1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀኝ አክራሪዎችና የማኅበራዊ መገናኛዎች

ሐሙስ፣ ነሐሴ 8 2006

ጀርመን ዉስጥ ኒዮ ናዚዎች ጥላቻና አመፅ የሚያቀጣጥል መልዕክቶቻቸዉን በማኅበራዊ መገናኛዎች ማሰራጨት መጀመራቸዉ ወጣቶች ላይ ተፅዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል ተገለጸ። የቀኝ አክራሪዎቹን መልዕክቶችየፌስ ቡክ ወይም ትዊተር አለያም ዩ ትዩብ ተጠቃሚዎች ባይደግፉትም ከሚጠቀሙበት ገጽ ላይ ወደሌሎች ሊያሰራጩት በሚችሉበት መልኩ የተቀነባበረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1CuKd
Rechtsextreme Propaganda im Netz Screenshot Neonazi Seite Zukunftsstimmen
ምስል Zukunftsstimmen

የድረገጽ መገናኛዉ መሥመር ከላይ ሲታይ የተለየ ነገር የያዘ አይመስልም። ምክንያቱም በዩ-ትዩብ ቪዲዮ አማካኝነት በአንድ ወጣት የፌስ ቡክ ማኅበራዊ መገናኛ ገጽ ላይ የተለጠፈዉ ወቅታዊ የሆሊዉድ ፊልም ርዕስን ያነገበ ነዉና። ሲከፍቱት ግን በተባለዉ የሆሊዉድ ፊልም ፈንታ የሚሰማዉ የኒዮ ናዚዎች የሚያነሳሳ መልዕክት ነዉ። በዚህ መልኩም ራሳቸዉን «የማይሞቱ» የሚሉት ኒዮ ናዚዎች ከስነምግባር አኳያ ፍፁም የጥፋት መልዕክታቸዉን ያሰራጫሉ። የተገኘዉን ተካፍሎ የሚያነበዉ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚም ከጀርባ ያለዉን የቀኝ አክራሪዎቹን መልዕክት ምንነት የሚረዳዉ ዘግይቶ ይሆናል። ይህ መርዛማ መልዕክት ወድጀዋለሁ ከሚለዉ ቁልፍ ጋ ተገናኝቶ ስለሚላክም በሺዎች የሚገመቱ የገጹ ተጠቃሚዎች ሳያስቡት ይጋሩታል። ይህ ቀኝ አክራሪዎቹ እንደፌስ ቡክ፣ ትዊተር እና ዩ-ቱዩብ ባሉ ማኅበራዊ መገናኛዎች መልዕክታቸዉን ለወጣቱ የኢንተርኔት ተጠቃሚ በሽምቅ ዉንብድና በእጅ አዙር ከሚያዳርሱባቸዉ መንገዶች የአንዱ ማሳያ ነዉ።

Rechtsextreme Propaganda im Netz Screenshot Neonazi Seite Wirkungsfeuer
ምስል Wirkungsfeuer

የፌደራል ሲቪክ ትምህርት ተቋም ፕሬዝደንት ቶማስ ክሩገር እንደሚሉትም እንዲህ ያለዉ አጋጣሚ የቀኝ አክራሪዎቹ ደጋፊ ያልሆኑት ወገኖች ሳይቀሩ የመልዕክታቸዉ አሰራጮች እንዲሆኑ ያደርጋል ይላሉ፤

«እናም እንዲህ ያለዉ ምንነቱ ያልተገለጸ መረጃ ልዉዉጥ በማኅበራዊ መገናኛዉ ባልተለመደ ሁኔታ በብዛት እየመጣ ነዉ። ይህ ነዉ እንግዲህ የቀኝ አክራሪዎችን አስተሳሰብ በምንም መልኩ የማይደግፉ ሰዎችም ሳይቀሩ ሳያዉቁት የመልዕክታቸዉ አከፋፋይ የሚያደርጋቸዉ።»

ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ በርሊን ላይ የቀኝ አክራሪዎች በኢንተርኔት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የቃኘ ዘገባ ቀርቧል። የዘገባዉ ዋና ሃሳብም ያለፈቃዳቸዉና ፍላጎታቸዉ የቀኝ አክራሪዎቹም መልዕክቶች የሚያሰራጩ ወገኖች ቁጥር መበራከቱን አመላክቷል። መረጃዎች ከብዙ ሰዎች ጋ በደቂቃዎች መካፈልም ሆነ መለዋወጥ የሚያስችሉት እንደ ፌስ ቡክ ትዊተርና፤ ቱምብለር እና ዩ ቱዩብ ያሉት ማኅበራዊ መገናኛዎችና መድረኮች ለቀን አክራሪዎቹ እጅግ ጠቃሚ የፕሮፓጋንዳ ማስተላለፊያ ዘዴዎች እንደሆኗቸዉ ይገልጻሉ ለወጣቶች የሚቀርቡ የኢንተርኔት ገጾችን የሚመረምረዉ ተቋም « ወጣቶችን ተከላካይ መረብ» ምክትል ኃላፊ ሽቴፈን ግሌዘር። ግሌዘር ኒዮ ናዚዎቹ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳና አመፅ መልዕክት የተሸከመዉን ቪዲዮ የትና እንዴት እንደሚያሰራጩት ሲገልጹ፤ በመጀመሪያ ማኅበራዊ ድረገጾች ለቀኝ አክራሪዎች ዋነኛ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ እየሆኑ መሄዳቸዉን መረዳታቸዉ ገልጸዋል። ባለፈዉ ዓመት 5,500 ጊዜ ካካሄዱት የገጾች ቅኝትም 70 በመቶዉ በፌስ ቡክ፤ ትዊተርና ዩ ትዩብ መተላለፉን ገልጸዋል።

Rechtsextreme Propaganda im Netz Screenshot Neonazi Video mit dem Titel Fluch der Karibik
ምስል YouTube

«በሙስሊም፤ በአይሁድ፤በሲንቲና ሮማ፤ እንዲሁም በግብረ ሰዶማዊ ዉያን ላይ ግልፅ የማነሳሳት መልዕክት። ማኅበራዊ መገናኛዎቹ በእርግጥም እጅግ ብዙ ናቸዉ። ያ ደግሞ በርካቶችን የሚያነቃንቅ ነዉ። በተለይ ደግሞ ስሜታዊ የሆኑ ንግግሮችና ርዕሰ ጉዳዮችን ቶሎ ነዉ የምንወስደዉ። እናም አንዳንዶች የጻፏቸዉን አስተያየቶችና ሌሎች ነገሮች ምን መዘዝ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ዳግም እንኳ ለማጤን ጊዜ ሳይወስዱ ነዉ የሚለጥፉት። እናም እንደምናየዉ ከፍተኛ የማነሳሳት አቅም አላቸዉ።»

ግሌዘር እንደሚሉትም ኒዮ ናዚዎቹ እና የእነሱ ክንፍ የሆኑት ቀኝ አክራሪዎች ጥላቻ ያዘሉ መልዕክቶቻችን በሁለት መንገዶች ያሳራጫሉ። ይኸዉም የነሱ መገለጫ የሆኑ ደረቅ መፈክሮችን ከመጠቀም ዉብና ማራኪ ቀለሞችን ተንተርሶ የፖፕ ባሕል እና መዝናኛ በሚመስሉ ሽፋኖች ማጀብ። ለምሳሌ እንደሚኪ ማዉስ ያሉ ታዋቂ ገጸባህሪያትን ወይም ኮኪ ሞንሰትርን ደጋግመዉ መጠቀማቸዉንም ያስረዳሉ። ተቋማቸዉ ባለፈዉ ዓመት ብቻም 1842 ጸያፍ መልዕክቶችን መርምሯል። የጀርመን የቤተሰብ ጉዳዮች ሚኒስቴር የወጣቶች አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ሊያደርጉ የሚችሉ የቀኝ አክራሪዎችን የኢንተርኔት ፕሮፓጋንዳ ለመከላከል የሚያስችል ዘመቻ በገንዘብ እንደሚደግፍ ጥናቱ በቀረበ ወቅት አስታዉቋል። ለዚህም 38 ሚሊዮን ዩሮ ከመጪዉ ዓመት አንስቶ ለቀጣይ አራት ዓመታት ተመድቧል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ