነው በመጠባበቅ ላይ የምንገኘው።»
ፎልክስ ቫገን ለገባበት ቅሌት ተጠያቂዎቹ ጥቂት ሰዎች መሆናቸውን ያምናል። ማቲያስ ሙለር ወደ የዋና ሥራ አሰፈጻሚነት ኃላፊነቱን ሲረከቡ ለተፈጠረው ቀውስ መልስ ፍለጋ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰሠ

Symbolbild Daimler-Boss lässt in Flüchtlingszentren nach Arbeitskräften suchen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Weißbrod
Parkplatz VW Wagen Autos
ምስል picture-alliance/dpa
Deutschland EU Auto-Neuzulassungen steigen weiter
ምስል picture-alliance/dpa