1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሸዋዬ በሞለታ

ሰኞ፣ የካቲት 5 2004

ለምግብ፤ ለመጠጥ፤ እና ለመሳሰሉ የዕለት ከዕለት ፍጆታዎች የሚዉል ነዉ።ይሁንና ጠበቃዉ እንዳሉት ከኖቬምበር አስራ-አምስት እስከ ፌብርዋሪ አስር የተሰጣት ገንዘብ አራት መቶ ዩሮ ነዉ።ሌላ--- ግን ጠበቃዉ አሻሽለዉ ለሸዋዬ የሚሰጠዉ በሳምንት መቶ ዩሮ ነዉ አሉ

https://p.dw.com/p/142pL
Blick auf die Insel Malta mit Hafen und Booten im Vordergrund
ሞልታምስል DW

13 02 12

                   
ኑሮ በሞልታ (ማልታም) የሚሏት አሉ ለሸዋዬ መጥፎ-የሚባል አይደለም።እየታከመች፥ በፈላ ዉሐ የተቀቀለ ሰዉነትዋ እያገገመ ነዉ።ወድሟም ከኢትዮጵያ መጥቶላታል።ግን በቀደም እንደነገረችን የሚቀር ብዙ አለ።ወይም ብዙዉ ነገር እንደተባለ፤ እንደተነገረዉ አይደለም።እሷ---ሥለ እሷ በእንግሊዝኛ የዘገቡ ወይም የእግሊዘኛዉን ዘገባ እንዳለ የገለበጡት-ሸዋይጌ ሙላሕ ይሏታል።ወይም ጋዳፊስ ናኒ።ሸዋዬ ሞላ ናት።የሞልታ-ኑሮ ሕክምናዋ እንዴትነት-የችግሯ ምንነት የፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።
               
«እዚሕ ሊናገሩት የማይቻል ጭካኔ ተፈፅሟል።ይሕ የሐኒባል ጋዳፊ ቤት ነዉ።እዚሕ የተፈፀመዉ በእዉነቱ ዘግናኝ ነዉ።ሸዋይጌ ሙላሕን፤ የሰላሳ አመቷን ኢትዮጵያዊት ሞግዚትን ተመልክቱ (አግኟት) ።»ሲ ኤን ኤን የተሰኘዉ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘጋቢ።«መታጠቢያ ቤት አስገባችኝ።እጆቼን የፊጥኝ አሰረችኝ።እግሮቼንም አሰረችኝ።አፌን ለጎመችዉ።ከዚያ በሕዋላ የደላ ዉሐ አናቴ ላይ ትቸልሰዉ ገባች።»


ነሐሴ ማብቂያ ከምዕራባዊ ትሪፖሊ የተሰራጨዉ ይሕ ዘገባ እና ዘገባዉን ያጀመበዉ የሸዋዬ ምሥል ዘገባዉን ባየዉ ሰዉ ዘንድ የሚፈጥረዉ ስሜት ብዙዎች እንዳሉት ዘግናኝ፥ አሳዛኝ፥ አናዳጅ፥ አስቆጪ ብሎ ማሳጠር አይገድም።የሸዋዬ ታሪክና ምሥል ለኢትዮጵያዉያን አሳዛኝ፥ አናዳጅ፥ የሚያስቆጣ ነዉ ብሎ ማለፍ ግን የስሜቱን ክረት፥ የግፉንም መጠን ማሳነስ ሊሆን ይችላል።

የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ አማት ማለት የቃዛፊ ወንድ ልጅ የሐኒባል ባለቤት አሊኔ በኢትዮጵያዊቷ ሞግዚት ላይ የፈፀመችዉ ግፍ-ጤነኛ አዕምሮ ያለዉ የሚፈፅመዉ መሆኑ ያጠራጥራል።ግን ተፈፀመ።


የአሊኔ ምግባር የሰዉ ልጅን የጭካኔ ርቀት፥ የማሳየቱን ያክል የሸዌዬ ጥንካሬ የሰዉ ልጅን ብርቱነት፥ የእነ-አሊኔ ሐኒባልን ጭቃኔ እያወቁ፥ ከእነሱ እጅ ሳይወጡ ሸዋዬን ለማሳከም የሞከሩት ባልደረቦችዋ የሰዉን ቅንነትን ጠቋሚ፥ የሐኪሞችዋ ፍራት የሰዉ ድክመቱን አመልካች ነዉ።ሸዋዬን የሜድትራኒያን ባሕርን አሻግሮ ሞልታ የዶለዉ ግን የሰዉ ልጅ ርሕራሄ ነዉ።

ባለፈዉ መስከረም ሞልታ ከገባች በሕዋላ በፈላ ሁሐ የተቀቀለ ሰዉነቷን ለማዳን ሁለቴ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል።ሙሉ በሙሉ ግን አልዳነችም።ጠበቃዋ ዶክተር ካቪየን አዞፓርዲ እንዳሉት ጤናዋ በእጅጉ ተሻሽሏል።ለሰወስተኛ ቀደ ሕክምናም ሆስፒታል ቀጠሮ አላት።
        
«እርግጥ ነዉ አሁን ሕክምናን በተመለከተ ጤናዋ በፊት ከነበረችበት በጣም ደሕና መሆኑን መጥቀስ አስፈላጊ ነዉ።በግምት ከአንድ ወር ከአስራ-አምስት ቀን በሕዋላ ሌላ ቀደ ሕክምና እስኪደረግላት ድረስ (ከዚሕ በፊት ከተደረገላት ቁስል) እስኪድን እየጠበቀች ነዉ።ሙሉ በሙሉ እስክትድን ድረስ የሞልታ መንግሥት የሚያስፈልጋትን ለሟሟላትና በሞልታ ቆይታዋ ደስተኛ መሆንዋን ለማረጋገጥ አስፈላጊዉን ሁሉ ያደርጋል።»

ይሕ በርግጥ አስደሳች ዜና ነዉ።አለም ጨካኞችን ብቻ ሳይሆን አዛኞችን፥ ክፉዎችን ብቻ ሳይሆን ደጎችን ፤ ንፉጎችን ብቻ ሳይሆን ለጋሶችን የያዘች ለመሆንዋም ተጨማሪ ምስክር። ሸዋዬ እንደምትለዉ ግን የሚያስፈልጋት ነገር የተገባዉን ቃል-ወይም በመገናኛ ዘዴዎች የተነገረዉን ያክል አልተሟላላትም።ባለፈዉ ታሕሳስ ሸዋዬን ለመርዳት ከኢትዮጵያ የመጣዉ ወንድሟም ተመሳሳዩን ይናገራል።
                 
ዶክተር ኦዞፓርዲ ለሸዋዬ ጥብቃ የቆሙት ሸዋዬን ለማሳከም ወደ ሞልታ ባስመጣት በሞልታ መንግሥት ተጠይቀዉ፣ በሞልታ መንግሥት ሙሉ ፍቃድ ነዉ።ግን እሳቸዉ እንደሚሉት ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ፤ተጠሪነታቸዉም ለደንበኛቸዉ ለሸዋዬ ብቻ ነዉ።ይሕን በማድረጋቸዉ ወይም ላገልግሎታቸዉ ከሸዋዬ፤ ሸዋዬን ከሚረዱት ድርጅቶችም ሆነ ከሞልታ መንግሥት የሚከፈላቸዉ የለም።በሌላ አባባል በነፃ ነዉ የሚያገለግሉት።

ሸዋዬ ገንዘብን በተመለከተ ላነሳችዉ ችግር ግን ጠበቃዉ አንድና ቀጥተኛ መልስ አልሰጡም።
            
«እራሴን ግልፅ ላድርግ እኔ ሸዋዬ ሥለምታገኘዉ ገንዘብን በሚመለከት ጉዳይ አልተሳተፍኩም።ይሁንና ትናንት አንተ ከጠየቅኸኝ በሕዋላ ጉዳዩን አጣርቻለሁ።እና ማለት የምችለዉ ለሚያስፈልጋት ነገር ምንም አትከፍልም።ለሕክምናዋ ምንም አትከፍልም።ሁሉንም የሚከፍለዉ መንግሥት ነዉ።አንተ የጠቀስከዉን ገንዘብ በተመለከተ እንደ ኪስ ገንዘብ የሚሰጣት ነዉ።ምን ያሕል እንደምታገኝ አላዉቅም።ትናንት ባገኘሁት መረጃ መሠረት ግን ከኖቬምበር አስራ-አምስት እስከ ዛሬ (ባለፈዉ አርብ ነዉ) አራት መቶ ዩሮ እንዳገኘች ተነግሮኛል።»

ይሕ ገንዘብ ለምግብ፤ ለመጠጥ፤ እና ለመሳሰሉ የዕለት ከዕለት ፍጆታዎች የሚዉል ነዉ።ይሁንና ጠበቃዉ እንዳሉት ከኖቬምበር አስራ-አምስት እስከ ፌብርዋሪ አስር-(ባለፈዉ አርብ ማለት ነዉ) በነበረዉ ሰወስት ወር ጊዜ በጥቅሉ ሸዋዬ የተሰጣት ገንዘብ አራት መቶ ዩሮ ነዉ።ሌላ-ግን ተያያዥ ጥያቄ ሳነሳባቸዉ ግን ጠበቃዉ የሰጡኝ መልስ ሌላ ነዉ።በሰወስት ወር አራት መቶ ዩሮ ያሉትን አሻሽለዉ ለሸዋዬ የሚሰጠዉ በሳምንት መቶ ዩሮ ነዉ አሉ።
            
«ባገኘሁት መረጃ መሠረት በሳምንት ቢያንስ አንድ መቶ ዩሮ ይሰጣታል።---መረጃዉን ያገኘሁት ከመንግሥት ነዉ።»

የሸዋዬ ወንድም ሞልታ የገባዉ ባለፈዉ ታሕሳስ ነዉ።ጠበቃዉ ባሉት መሠረት በሳምንት መቶ ዩሮ ለሸዋዬ ተሰጥቷን  ቢሆን እንኳን በተለይ ወድሟ ከመጣበት ከታሕሳስ ወዲሕ ላለዉ ጊዜ ለሁለቱ ወጪ በቂ አይደለም።ይሕንንም ቢሆን የሸዋዬን የቤት ኪራይና የቀለብ ወጪ የሚሸፍነዉ የቀጠር በጎ አድራጎት ድርጅት ነዉ።
            
ጠበቃዉም በዚሕ ይስማማሉ።
        
«አዎ በርግጥ እስካሁን የተሰጣትን ገንዘብ ያገኘችዉ የቀጠር መንግሥት ከዘረጋዉ የርዳታ መርሐ-ግብር ነዉ።የቀጠር መንግሥት በደል የተፈፀመባቸዉን ሰዎች ለመርዳት የመሠረተዉ የርዳታ መርሐ-ግብር አለዉ።እና እሷም ለዚሕ መርሐ-ግብር ከተመደበዉ ገንዘብ ወይም ርዳታ ተጠቃሚ ሆናለች።ምናልባትም ለዚሕ ይመስለኛል፤ ይሕ የርዳታ ገንዘብ ከቆመ የገንዘብ ችግር ያጋጥመኛል ብላ ሳትሰጋ አትቀርም።ነገር ግን መርሐ-ግብሩ ቢቆም የሞልታ መንግሥት ወዲያዉ ጣልቃ ገብቶ የሚያስፈልጋትን ገንዘብ ከራሱ በጀት ይሸፍናል።»

ገንዘቡን ከቀጠር በጎ አድራጊ ድርጅት ተቀብሎ ለለሸዋዬ የሚሰጠዉ ግን የሞልታ መንግሥት ወይም መንግሥት የወከለዉ ግለሰብ ነዉ።ይሕ ለምን እንደሆነ ወይም ረጂዉ ድርጅት በቀጥታ ለተረጂዋ ለምን እንደማይሰጥ ጠበቃዉም-ሸዋዬም አያዉቁም።በዚሕም ብሎ በዚያ ሸዋዬ እና ወድሟ እንዳሉት ከወር ከወር እወር የሚያደርሳቸዉ ገንዘብ አያገኙም።

የመኖሪያ ፍቃድ ሌላዉ ግልፅ ያልሆነ ጉዳይ ነዉ።ሸዋዬ ሞልታ ስትገባ የሞልታ መንግሥት የመኖሪያ ፍቃድ እንደሰጣት ተዘግቦ ነበር።እሷ እንደምትለዉ ግን መኖሪያ ፍቃድ ቀርቶ ፓስፖርቷም በእጇ የለም።በዚሕም ምክንያት የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ ለመግዛት እንኳን ወደ ዉጪ ስትወጣ እየፈራች እየተሸማቀቀች ነዉ።ሌላዉ ደግሞ በስሟ የተዋጣዉ ገንዘብ ነዉ።በጎ አድራጊዎች ለሸዋዬ መርጃ አርባ ሺሕ ዶላር ማዋጣታቸዉ ተዘግቦ ነበር።እስካሁን ግን ምንም የደረሳት ነገር የለም።
          
የመኖሪያ ፍቃድን እና የተዋጣዉን ገንዘብ በተመለከተ ጠበቃ አዞፓርዲ የሰጡት አስተያየት አለን።የሞልታ መንግሥት ተወካይን ለማነጋገር ያደረግነዉ ሙከራ አስካሁን አልተሳካልንም።የሸዋዬን፤ ጠበቃ በስልክ ካነጋገርን በሕዋላ የመንግሥትን ተወካዮች ለማነጋገር በምን ሞክርበት መሐል ጠበቃዉ ከሞልታ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸዉን ገልጠዉልናል።

የመንግሥትና የቀጠር የርዳታ ድርጅት ተወካዮች ደግሞ ሸዋዬን ማነጋገራቸዉ፤ የጎደላት ነገር ካለም ለማሟላት ቃል መግባታቸዉን ዛሬ ሰምተናል።በዚሕም ምክንያት የመኖሪያ ፍቃድን፤ የተዋጣዉን ገንዘብ፤ የወደፊት ኑሮዋን በተመለከተ ጉዳዩን ተከታትለን ወደፊት ለማቅረብ በቀጠሮ እንለያይ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ




   
 

 



 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ