1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቅሌትና ስጋት-ፎልክስ ቫገን

Eshete Bekeleሰኞ፣ መስከረም 17 2008

የፎልክስ ቫገን ኩባንያና የሚያመርታቸው መኪኖች ለጀርመን የጥንካሬ ምልክት ብቻ ሳይሆን ከባህልና ማንነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን ኩባንያው በቅሌት እየታመሰ ነው። በዓመት ከ15-16 ሚሊዮን ዩሮ ይከፈላቸው የነበሩት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርቲን ቪንተርኮርን ተሰናብተዋል።

https://p.dw.com/p/1GetC
Deutschland VW Logo Symbolbild zum Abgasen-Skandal
ምስል Reuters/F. Bimmer

ቅሌትና ስጋት-ፎልክስ ቫገን

ከሁለት ሳምንት በፊት በ160 ዶላር ይሸጥ የነበረው የፎልክስ ቫገን አክሲዮን ዋጋ ወደ 110 ዶላር አሽቆልቁሏል። ይህ አጠቃላይ የኩባንያው ዋጋ በ 30 በመቶ እንዲቀንስ አስገድዶታል። ዋና ሥራ አስኪያጁ ማርቲን ቪንተንርኮን ተሰናብተዋል። የስመ ጥሩዎቹ ፎልክስ ቫገን መኪኖች ደንበኞች ግራ ተጋብተዋል። የኩባንያው ምርቶች በአሜሪካ፤ አውሮጳና እስያ ምርመራ ይጠብቃቸዋል። ይህ ሁሉ በአንድ ሳምንት ውስጥ በፎልክስ ቫገን ላይ የወረደ ዱብ እዳነው። ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መግለጫ የመጣ ይሁን እንጂ ፎልክስ ቫገን ጠንቅቆ የሚያውቀው ባስ ሲል ደግሞ የቅሌቱን መነሾ ቀድሞ የተዘጋጀበት መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።በዶይቼ ቨሌ የኤኮኖሚ ጉዳዮች ዘጋቢ አንድሪያስ ቤከር «የአሜሪካ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ፎልክስ ቫገን የብክለት ምርመራን ሳይጭበረብር አይቀርም ብለው ካሳወቁ በኋላ »ቀውሱ መጀመሩን ይናገራሉ።

«በካሊፎርኒያ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት በተወሰኑ የናፍጣ መኪኖች ላይ ባካሄደው ፍተሻ ያገኘው ውጤት በቤተ-ሙከራ ከተገኘው ይፋዊ ውጤት እጅግ የበለጠ ሆነ። ሁሉም መኪኖች የብክለት ፍተሻ ይደረግላቸዋል። ፍተሻው የሚካሄደው በመንገድ ላይ ሳይሆን በቤተ-ሙከራ ነው። ይህ ፍተሻ በሚካሄድበት ወቅት በሞተር መቆጣጠሪያው ክፍል የሚገኝ ሶፍትዌር ሞተሩ አነስተኛ ጋዝ እንዲለቅ ባህሪውን ይቀይረዋል።»

Symbolbild Auspuff Abgas VW Volkswagen Skandal Diesel AU Abgassonderuntersuchung
ምስል picture-alliance/dpa/Jan Woitas

ይህ በናፍጣ መኪኖች ላይ የተቀሰቀሰው ቅሌት በፎልክስ ቫገን ታሪክ ከፍተኛው ሆነ። ኩባንያውም የዩናይትድ ስቴትስ የብክለት ፍተሻን ማጭበርበሩን ለተቆጣጣሪዎች የተሳሳተ መረጃ መስጠቱን አምኗል። ኩባንያው በዚህ ቅሌት እስከ 18 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሏል። በፎልክስ ቫገን መኪኖች ዘላቂ ተቀባይነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል በተባለው በዚህ ቅሌት ብቻ ኩባንያው ቀደም ብሎ የሸጣቸውን ግማሽ ሚሊዮን መኪኖች ችግር አለባቸው። ይመለሱ ሲል ጥሪ አስተላልፏል። የብክለት ፍተሻን የሚያጭበረብረው ሶፍትዌር የተገጠመው ግን 11 ሚሊዮን ለሚደርሱ መኪኖች ነው።

ረቡዕ መስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም.

«ክቡራትና ክቡራን በናፍጣ መኪኖቻችን ላይ የታየው የጥራት ደረጃ ፎልክስ ቫገን ከቆመለት ዓላማ ተቃራኒ ናቸው። አሁን ለሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ የለኝም። ነገር ግን ምን እንደተፈጠረ መነሻዉን ለማጣራት እየሠራን እንገኛለን።»

ኩባንያውን ለስምንት ዓመታት በሥራ አስኪያጅነት የመሩት የስልሳ ስምንት ዓመቱ ጎልማሳ ማርቲን ቪንተርኮን ቃል ነበር። በስምንት ዓመታት የፎልክስ ቫገን የሥራ አስኪያጅነት ዘመናቸው ኩባንያውን በዓለም የተሽከርካሪ ሽያጭ ከቀዳሚዎቹ ተርታ አስመድበውታል። በኩባንያው አመራሮች መካከል ተፈጥሮ በነበረ ቀውስ ከስልጣናቸው እንዲለቁ የቀረበባቸውን ግፊት በአሸናፊነት የተወጡት ዶ/ር ማርቲን ቪንተርኮርን አዲስ የሥራ ውል ለመፈረም በዝግጅት ላይ ነበሩ። ግን እቅዳቸው ሳይሰምር ቀርቶ በዕለተ ረቡዕ አንገታቸውን ሰበሩ። ይቅርታም ጠየቁ።

Deutschland - Volkswagen Martin Winterkorn
ምስል Getty Images/S. Gallup

«ክቡራትና ክቡራን በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመኪኖቻችንና ቴክኖሎጂያችን ላይ እምነት አላቸው። ይህን እምነት በመስበራችን ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ደንበኞቻችንን፤ የመንግሥት መሥሪያቤቶችን እና አጠቃላይ ህዝቡን ለተፈጠረው ስህተት በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ።»

ከተመሠረተ 78 ዓመታትን ያስቆጠረው የፎልክስ ቫገን ኩባንያ በአሁኑ ወቅት 600,000 ሠራተኞች ሲኖሩት ዓመታዊ ገቢው 200 ቢሊዮን ዩሮ (224 ቢሊዮን ዶላር) ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ በአስራ ሁለት አይነት ምርቶቹ 10.2 ሚሊዮን መኪና በመላው ዓለም ሸጧል።

አሁን ከኩባንያው የሥራ አመራር ቦርድ ጋር በደረሱበት መግባባት ከኃላፊነታቸው የተነሱት የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ማርቲን ቪንተርኮርን የጃፓኑን ቶዮታ ዓመታዊ የምርት መጠን በመብለጥም የረጅም ጊዜ እቅዳቸውን አሳክተው ነበር። ኩባንያው እስከ ያለፈው ሰኔ ወር ድረስ 5.04 ሚሊዮን መኪኖችን በመላው ዓለም ሸጧል። ይህም ከጃፓኑ ቶዮታ ኩባንያ በ20,000 ይልቃል።

ፎልክስ ቫገን ስኬታማ የጀርመን ኩባንያ ብቻ አይደለም። የጀርመናውያን የኩራት ጭምር እንጂ- አንድሪያስ ቤከር

«ግዙፍ ኩባንያ ነው። በመላው አውሮጳ ትልቁ የመኪና አምራች ኩባንያ ነው። በሽያጭም በያዝነዉ ዓመት የመጀመሪያ ወራት ከዓለም ቀዳሚ ነው። ለጀርመናውያን ደግሞ የክብር ምልክት ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጀርመናውያን ስኬት የተገለጠበት ኩባንያ ነው። ስራ የጀመሩት በጦርነቱ ወቅት ቢሆንም ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ወደ ውጪ መላክ ተጀመረ። ማንኛውም ሰው እንደአቅሙ ሊገዛው የሚችል ነበር። ብዙ ጀርመናውያን በፎልክስ ቫገን አድገዋል። በርካታ ሠራተኞችም አሉት። ዋና ጽ/ቤቱ በሚገኝበት የቮልፍስቡርግ ከተማ ነዉ ኩባንያው የተመሠረተው። በዚህ ምክንያትም ቮልፍስቡርግ፦ፎልክስ ቫገን ነው ፎልክስ ቫገንም ቮልፍስቡርግ ነዉ የሚል አባባል አለ። በዚያ ብቻ 70,000 ሠራተኞች ይሠራሉ። ስለዚህ የስሜት ብቻ ሳይሆን የገንዘብም ጭምር ቁርኝት አለ። ፎክስ ቫገን በመላዉ ዓለም 600,000 ሠራተኞች አሉት። ከኩባንያው ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው በርካታ ሰዎች አሉ። እናም ብዙ ሰዎች ይህ ቀውስ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋት አላቸው።»

የአውሮጳና የእስያ ፓስፊክ ለፎልክስ ቫገን ቁልፍ ገበያዎች ናቸው። የፎልክስ ቫገን ምርቶች 40.6 በመቶው በእስያና ፓስፊክ ቀጣና፤ 43 በመቶው ደግሞ በአውሮጳ ይሸጣሉ። ሰሜን አሜሪካ 8.7 በመቶ ደቡብ አሜሪካ ደግሞ 7.8 በመቶ ድርሻ አላቸው። ኩባንያው ከቻይና የመኪና ሽያጭ የ40 በመቶ ድርሻም አለው።

VW Golf VII Produktion in Wolfsburg
ምስል Reuters

በአውሮጳ ትልቁ የመኪና አከፋፋይና አምራች ፖርሼ ሆልዲንግ በ50.7 በመቶ ቀዳሚው ነው። በጀርመን ሰሜን ምዕራብ የምትገኘው የሎወር ዛክሰን ግዛት 20 በመቶ፤ የኳታር ኢንቨስትመንት ባለስልጣን 17 በመቶ ድርሻ አላቸው። የፖርሼ ሆልዲን መስራች ቤተሰብ ኩባንያ የሆነው ፖርሼ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለ 2.2 በመቶ ባለድርሻ ነው። አሁን የተፈጠረው ቀውስ በኩባንያው እና በምርቶቹ ላይ ብቻ አልተወሰነም። ከባለ ድርሻዎቹ መካከል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ የተዘጋጁ መኖራቸው ተሰምቷል። በአሜሪካ የቀረበበትን ቀውስ የተቹት የሎወር ዛክሶን አገረ ገዢና በፎልክስ ቫገን ኩባንያ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል የሆኑት ሽቴፋን ቬይል ጉዳዩ የገንዘብ ብቻ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

«ሁሉም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የጉዳዩን ስፋት ይረዳሉ። አሳሳቢው ጉዳይ በኩባንያው ላይ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ብቻ አይደለም። ቀዳሚው ነገር ተዓማኒነት ማጣት ነው።»

ፎልክስ ቫገን እያወቀ ገብቶበታል በሚባለዉ ቅሌት በመላው በዩናይትድ ስቴትስ ምርመራና ክሶች ይጠብቁታል። ደንበኞቹም ቢሆኑ ዝም ብለው እንደማይቀመጡ ይገመታል። ምርመራው ግን በዚህ የሚያበቃ አይመስልም። ከፎልክስ ቫገን ተሻግሮ ሌሎች የመኪና አምራቾችንም ጥርጣሬ ውስጥ እየከተተ ነው። የቢኤም ደብሊው መኪኖች በአውሮጳ ህብረት ከተፈቀደው በላይ አስራ አንድ እጥፍ በካይ ጋዝ ወደከባቢ አየር እንደሚለቁ ቢልድ የተሰኘዉ የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። የጀርመን የመጓጓዣ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንድት በመኪና አምራቾች ላይ ጥብቅ ፍተሻ አስጀምረዋል።

«የሞተር ተሽከርካሪዎች ፌዴራላዊ ቢሮ ምርመራ የሚያተኩረው በፎልክስ ቫገን መኪኖች ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አምራቾች መኪኖች ላይም ድንገተኛ ፍተሻ ያካሂዳል።»

Volkswagen Parkplatz voller Nutzfahrzeuge
ምስል picture-alliance/dpa/J.Stratenschulte

ቢልድ የተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ 2.8 ሚሊዮን የፎልክስ ቫገን መኪኖች የተፈቀደውን የበካይ ጋዝ ልቀት ደረጃ አያከብሩም የሚል ዘገባ አስነብቧል። ከጀረመን ሥራ አስኪያጆች አንደኛ የሚል ማዕረግ የተሰጣቸውና በዓመት ከ15-16 ሚሊዮን ዩሮ ይከፈላቸው የነበሩት ማርቲን ቪንተርኮርን የሚያስተዳድሩት ኩባንያ ስለገባበት ቅሌት የማውቀው ነገር የለም ብለዋል። ይህ ለአንድሪያስ ቤከርም ቢሆን ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።

«በመጀመሪያ ይህ አሁንም ግልጽ አይደለም። ምክንያቱም ከኋላፊነታቸው ለመልቀቅ የተገደዱት አለቃ አላደረኩትም የማውቀውም ነገር የለም ብለዋል። ኃላፊነቱ የማን ነው? ማንስ እንዲህ ያደረገው? አሁንም ግልጽ አይደለም። በዚህ መሃልም ችግሩ አለባቸው የተባሉት መኪኖች ቁጥር እየጨመረ ነው። በመጀመሪያ በዩናይትድ ስቴትስ ግማሽ ሚሊዮን መኪና ነበር የተባለው። ትንሽ ቆይቶ ፍተሻዉን የሚያጭበረብር ሶፍትዌር ያላቸው መኪኖች 11 ሚሊዮን ናቸው ተባለ። የጀርመን የመጓጓዣ ሚኒስትር በአውሮጳ ያሉ ሌሎች መኪኖችም ፍተሻ የሚያጭበረብረዉ ሶፍትዌር እንዳላቸው ማስረጃ መኖሩን ተናግረዋል። ስለዚህ በየዕለቱ ቁጥሩ በጣም እያደገ ነው።»

የጀርመን መንግስትም ይሁን የአውሮጳ ህብረት ፎልክስ ቫገን የብክለት ፍተሻዎችን ማጭበርበሩን ቀደም ብለው እያወቁ እርምጃ ሳይወስዱ ቀርተዋል የሚል ዘገባ ዲ ቬልት የተሰኘው ጋዜጣ አስነብቧል። የጀርመኗ መራሒተ-መንግስት አንጌላ መርክል ኩባንያው ለገባበት ቀውስ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያበጅ አሳስበዋል። ለመሆኑ ፎልክስ ቫገን የገባበት ቅሌት የት ያደርሰው ይሆን? አሁንም አንድሪያስ ቤከር፦

«እስከ 18 ቢሊዮን የሚደርሰው ከባድ ቅጣት አለ። ሊቀንስም ይችላል። ነገር ግን በአክሲዮን ገበያ እስከ 30 ቢሊዮን ዩሮ የሚደርስ ኪሳራ ገጥሟቸዋል። ይህም እንደ ሁኔታው በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ሊያገግም ይችል ይሆናል። ከዚያ ክሶች ይኖራሉ። ምን ያህል ወጪ እንደሚያስወጣ መገመት ያዳግታል። ቀጥሎ በገበያው ሽያጭ ይቀንሳል። በተጨባጭ ያለዉ አሁን ኩባንያው በዚህ ዓመት ከትርፉ እስከ 7 ቢሊዮን ድረስ ሊያጣ ይችላል የሚለዉ ግምት ነዉ። መዘዙ በዚህ ይቆማል አይቆምም የሚለዉን እንግዲህ በቀጣይ እናያለን።»

‘በጀርመን የተሠራ’ወይም 'Made in Germany'የጀርመናውያን የጥራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መፈክር ነው። ጀርመናውያን ግን ሃሳብ ገብቷቸዋል። የፎልክስ ቫገን ቅሌት ጀርመን በዓለም አቀፍ የንግድ መድረኮች ባላት ተቀባይነት ላይ ጥላ እንዳያጠላ።

ፎልክስ ቫገን እንዲህ አይነት ቀውስ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ስሙ የህዝብ መኪና የተሠራዉም አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነበር።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ