1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማልያና የአውሮፓው ኅብረት፧

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 9 1999

በሞቐዲሹ፧ የታጣቂ የሃውያ ጎሣ ሚሊሺያ ጦረኞችን ትንኮሣ ለመግታት በተወሰደ መጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ፧ የብዙ ሲቭሎች ህይወት ሳይቀጠፍ አልቀረም የሚል መልእክት ለአውሮፓው ኅብረት ደርሶ ነበር።

https://p.dw.com/p/E0YW
ሰላም ለማስከበር ሞቐዲሹ የገቡት የዩጋንዳ ወታደሮች፧
ሰላም ለማስከበር ሞቐዲሹ የገቡት የዩጋንዳ ወታደሮች፧ምስል AP

የአውሮጳው ኅብረት የልማት ኮሚሽን ስለዚህ ጉዳይ መረጃ ካለው እንዲያብራራ፧ የልማት ኮሚሽነሩን ቃል አቀባይ Amedeu Altafaj ን ተክሌ የኋላ ጠይቋቸው ነበር።
«የአውሮፓው ኅብረት በዚያ ሁኔታውን መርምሮ እንዲህ ነው ለማለት ችሎታው፧ ኃይሉም፧ መሣሪያውም የለውም። ባለፉት ጊዜያት ያሳሰበንን ጉዳይ አሁንም ድረስ ያለውን ኃይልን ከመጠን በላይ መጠቀምን በተመለከተ ማሳሰባችን አልቀረም፧ በተለይ ባለፉት ሳምንታት፧ በሞቐዲሹ እንደሆነው ማለት ነው። ህዝቡ፧ በሁለት ወገን ሆኖ ለይቶ ማነጣጠር በማይቻልበት የተኩስ ልውውጥ ገፈት ቀማሽ ሆኗል። ሰብአዊ እርዳታ ማግኛው መሥመርም ከፍልሚያው ጋር በተያያዘ አልተከበረም። ስለሆነም ውዝግቡ የሚመለከታቸው ሁሉ ዓለም አቀፉን ሰብአዊ ህግ ማክበር ግዴታቸው ስለሆነ ለዚህ ተገዢ እንዲሆኑ እናሳስባለን። ይህ እንዲከበር፧ ያለማቋረጥ ግፊት እናደርጋለን። ምክንያቱም የሶማልያ ህዝብ፧ እስካሁን እጅግ ተሠቃይቷል። ያሁኑ ሁኔታም በቸልታ የሚታይ አይደለም። የምንቀበለው አይደለም።«
ባለፈው ሳምንት የሶማልያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮችና የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሞቐዲሹ ውስጥ፧ ከታጣቂ ሚሊሺያዎች ጋር ባደረጉት ያገረሸ ውጊያ ሳቢያ ጋላጋዱድ ከተባለው አካባቢ ብቻ 124,000 መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር። ካለፈው ጥር ወር ማለቂያ ገደማ ወዲህ ከመዲናይቱ ከሞቐዲሹ አንድ ሚልዮን ኑዋሪዎች መካከል 208 ሺው ማለትም፧ ከአንድ አምስተኛ በላይ የሚሆኑት ከተማይቱን ለቀው መውጣታቸውን ይኸው ኮሚሽን አስታውቋል። የአውሮፓው ኅብረት ሶማልያ ውስጥ ዕርቀ-ሰላም እንዲወርድ ከአጎራባች አገሮች በተለይም ከ ኢ ጋ ድ አባል መንግሥታት ጋር ጠንከር ያለ ትብብር እንደሚሻ የኅብረቱ የልማት ኮሚሽን ይገልጻል። ኀብረቱ፧ ሶማልያን ለማረጋጋት በገንዘብም በዲፕሎማሲም የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረጉ አልቀረም።
«የአውሮፓው ኅብረት እርግጥ ነው፧ የአፍሪቃን የሰላም አስከባሪ ኃይል በሶማልያ ለመደገፍ መወሰኑ አይታበልም። ይሁንና ፀጥታ የማስከበሩ ጥረት ተፈላጊው የፖለቲካ እርምጃ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በጥብቅ ነው ያስገነዘበው። በሶማልያ ቀጣይነት ላለው ሰላምና መረጋጋት ሦስት ዓምዶች የምንላቸው፧ ፀጥታ አጠባባቅ የአካባቢው አገሮች አዎንታዊ አስተዋጽዖ፧ እንደሚታወቀው የሶማልያ ውዝግብ፧ የውስጥ ውዝግብ ብቻ ሳይሆን፧ አካባቢያዊ ነው። ሦስተኛውና ምናልባትም ላቅ ያለ ትርጓሜ የሚሰጠው፧ በሶማሌዎች መካከል የሚደረግ የፖለቲካ ውይይት ነው። ይህ የፖለቲካ ውይይት ደግሞ፧ በተቻለ መጠን፧ የሶማልያን ኅብረተሰብ በመላ ሊወክሉ የሚችሉ ፓርቲዎችን ሁሉ ያቀፈ መሆን ይኖርበታል።«
የሶማልያው የዕርቀ-ሰላም ጉባዔ፧ ሁከት አልተወገደም በሚል ሰበብ መሸጋሸጉ የሚታወስ ነው። በሰኔ ወር ይካሄዳል የተባለው የዕርቀ-ሰላም ጉባዔ፧ የቀድሞው ፕሬዚዳንትና የዕርቀ-ሰላሙ ጉባዔ ሊቀ-መንበር አሊ መህዲ መሐመድ እንዳስታወቁት ከሆነ፧ አሁንም እንደገና በመሸጋሸግ፧ ቅዳሜ 7 ቀን 1999 ዓ ም ይሆናል የሚከፈተው።