1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቁምስቅል በኤርትራ

ዓርብ፣ ግንቦት 13 1996

ዓለም-አቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት ኣምነስቲ ኢንተርናሽነል አሁን ባቀረበው አዲስ ዘገባ መሠረት፣ ኤርትራ ውስጥ ከሁለት ዓመታት ተኩል በፊት በተቀሰቀሰው ሰላማዊ ተቃውሞና የዴሞክራታዊ ለውጥ ጥሪ አንፃር የመንግሥት ክትትል ርምጃ ከተወሰደ ወዲህ፣ ቁምስቅል፣ የግፍ እሥራት፣ እንደወጡ መቅረትና የፖለቲካ እሥረኞች መጉላላት በዚያችው ሀገር ውስጥ ሥር የሰደደ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/E0kz

የኣምነስቲ ኢንተርናሽነል ዘገባ እንደሚለው ከሆነ፣ የኤርትራው መንግሥት ሀገሪቱ ውስጥ ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ገለልተኛ ፍተሻ እንዲደረግ እንኳ አይፈቅድም። “የመጠየቅ መብት የላችሁም” ይላል የዘገባው ርእስ---የሕዝቡን መብት ነፈጋ በመጠቆም።

“የፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የነጠላ ፓርቲ መንግሥት ስለ ሰብዓዊው መብት መላውን ውይይት አቁሟል፣ ሰብዓዊው መብት ስለሚጣስበትም ሁኔታ ፍተሻ እንዲደረገ የሚቀርብለትን ጥያቄ ሁሉ ውድቅ ነው የሚያደርገው፣ እንዲያውም፥ይኸው የኤርትራው መንግሥት እምቢታ ግልጽነት እንዲኖረውና ስለ ሰብዓዊው መብት አያያዙ መጠየቅ እንዳለበት የሀገሪቱ ሕገመንግሥትና ሕግጋት ለሰብዓዊው መብት ደኅንነት የሚደነግጉትን፣ እንዲሁም ራሷ ኤርትራ ያፀደቀችውን ዓለምአቀፉን የሰብዓዊ መብት አዋጅ የሚቃረን ነው” ይላል ኣምነስቲ ኢንተርናሽነል።

ይኸው ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት ኤርትራ ነፃ መንግሥት የሆነችበት ፲፩ኛው ዓውዳመት በግንቦት ፲፮ የሚከበርበትን ድርጊት መነሻ በማድረግ ባዘጋጀው ዘገባው፣ የኤርትራው መንግሥት የተለየ አመለካከት ስላላቸው ብቻ የታሠሩትን ሁሉ እንዲፈታ፣ የቁምስቅልን አድራጎት እንዲያስወግድ፣ መላውን እሥረኞች አድላዊ ላልሆነ ለአንድ የፍትሕ ሥርዓት እንዲያቀርብ፣ እሥርቤትም ውስጥ ሰብዓዊ አድራጎትን እንዲያጠናክር፣ እንዲሁም ለሰላማዊው ንግግር መብት፣ ለሃይማኖት ነፃነት፣ ለጋዜጣም ነፃነት ዋስትና እንዲሰጥ አጥብቆ ይጠይቃል። የዓለም ኅብረተሰብ በበኩሉ፥ ለኤርትራውያን ስደተኞች ሙሉ ተገን እንዲሰጥ ኣምነስቲ ኢንተርናሽነል ማሳሰቢያውን አጉልቷል።

ኤርትራ ውስጥ የኅሊና/ማለት ሐሳባቸውን በነፃ የመግለጽ ነፃነታቸውን ተገፍፈው እሥርቤት ውስጥ ከተዶሉት ወገኖች መካከል የኤርትራን ነፃነት ያስገኙት የቀድሞ ሐርነት እንቅስቃሴ መሪዎችም ይገኙባቸዋል። የኤርትራው መንግሥት የቀድሞው ውጭ-ጉዳይ ሚኒስትር ኃይሌ ወልደንሴ እና በመስከረም ፲፱፻፺፬ ተይዘው የታሠሩት እውቅ ሃያስያን በኢትዮጵያ አንፃር በተካሄደው የድንበር ጦርነት ወቅትና ከዚያም በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ያበሩ ከሃዲዎች ናቸው ባይ ነው። አሥር ነፃ ጋዜጠኞችም ነበሩ እየታፈሱ የታሠሩት፣ መላው የግል ፕሬስም ነበር እንዲዘጋ የተፈረደበት። ለእሥርቤት የተዳረጉት ሁሉ የኢትዮጵያ ቅጥረኞችና ሰላዮች ናቸው የሚል ክስ ነው የተለጠፈባቸው፥ ግና ለዚሁ ውንጀላ አንዳች ማስረጃ የለም።

ከእሥረኞቹ መካከል አንዱ እንኳ የወንጀል ክስ አልተከፈተበትም ወይም በፍርድቤት ፊት አልቀረበም። ከታሠሩ ወዲህ ቤተሰቦቻቸው አይተዋቸው አያውቁም፣ የት እንደታሠሩ ወይም በየትኛው አያያዝ ላይ እንደሚገኙ ባለሥልጣናቱ አንዳች ፍንጭ አይሰጡም--ለመስጠት አይፈልጉም። በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች የፖለቲካ እሥረኞችም የት እንዳሉ አይታወቅም “እንደተሰወሩ” ናቸው ይላል ኣምነስቲ ኢንተርናሽነል።

ኣምነስቲ ኢንተርናሽነል ባገኘው መረጃ መሠረት፣ የእሥረኞች እና የተሰዋሪዎቹ እናቶች የልጆቻቸውን ሁኔታ ለመጠየቅ በሞከሩበት ወቅት “የመጠየቅ መብት የላችሁም” እስከመባል ነበር የደረሱት። የኤርትራው መንግሥት ስለ ሰብዓዊው መብት ጉስቁልና፣ ስለቁምስቅል መስፋፋት የሚቀርብበትን በማስረጃ ሠነድ የሚደገፈውን ሂስ ሁሉ እንደ “ስም ማጥፊያ ተንኮል” እና እንደ “መረጃ ጉድለት” እየቆጠረ ነው የሚያጣጥለው።

ኤርትራ ውስጥ በእሥረኞች ላይ ስለሚፈፀሙት ልይዩ የቁምስቅል አድራጎቶች ኣምነስቲ ኢንተርናሽነል ባሁኑ ዘገባው በቂ ማስረጃና ማብራሪያ እንዳለው አስገንዝቧል። በዚህም መሠረት፣ እሥረኞች በገመድ እየተጠፈሩ ለቀናት ወይም ለሣምንታት ሳያቋርጡ በተጠማዘዘ ኣካል ሲሰቃዩ እንዲቆዩ ይደረጋሉ፥ እነዚሁ ማሰቃያ ዘዴዎች ለምሳሌ “ሄሊኮፕተር”፣ “እየሱስ ክርስቶስ” የተሰኘው ቅጽል ስም ነው የተለጠፈባቸው( እንደ ክርስቶስ ስቅለት መሆኑ ነው)፣”ቁጥር-ስምንት” የሚል አነጋገርም ነው ያለው በቁምስቅሉ ረገድ። ከውትድርና አገልግሎት ለማምለጥ የሞከረ ወይም ወታደራዊ ጥፋት ፈፀመ፣ ወይም የፖለቲካ ተቃውሞ አነሳ ተብሎ የታሠረው ሰው የሚደርስበት መደበኛው ቅጣት ቁምስቅል ነው።

እሥረኞች በአሰቃቂ ሁኔታ ላይ ነው የሚወድቁት፣ በቆሸሹ የትህተምድር መሣግርት፥ በሐሩራማ የመርከብ ኮንቴይነሮች፣ በየፖሊስ ጣቢያውና በየወህኒው ምሥጢራዊ ጉሮኖዎች ውስጥ ነው የሚዶሉት። በቂ ምግብና ውሃ አያገኙም፣ ከቁምስቅል ቅጣት የመጣባቸውንም ቁስል ወይም ሕመም ማስታገሻ ሕክምና አይሰጣቸውም።

በውሁዳን ሃይማኖቶች ተከታዮችም ላይ የሚደረገው ክትትል በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በጣም እየተባባሰ ነው የሄደው። አማንያኑ ይህንኑ እምነታቸውን እንዲተው ለማስገደድ ወደ እሥርቤቶች እየተዶሉ ለቁምስቅል ቅጣት ነው የተዳረጉት። ባለሥልጣናቱ የእነዚሁኑ አማንያን መጽሐፍ-ቅዱሳት እስከማቃጠልም ነው የደረሱት።

የአምነስቲ ኢንተርናሽነል ዘገባ ቀጥሎ፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ አሁንም በቀጠለው ውጥረትና በተደቀነው የአዲስ ጦርነት ሥጋት አንፃር ያከለው አንቀጽ፥ ባለፈው ጦርነት በሁለቱም በኩል በቡርጌሶችና በጦርምርኮኞች ላይ የተፈፀመው ዓይነቱ የሰብዓዊ መብት በደል እንዳይደገም በጥብቅ ነው የሚያስጠነቅቀው።