1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፣ የመርከብ ዘረፋ እና የአለም ምግብ ድርጅት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 14 1999

«አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፈጣን እርምጃ ካልወሰደ ምግብ የሚያስፈልገዉ ሕዝብ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ለረሐብ ይጋለጣል።»

https://p.dw.com/p/E0YL
የአለም ምግብ ድርጅት
የአለም ምግብ ድርጅት

አለም አቀፉ ማሕበረብ ወደ ሶማሊያ የሚቀዝፉ መርከቦችን የሚዘርፉና የሚያግቱ ሐይላትን ካልተቆጣጠረ ለሶማሊያ ሕዝብ የሚላካዉ ርዳታ ሙሉ በሙሉ እንደሚቋረጥ የአለም ምግብ ድርጅት አስጠነቀቀ።የርዳታ፤ የንግድና የአሳ ማጥመጃ መርከቦች በተደጋጋሚ በመዘረፍ ወይም በመታገታቸዉ የመርከብ ኩባንዮች መርከቦቻቸዉን ወደ ሶማሊያ አንልክም እያሉ ነዉ።በቅርቡ የአለም ምግብ ድርጅትን 850 ቶን የርዳታ ዕሕል የጫነ መርከብ ወደ ሶማሊያ እንዳይሄድ አከራዩ ድርጅት ከልክሏል።ነጋሽ መሐመድ በናይሮቢ የአለም ምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ፒተር ስመርዶምን አነጋግሮ የሚከተለዉ ዘገባ አጠናቅሯል።

ሶማሊያ ችግር በተለይ የምግብ ችግር ጠፍቶ-አያዉቅም።ያሁኑ ደግሞ በአለም ምግብ ድርጅት የናይሮቢ ቅርንጫፍ ቃል አቀባይ ፒተር ስመርዶም እንደሚሉት ከእስካሁኑ የከፋ ነዉ።


«አሁን ደግሞ በቅርቡ በነበረዉ ዉጊያ ከመቅዲሾ ብቻ ከሰወስት እስከ አራት መቶ ሺሕ ሕዝብ በመፈናቀሉ በጣም ብዙ ተጨማሪ ሕዝብ ምግብና ሌሎች የሠብአዊ ርዳታዎች ያስፈልጉታል።»

ከሰብአዊና ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ተደጋጋሚ ጥሪ በሕዋላ መርዳት የሚችለዉ አለም እያዘገመም ቢሆን መለገሱ አልቀረም።በብዙ ጉትጎታ የተገኘዉ ርዳታ-ከርዳታ ፈላጊዉ እንዳይደርስ ሌላ እንቅፋት መደንቀሩ-ነዉ ያሁኑ ጭንቅ።ዘረፋ።

«ባሁኑ ወቅት የአለም ምግብ ድርጅት መርከቦቻቸዉን ወደ ሶማሊያ የባሕር ክልል የሚልክቡ ኩባንዮች ጨርሶ አይኖሩም የሚል ሥጋት አለዉ።ምክንያቱም መርከቦቻቸዉ ቤዛ በሚጠቅቁ ሐይላት ይታገታሉ ብለዉ ሥለሚፈሩ።በዚሕም ምክንያት የአለም ምግብ ድርጅት እርዳታ የሚያቀብልበት ዋና መሥመር በዘራፊ (ወይም አጋቾች) ሙሉ በሙሉ ሳይዘጋበት አይቀርም።»

ለአብዛኛዉ የሶማሊያ ተፈናቃይ እና ችግረኛ ሕዝብ ምግብ የሚያደርሰዉ የአለም ምግብ ድርጅት ነዉ።ድርጅቱ ሰማንያ በመቶዉን የምግብ ርዳታ የሚልከዉ ደግሞ በባሕር ነዉ።የባሕር መስመር ተዘጋ-ማለት ፒተር ስመርዶም እንደሚሉት ምግብ ፈላጊዉ ተራበ ማለት ነዉ።

«አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፈጣን እርምጃ ካልወሰደ ምግብ የሚያስፈልገዉ ሕዝብ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ለረሐብ ይጋለጣል።»

አለም አቀፉ ማሕብረሰብ ሶማሌዎችን ከረሐብ ለመዳን-እርዳታ እንደሰጠ ሁሉ የሰጠዉ ርዳታ ከፈላጊዎቹ እንዲደርስ ዘራፊዎችን መቆጣጠርም አለበት-ነዉ የምግብ አቅራቢዉ ድርጅት አቤቱታ።እንደገና ስመርዶም።

«በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ መሪዎች አስፈላጊዉን መፍትሔ ለማግኘት ባስቸኳይ ተሰብስበዉ ሥለ ችግሩ እንዲወያዩ አጥብቀን እንጠይቃለን።እንዳልከዉ ሶማሊያ ባሕር ላይ መርከቦች ሲዘረፉ ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም።ይሁንና በዚሕ አመት ዘረፋ-እና እገታዉ በጣም ተባብሷል።በያዝነዉ አመት እስካሁን ድረስ ብቻ አምስት መርከቦች ታግተዋል።»

ስመርዶም-ይሕ አመት ያሉት ሁለት ሺሕ ሰባት ገና መንፈቁን አልጨረሰም።በትንሹ በወር አንድ መርከብ ታግቷል-ማለት ነዉ።እየተደጋገመ-እየሰፋ የመጣዉን ዘረፋ ባስቸኳይ ለመከላከል-ቃል አቀባይ ፒተር ስመርዶም እንደሚሉት የሶማሊያ ጉዳይ ይመለከተናል የሚል በሙሉ ሐላፊነት አለበት።

«የሶማሊያ ጉዳይ የሚመለከታቸዉ ሐገራት ፈንታ ነዉ።የሶማሊያ ሕዝብ ችግር የሚያሳስባቸዉ፣ ችግሩ እንዲቃለል የሚፈልጉትን ሁሉ የሚመለከት ነዉ።ማድረግ የሚችሉ እና ያለባቸዉን መወሰን የሚገባቸዉ እነሱ ናቸዉ።በርግጥ ብዙ ነገር ሊደረግ ይችላል።ፌደራላዊ የሽግግር መንግሥት አለ።የፑትላንድ ከፊል ራስ-ገዝ መስተዳድር አለ።እነዚሕ ሁለቱ ዘራፊዎቹ ወደሚንቀሳወሱበት የባሕር ጠረፍ ሐይል ማሰማራት ይችላሉ።ከዚሕም በተጨማሪ አንተ እንዳልከዉ (የሌሎች) የባሕር ሐይላት እርምጃ ሊወስዱባቸዉ ይችላሉ።ዘራፊዎቹ ከሶማሊያ የባሕር ክልል ብዙ ርቀዉ በሚገኙ አንዳዴም በአለም አቀፍ የዉሐ ክልሎች ላይ አደጋ ያደርሳሉ።»

ባለፈዉ አምስት ወር ተኩል ከታገቱት መርከቦች ሌላ ስምንት መርከብ ወይም ጀልባዎች አደጋ ተጥሎባቸዋል።