1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶሪያ፤ ማብቂያ ያጣዉ ጦርነት

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 12 2007

ጦርነቱ በርግጥ እንደቀጠለ ነዉ።አሰድን ከደማስቆ ቤተ-መንግሥት ጋር የምታስተሳስረዉ የሥልጣን ገመድ ግን እየተወጠረች፤ እየመነመነች፤ እየሰለለች ነዉ።ቶሎ ትበጠስ ይሆን?

https://p.dw.com/p/1GHNW
ምስል picture alliance/dpa/RIA Novosti

ስደተኞች እና የርዳታ ችግር

የሶሪያ መንግሥት ጦር ርዕሠ-ከተማ ደማስቆ አካባቢ አማፂያን «መሽገዉባቸዋል» የሚላቸዉን ሥፍራዎች በተከታታይ በተዋጊ ጄት እየደበደበ ነዉ።በተደጋጋሚዉ ድብደባ ክፉኛ በተጎዳችዉ ዱማ በተባለችዉ ከተማና አካባቢዋ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉ ተነግሯል።ካይሮ የሚገኘዉ ጀርመናዊ ጋዜጠኛ ብየርን ብላሼክ ተደጋጋሚዉ የጦር ጄት ድብደባ የፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድ መንግሥት «የመዳከሙ ምልክት» ነዉ ይላል።

እንደ ጋዜጠኛዉ ወግ ድርጊት- እዉነቶችን ከማፍታት ይልቅ እንደ ተንተኝ አስተያየት፤ ትንበያ የተጫጫነዉ ዘጋቢ ከአንድ ቪዲዮ ያገኘዉን የሰዉ-ጩኸት እና የተኩስ እሩምታን-የአማፂያኑ የድል ብሥራት ቃጭል ይለዋል።

ሐማ በተባለችዉ ከተማ ሠፍሮ የነበረዉ የፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድ መንግሥት ጦር ከተማይቱን ለቅቆ ሲወጣ ነዉ።የሰማነዉ የተባለዉ።የደማስቆ መንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚሉት ግን ጦራቸዉ የሐማ ይዞታዉን የለቀቀዉ የዉጊያ ሥፍራዉን አሻሽሎ ሌላ ሥፍራ ለመስፈር ነዉ።ሁሉም እንዳሻዉ ቢተረጉመዉም የሶሪያዉ ዉጊያ የፕሬዝደንት አሰድ የሐይማኖት ሐራጥቃ ተከታዮች ፤አለዊቶች በብዛት ይኖሩባታል ከሚባለዉ ግዛት መድረሱን ጠቋሚ ነዉ።ላታኪያ።

Syrien Krieg IS Tel Abyad
ምስል picture-alliance/dpa/S. Suna

የመንግሥት ጦር ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ አካባቢዎችን እየተቀማ ነዉ።ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የፕሬዝደንት አሰድ መንግሥት እስካሁን የሚቆጣጠረዉ ከአጠቃላይ የሐገሪቱ የቆዳ ስፋት አርባ በመቶ ያሕሉን ብቻ ነዉ።ቀስ በቀስ ክንዱ የዛለዉ ወይም የዛለ የሚመስለዉን የደማስቆ ሥርዓት ዳግም ሳያንሰራራ መንግሎ ለመጣል የአካባቢዉ ሐያል መንግሥታት ለአማፂያኑ የሚሰጡትን ድጋፍ እያጠናከፉ ይመስላሉ።

ሳዑዲ አረቢያ፤ ቀጠርም ሆነች ቱርክ ልዩነታቸዉን አቻችለዉ አራት ዓመት ገንዘብ፤ እዉቀት፤ ጊዜ ሐይላቸዉን ያፈሰሱላቸዉ አማፂያንን ለድል ለማብቃት እየተጣጣሩ ነዉ።ፕሬዝደንት አሰድ ባለፈዉ ወር ማብቂያ እንዳሉት ግን የጠላቶቻቸዉን ሴራ ለማክሸፍ የቆረጡ ነዉ-የሚመስሉት።

«አካባቢዎችን የሚቆጣጠረዉን ጦር ሐይል ጥንካሬና ፅናት ለመጠበቅ እና ዉድቀትን ለማስወገድ የየግዛቶቹን ጥበቃ አስፈላጊነት በቅጡ መገንዘብ አለብን።»

ይበሉ እንጂ አሰድ የዉጪዉ-ድጋፍ፤ የዉስጡም ምርኩዛቸዉ እየከዳቸዉ ይመስላል።እስካሁን ጠንካራ ድጋፍ የምትሰጣቸዉ ሩሲያ ቀዳሚዋ ናት።ከዚሕ ቀደም የተተኮሰዉ መርዛማ ጋስ ላደረሰዉ ጥፋት ተጠያቂዉ እንዲለይ የሚጠይቀዉን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ረቂቅ ዉሳኔን ሩሲያ ደግፋዋለች።ኢራን ትከተላለች።ቴሕራኖች የአሰድን መንግሥት ለረጅም ጊዜ ቢደግፉም የሶሪያ የግዛት ሉአላዊነት እና አንድነት እስከተጠበቀ ድረስ «አሰድ ኖሩም አልኖሩ» ብዙም እንደማይጨነቁ ብዙ ጊዜ ተናግረዋል።

Syrien TV-Auftritt Bashar Assad
ምስል picture-alliance/Press TV via AP video

ከሐገር ዉስጥ ጠንካራ ደጋፊያቸዉ የአለዊት እምነት ተከታዩ ነዉ።አብዛኛዉ ላታኪያ ግዛት የሚኖረዉ የዚሕ ሐራጥቃ ተከታይ ሕዝብ የምጣኔ ሐብቱ ችግር ሲጠናበት በመንግሥት ላይ ማንገራር ጀምሮ ነበር።በቅርቡ ደግሞ አንድ የአሰድ የቅርብ ዘመድ የግዛቲቱ ተወላጅ የነበረ አንድ የአየር ሐይል ባልደረባ መግደሉን ሲሰማ ወትሮም «ሆድ የባሰዉ» ሕዝብ መንግሥትን በደባባይ ሰልፍ ተቃዉሟል።

ጦርነቱ በርግጥ እንደቀጠለ ነዉ።አሰድን ከደማስቆ ቤተ-መንግሥት ጋር የምታስተሳስረዉ የሥልጣን ገመድ ግን እየተወጠረች፤ እየመነመነች፤ እየሰለለች ነዉ።ቶሎ ትበጠስ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ