1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶሪያ፤የዝብርቅርቁ ጦርነት ዝብርቅርቅ ተኩስ አቁም

ሰኞ፣ የካቲት 21 2008

ተንታኞች እንደሚሉት ግን ዋና አደራዳሪ ስታፋን ደ ሚስቱራ የአማፂና የደማስቆ ተወካዮችን አንዴ ዤኝቭ ሌላ ጊዜ ቪየና ከሚያግተለትሉ ላቭሮቭን ከሞስኮ፤ ኬሪን-ከዋሽግተን፤ዛሪፍን-ከቴሕራን፤ አል ጀባርን ከሪያድ ቢጠሩ የተሻለ ዉጤት ያገኛሉ።ላሁኑ ተኩስ አቁምም-ሞስኮና ዋሽግተኝ እንጂ ሌሎቹ አላስፈለጉም

https://p.dw.com/p/1I4Pw
ምስል Reuters/B. Khabieh

ሶሪያ፤የዝብርቅርቁ ጦርነት ዝብርቅርቅ ተኩስ አቁም

ተኩስ ቆሟል እንዳይባል የአዉሮፕላን ቦምብ-ሚሳዬል፤ የመድፍ-ታንኩ አረር ዛሬም እንደ ዛሬ አምስት ዓመቱ ሶሪያን ያወድማል።ጦርነቱ ቀጥሏል እንዳይባል አንዳድ አካባቢዎች ፀጥ ብለዋል።ከኒዮርክ ዲፕሎማቶች እስከ ብራስልስ ፖለቲከኞች፤ ከፋርስ መሪዎች እስከ አረብ ገዢዎች «የሶሪያን መፃዔ ዕድል የሚወስነዉ የሶሪያ ብቻ ሕዝብ ብቻ ነዉ» ይሉናል-በተደጋጋሚ።ሶሪያን ያወደመዉ ጦርነት ቀጠለም-ቆመ የሐገሪቱን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ተፋላሚ ሐይላት የተፈራረሙት ስምምነት የለም።የዋሽግተን እና የሞስኮ ሐያላን በሚፈልጉበት ስፍራ፤ በሚሹት ቀን ተኩስ እንዲቆም ተስማሙ።ተቀናቃኝ ተከታዮቻቸዉን አዘዙ።በከፊል ተኮስ ቆመ።በቃ።የዝብርቅርቁ ጦርነት ዝብርቅርቅ ተኩስ አቁም የዛሬ ትኩረታችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት በፈቃዳቸዉ የተደራጁት ነብስ አድን ሠራተኞች በትዊተር ገፃቸዉ የለጠፉት ፎቶ-ግራፍ የተዘጋ በር ያሳያል።በሩ ላይ «ዝግ ነዉ-በተኩስ አቁሙ ምክንያት» የሚል ፅሁፍ አለበት-እንደ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ።ሐኪሞች፤ነርሶች፤ የመጀመሪያ ሕክምና ርዳታ ሰጪዎች እና ሾፌሮች የሚካተቱባቸዉ የሶሪያ የነብስ አድን ሠራተኞች ባለፉት አራት-አምስት ዓመታት እንቅልፍና ዕረፍት የሚያገኙት ተዋጊዎች ሲደክማቸዉ ወይም ሲያርፉ ብቻ ነዉ።

«ባለ ነጭ ቆብ» በሚል ሥም የተደራጁት የነብስ አድን ሠራተኞች በመላዉ ሶሪያ 114 የሥልክ ጥሪ መቀበያ ማዕከል አላቸዉ።«አንዳድ ቀን በየአንዳዱ ማዕከል እስከ ሐምሳ የሚደርስ የድርሱልን ጥሪ እንቀበላለን» ይላሉ የቡድኑ ቃል አቀባይ አብዱረሕማን።ትናንት ግን በተለይ አሌፖ የሚገኙ ሠራተኞች በከተማይቱ ስታዲዮም እግር ኳስ ሲጫወቱ ነዉ የዋሉት።ተኩስ ቆሟል።

በጦርነቱ ለተቸገሩ፤ቤት አልባ ለቀሩ፤ ከቤት ንብረታቸዉ ለተፈናቀሉ ምግብ፤ መድሐኒትና የመጠለያ ቁሳቁስ ለሚያቀብሉ የርዳታ ሠራተኞች ግን የሚያርፉበት ሳሆን የሚባትሉበት ጊዜ ነዉ።ተኩስ ቆሟል እና።ኬር የተሰኘዉ የርዳታ ድርጅቶች ሕብረት የጀርመንና የላክሰምበርግ አስተባባሪ ኤሚሊ ጊኔስቱ እንደሚሉት በተለይ ለአሌፖ ችግረኞች ርዳታ ማቅረብ ፈተኛ፤ አጣዳፊም ነዉ።

Syrien Waffenruhe spielende Kinder
ምስል picture-alliance/dpa/M. Badra

«ችግረኞቹ ያሉበት ሁኔታ አሳዛኝ ነዉ። አምስት ዓመት ያስቆጠረዉ ጦርነት ያደረሰዉን ጥፋት በቀላሉ መግለፅ አይቻልም።አሁን ተኩስ ቢቆምም ባለፉት ተከታታይ ቀናት ዉጊያዉ ተባብሶ ነበር።ትምሕርት ቤቶች እና ሐኪም ቤቶች ሳይቀሩ በጄት ተደብድበዋል።በተለይ አሌፖ ከፍተኛ ዉጊያ ከተደረገባቸዉ አካባቢዎች አንዷ ናት።ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ከሰባ ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።»

የሰዉ ልጅ ዕዉቀት፤ ጥበብ የፈለቀባት፤ ፖለቲካዊ ሴራ፤ ሸር፤ ሐይማኖቱ የፋፋባት፤ ታለቁ አሌክሳንደር የቆመጠላት፤ቱርኮች የተራቀቁባት፤ አቡ አብዱላሕ መሐመድ ኢብን ባቱታ የተማረከላት፤ ዊሊያም ኤቶን ያወደሳት ያቺ ጥንታዊ ማራኪ፤ ዉብ ከተማ ዛሬ የጥፋት ተምሳሌት ሆናለች።አሌፖ።

ቱርኮች፤ኩርዶች፤አረቦች፤አሶሪያዎች፤ ሙስሊሞች፤ ክርስቲያኖች፤ ሐይማኖት የለሾች ለዘመነ-ዘመናት የኖሩባት ያቺ የሚሊዮኖች ከተማ አሁን የእልቂት-ፍጅት፤ የጥፋት ካስማ፤ የሶሪያ ጥፋት ምሳሌ ሆናለች።የሶሪያ የምጣኔ ሐብት ቋት፤ የጥበብ-ሥልጣኔ መስራቾቹ የልጅ፤ ልጅ፤ ዉላጆች ዛሬ አንድም ተፈናቃይ አለያም ስደተኛ ሆነዉ የዉጪ ምፅዋት ጠባቂ ናቸዉ።

በሶሪያ የሠዓት አቆጣጠር ካለፈዉ ቅዳሜ እኩለ-ሌት ጀምሮ ተኩስ በመቆሙ ነጭ ቆብ የተሰኘዉ የነብስ አድን ሠራተኞች ሕብረት እንደሚለዉ ትናንት ዕሁድ ከአሌፖ የደረሳቸዉ የድረሱልኝ ጥሪ አስር ብቻ ነዉ።ሠላም ነዉ።ያም ቢሆን ሠራተኞቹ ኳስ የሚጫዎቱት የአምቡላንስ መኪኖቻቸዉን ከነሙሉ የርዳታ ትጥቃቸዉ ስታዲዮሙ አጠገብ ደርድረዉ ነዉ።«የሚሆነዉ አይታወቅም» ይላሉ ቃል አቀባይ አብዱረሕማን።የኬር አስተባባሪ ኤሚሊ ጊኔትስ በፋንታቸዉ አጋጣሚዉን ለመጠቀም «መጣደፍ አለብን» ባይ ናቸዉ።

Schweiz Genf PK Staffan de Mistura
ምስል Reuters/P. Albouy

«እኛ ኬሮችም ሆንን ሌሎች በዕርዳታ አቅርቦቱ የተሠማሩ ድርጅቶች የተኩስ አቁሙ እጅግ አስፈላጊያችን ነዉ።(ጊዜዉን) ፈጥነን መጠቀም አለብን።እዚያ ላሉት ሰዎች ርዳታ ለማቀበል በጣም አስፈላጊዉ ነገር ሠላም ነዉ።የተኩስ አቁሙ ከዚያ ለመድረስ አንድ ትንሽ እርምጃ ሊሆን ይችላል።ባለፉት ቀናት እንዳየነዉ ተፋላሚዎቹ ቃላቸዉን ሥለማክበራቸዉ ብዙም ማረጋገጪያ አላየንም።በኛ አመለካከት ተፋላሚ ሐይላት ቃላቸዉን እንዲጠብቁ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግፊት ማድረግ አለበት።»

«ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ» አንድ ሥም እንጂ አንድ አቋም የለዉም።አምስት ዓመቱን ያስቆጠረዉ ጦርነት እስካሁን ያደረሰዉን ያክል ጥፋት እንዲያደርስ ያደረገዉ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የሚባለዉ ሐያል-ሐብታም ዓለም ተፃራሪ ሐይላትን ደግፎ በጦርነቱ በቀጥታ በመሳተፉ ነዉ።

የዛሬ አምስት ዓመት ግድም የፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድን መንግስት በመቃወም የጠመንጃ ዉጊያ የጀመሩት አማፂያን በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ።ዛሬ ከሶሪያ መንግስት ሌላ፤ ባንድ በኩል በዩናይትድ ስቴትስ እና በተባባሪዎችዋ፤ በሌላ በኩል በሩሲያና በአጋሮችዋ የሚደገፉ፤ በሰወስተኛ ረድፍ ከሁለቱም ያልወገኑ ከአንድ መቶ በላይ ደፈጣ ተዋጊ ቡድናት አሉ።

ጦርነቱ ሲጀመር ከነበሩት አማፂያን አብዛኞቹ ከሐይማኖታዊ ፅንፍ የራቁ፤የዉጪ ዕርዳታም የማያገኙ ነበሩ።ዛሬ ግን አብዛኞቹ አማፂያን ግራ-ቀኝ በቆሙ የዓለም ሐያል-ሐብታም መንግሥታት የሚደገፉ፤ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ከፅንፈኛ ቡድናት ጋር የሚተባበሩ ናቸዉ።የጀርመኑ የሠላምና የግጭት ጉዳይ ጥናት ተቋም ባልደረባ ዳንኤል ሙለር እንደሚሉት አማፂያኑ እንደየ አቋማቸዉ ከተለያዩ ሐገራት ድጋፍ ያገኛሉ።

CARE Arbeiten in Syrien
ምስል CARE

«አብዛኞቹ የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎች መጀመሪያ ላይ ከሐይማኖታዊ ሐራጥቃ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸዉም።ጂሐዲስቶች አልነበሩም።ከዉጪም ምንም ዓይነት ድጋፍ አያገኙም ነበር።መንግሥትን የሚወጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ማሕበራት ወይም አማፂያን ነበሩ።በሒደት ግን ወደ ፅንፈኝነት ያዘነብሉ ገቡ።በሚከተሉት ሐይማኖታዊ አስተምሕሮ ላይ በመመሥረትም ከዉጪ በተለይም ከባሕረ-ሠላጤዉ አካባቢ ሐገራት ድጋፍ ያገኛሉ።»

ሐማኖታዊ ፅንፈኝነትን በግልፅ የሚያራምዱት እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS ወይም ዳአሽ) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን እና የአል-ኑስራ ግንባር የሚባለዉ ቡድን በርካታ አካባቢዎችን የሚቆጣጠሩ በጣም ጠንካራ ተዋጊ ሐይላት ናቸዉ።ሩሲያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ባደረጉት ሥምምነት መሠረት ካለፈዉ ቅዳሜ እኩለ ሌት ጀምሮ የፀናዉ ተኩስ አቁም እነዚሕ ቡድናትን እና ከነዚሕ ቡድናት ጋር የሚደረገዉን ዉጊያ አይመለከትም።

በሩሲያ የጦር ጄቶች የሚደገፈዉ የሶሪያ መንግሥት ጦር ዛሬ ጠዋት አሌፖ አካባቢ በመሸጉ የዳአሽ ተዋጊዎች ላይ በከፈተዉ ጥቃት አንድ ሥልታዊ መንገድ ተቆጣጥሯል።የዩናይትድ ስቴትስና የተባባሪዎችዋ መንግሥታት የጦር ጄቶች የሁለቱን ፅንፈኛ ቡድናት ይዞታዎች መደብደባቸዉም እንደቀጠለ ነዉ።

እና ጦርነቱ «ቆሟል» ምክንያቱም የሶሪያ መንግስት ጦር እና ምዕራባዉያን መንግሥታት «ለዘብተኛ» የሚሏቸዉ አማፂያን አይዋጉም።ደግሞ በተቃራኒዉ ጦርነቱ «አልቆመም» ምክንያቱም-የሶሪያ መንግሥት፤ ሩሲያ እና ተባባሪዎቻቸዉ፤ ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ «አሸባሪ» በሚሏቸዉ ደፈጣ ተዋጊዎች ላይ የከፈቱትን ጥቃት አላቆሙም።ምሥቅልቅል እዉነት።በዚሕ አለማብቃቱ ነዉ-የባሰዉ።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል፤ የዩናይትድ ስቴትስ ታማኝ ወዳጅ እና ከደማስቆ መንግሥት ግንባር ቀደም ጠላቶች አንዷ-ቱርክ እንደ ዳዓሽ ሁሉ የሶሪያ ኮርዶችን አማፂ ቡድን መደብደቧን እንደምጥቀጥል እየዛተች ነዉ።ለሶሪያ መንግሥት ደግሞ በምዕራባዉያን እና በአረቦች የሚደገፉት አማፂያን በሙሉ አሸባሪዎች ናቸዉ።ለነገሩ፤ የፖለቲካ ተንታኝ ዳንኤል ሙለር እንደሚሉት ከፅንፈኞች ጋር ግንኙነት የሌለዉ ቡድን የለም።

«በአምስት ዓመቱ ጦርነት ከቀድሞዎቹ ተቃዋሚ ቡድናት ንፁሕ መኖሩን ፈጣሪ ይወቅ።አንዳዶቹማ ከእስላማዊ ፅንፈኞች ጋር ጥብቅ ግንኙነት መሥርተዉ ነዉ የሚዋጉት።በሶሪያዉ ጦርነት ISIS ከመሠሉ ፅንፈኛ ቡድናት ጋር ምንም ዓይነት ትብብር የሌለዉ የለም ወይም በጣም ትንሽ ነዉ።»

ተኩስ አቁም እንዲደረግ የሩሲያ እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታት ተስማሙ እንጂ፤ በሶሪያ መንግሥት ይሁን በአማፂያኑ የተፈረመ ሥምምነት የለም።ይሁንና የተለዩ መንግሥታት፤ የተባበሩት መንግሥታት ዲፕሎማቶችና የርዳታ ድርጅት ሠራተኞች እንደሚሉት ተኩስ አቁሙ ዘላቂ ሥምምነት ለማድረግ እንደ መነሻ ሊያገልግል ይችላል ነዉ-ተስፋዉ።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር አንዱ ናቸዉ።

«ረጅም ጊዜ ያወዛገበዉ ተኩስ አቁም አሁን ገቢራዊ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።ተኩስ አቁሙ በሶሪያ ያለዉን ሁኔታ ቀይሮ ሶሪያ ዉስጥ ሕዝቡ የሚፈልገዉን (ዘላቂ) ለማስፈን ይረዳል የሚል ተስፋ አለኝ።»

እስካሁን ድረስ የዉጪዎቹም፤ የዉስጦቹም ተፋላሚ ሐይላት አንዱ ሌላዉን መዉቀስ-ማዉገዛቸዉ አልቀረም።በተለይ አስራ-ሰባት አማፂ ቡድናትን አስተባብራለሁ የሚለዉ ቡድን የሶሪያ ጦርና የሩሲያ ጄቶች ተኩስ አቁሙን ጥሰዉ ጥቃት እያደረሱ ነዉ በማለት ይወነጅላል።መንበሩን-ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ ያደረገዉ ቡድን እንደሚለዉ የሩሲያ የጦር ጄቶች እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ ብቻ ተኩስ አቁም የተደረገባቸዉ አካባቢዎችን 26 ጊዜ ደብድበዋል።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ግን «እራሳችን የተስማምንበትን ዉል እራሳችን የምንጥስበት ምክንያት የለም» ባይ ናቸዉ። መቶ በመቶ ብሎ ተኩስ አቁምም የለም።ያም ሆኖ ጅምሩ በላቭሮቭ እምነት ለዘላቂ ሠላም ጥሩ መሠረት ነዉ።

Syrien Latakia Russischer Kampfjet Sukhoi Su-34
ምስል picture-alliance/dpa/ V. Savitsky

«ተኩስ አቁሙ እንደሚከበር መቶ በመቶ ዋስትና መስጠት አይቻልም።አሁን የታየዉን መልካም ጅምር ለዘላቂዉ ለማፅናት የሚረዱ መሠረቶች ግን አሉ።»

የተባበሩት መንግሥት ድርጅት፤ የሶሪያ ተፋላሚዎችን ለማደራደር ለመጪዉ ሳምንት ቀጠሮ ይዟል።በድርድሩ ከአንድ መቶ ዓማፂ ቡድን ስንቱ እንደሚወከል ግልፅ አይደለም።ብዙ ተንታኞች እንደሚሉት ግን ዋና አደራዳሪ ስታፋን ደ ሚስቱራ የአማፂና የደማስቆ ተወካዮችን አንዴ ዤኝቭ ሌላ ጊዜ ቪየና ከሚያግተለትሉ ላቭሮቭን ከሞስኮ፤ ኬሪን-ከዋሽግተን፤ዛሪፍን-ከቴሕራን፤ አል ጀባርን ከሪያድ ቢጠሩ የተሻለ ዉጤት ያገኛሉ።ላሁኑ ተኩስ አቁምም-ሞስኮና ዋሽግተኝ እንጂ ሌሎቹ አላስፈለጉም።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ