ሶሪያ፥ ዩናይትድ ስቴትስና «ቀዩ መስመር»
ዓርብ፣ ነሐሴ 17 2005
የሶሪያ መንግሥትን ጦር ባለፈዉ ሮብ ርዕሠ-ከተማ ደማስቆ አካባቢ የሚገኝ የደፈጣ ተዋጊዎች ይዞታን በኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ደብድቧል በማለት ተቃዋሚዎቹ እየወነጀሉ ነዉ።መንግሥት ዉንጀላዉን አስተባብሏል።ምዕራባዉያን ሐገራት ጉዳዩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች እንዲጣራ አበክረዉ እየገፋፉ ነዉ።የሶሪያ መንግሥት እንደተጠረጠረዉ መርዛማ ጋዝ ተኩሶ ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ካንድ ዓመት በፊት ያስጠነቀቀችዉ «ቀይ መስመር» ተጣሰ ማለት ነዉ።በዚሕም ሰበብ ልዕለ-ሐያሊቱ ሐገር የሐይል እርምጃ እንድትወስድ ግፊት እየተደረገባት ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ግን፥ ክርስቲያን ኢግናትሲ እንደዘገበዉ የሐይል እርምጃ ለመዉሰድ የተዘጋጀች አይመስልም።የኢግናትሲን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ካንድ ዓመት በፊት «ቀይ መስመር» ያሉትን የማስጠንቀቂያ የሐሳብ ወሰን ማበጀታቸዉን ሲያዉጁ ብዙዎች የተረጎሙት፥ የሶሪያ መንግሥት ያን መስመር-በመርዛማ ጋዝ ፍንዳታ ከጣሰዉ፥ የዓለም ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገር ሐያል ጦር የበሽር አል-አሰድን ሕልቅት ለመፈጥረቅ አያመነታም ብለዉ ነበር።
የሶሪያ መንግሥትን ለማስወገድ የሚፋለሙት ጠላቶቹ እንደሚሉት ባለፈዉ ሮብ የመንግሥት ጦር ደማስቆ አጠገብ በሚገኝ የአማፂያን ይዞታን በመርዛማ ጋዝ አጥቅቷል።በጥቃቱ ሲያንስ-አምስት መቶ ሲበዛ አንድ ሺሕ ሰወስት መቶ ሰዉ መገደሉ ተዘግቧል።የሶሪያ መንግሥት ዉንጀላዉን አስተብሏል።ዉንጀላዉ መርማሪዎች ከተረጋገጠ ግን ለበሽር አል-አሰድ አደገኛ ሊሆን ይችላል።
የዚያኑ ያክል ኦባማንም ጦር እንዲያዘምቱ ከሚፈልገዉ ሐይል ጠንካራ ግፊት የሚያጋልጥ ነዉ።ይሕ ግን የመጀመሪያ አይደለም።በገለልተኛ አጣሪዎች አልተረጋገጠም እንጂ የሶሪያ መንግሥት ባለፈዉ ሰኔ መርዛማዉ ጋዝ ተኩሶ የኦባማን «ቀይ መስመር» መጣሱን ራሳቸዉ አሜሪካኖች አስታዉቀዉ ነበር።
የኦባማ መስተዳድር ግን የሶሪያ አማፂያንን ለማስታጠቅ ወሰነ እንጂ ብዙዎች እንደፈሩት፥አማፂያኑና ደጋፊዎቻቸዉ እንደተመኙት ጦር አላዘመተም።በምሕፃሩ MDR የሚባለዉ የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ የዋሽግተን ወኪል ዚልከ ሐሰልማን እንደምትለዉ የኦባማ የዉጪ መሪሕ ከቡሽ የተለየ ነዉ።«ኦባማ» ጋዜጠኛዋ እንደምታምነዉ ልዕለ ሐያሊቱ ሐገራቸዉ በጦር ሐይል ጡንቻ ዓለምን የምታስገብር «የዓለም ፖሊስ» እድትሆን አይፈልጉም።የድርድር መፍትሔ የሚሹ መሪ ሆነዉ መታወስን እንጂ።
የጀርመን የዉጪ መርሕ ማሕበረሰብ ባልደረባ ዮሴፍ ያኒንግ እንደሚሉት ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ሶሪያ ጦር የማታዘምተዉ አደገኛዉን መዘዝ ሥለምታዉቀዉ ነዉ።ያኒንግ እንደሚያምኑት የአሜሪካ ጦር ሶሪያ ከዘመተ የደማስቆ መንግሥትን የምትደግፈዉ ኢራን አሜሪካኖች ነገር እንደፈለጓት ነዉ የምትቆጥረዉ።የእስራኤል ደሕንነትም ላደጋ መጋለጡ አይቀርም።«ከዚሕም በተጨማሪ» ይላሉ ያኒንግ አሜሪካኖች «ጣልቃ መግባት» መጀመሪያዉ እንጂ ፍፃሜዉ እንደማይታወቅ ካለፈዉ አስር ዓመት ልምዳቸዉ በቅጡ መማር አለባቸዉ።
«ምክንያቱም በእንዲሕ ዓይነቱ ግጭት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ዉጤታማ ሊሆን እንደማይችል አሜሪካኖች ያዉቁታል።የአሜሪካ ጦር እንደዘመተ፥ እንዲዘምት ብቻ ሳይሆን ከዘመተበት ፈጥኖ እንዲወጣም አሜሪካኖች ላይ ወዲያዉ ግፊት ይደረግባቸዋል።»
በመሠረቱ ጣልቃ የመግባቱ አላማም ግራ አጋቢ ነዉ።አንድን ገዢን ማስወገድ? ከሆነ -ሳዳም ሁሴንን፥ ሙላሕ መሐመድን ዑመርን፥ቃዛፊን ከየአብያተ -መንግሥቱ አሸቀንጥሮ መጣል፥ መግደሉ በርግጥ ተችሏል።አሰድን መድገሙም አይገድም።ከዚያስ? ጆርጅ ቡሽ ይሉት እንደነበረዉ ሰላም እና ዲሞክራሲ ማስረፅ?-ያኒንግ «ሐሰት» ይሉታል።
«እኔ በግሌ እንደማምነዉ በሌለኛዉ የዓለም ክፍል በጦር ሐይል ጣልቃገብነት ሠላማዊ፥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት እና ምጣኔ ሐብታዊ ብልፅግናን ማምጣት ይቻላል ብሎ ማሰብ ሥሕተት ነዉ።አይቻልም»
የተቻለዉ ኢራቅ፥ አፍቃኒስታን፥ ሊቢያ የሚታየዉ ነዉ።ትርምስ።በጀርመን ምክር ቤት የአሜሪካ ጉዳይ ኮሚቴ አባልና የአረንጓዴዉ ፓርቲ ፖለቲከኛ ኦሚድ ኑሪፖር በበካላቸዉ አሜሪካ ሶሪያ ጦር የማታዘምተዉ በሁለት ምክንያት ነዉ ባይ ናቸዉ።አንደኛዉን ይጠይቃያሉ፥ «መርዛማዉን ጋዝ የተኮሰዉ ማነዉ?» ብለዉ።ሁለተኛዉ፥-
«በሐገሪቱ (ሶሪያ) ዉስጥ አደገኛ ጦርነት እየተደረገ ነዉ።የገንዘብ አቅማቸዉም ጣልቃ ለመግባት የሚያችል አይነት አደለም።ይሕ ማለት አሜሪካኖች ጦር ለማዝመት የሚያስፈልገዉ ነገር ሁሉ የላቸዉም።»
ሥለዚሕ አሜሪካኖች ቢያንስ ላሁኑ ጡንቻዉን ሰበብ ማድረጉን ነዉ-የመረጡት።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ