1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 15 2009

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትውልደ ኤርትራዊው ስዊድናዊ የ17 ዓመት አጥቂን ዛሬ በ10 ሚሊዮን ዩሮ  ከስዊድኑ AIK ቡድን ማስፈረሙን ገልጧል። የአፍሪቃ ዋንጫ እግር ኳስ ግጥሚያ ዛሬ እና ነገም ይከናወናል። በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ የተለያየው የጂማ አባቡና አሰልጣኝ ከቡድኑ መነሳታቸው ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/2WGtw
Africa Cup Togo vs Marokko
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

ስፖርት፣ ጥር 15፣ 2009 ዓም

የአፍሪቃ ዋንጫ እግር ኳስ ግጥሚያ አጓጊ ኮኗል፤ ዛሬ እና ነገም ይከናወናል። እስካሁን ጋና እና ሴኔጋል  ሁለት ጨዋታ ብቻ አከናውነው ከየምድባቸው ስድስት ስድስት ነጥብ መሰብሰብ ችለዋል። ሦስት ጨዋታዎችን ያከናወነችው ቡርኪና ፋሶ እና በሁለተኛ ጨዋታዋ 4 ነጥብ የያዘችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከየምድባቸው መሪዎች ናቸው። በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ የተለያየው የጂማ አባቡና ቡድን አሰልጣኝ ከቡድኑ መነሳታቸው ተገልጧል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት አርሰናል ሲድል ሲቀናው፤ የአምናው የዋንጫ ባለድል ላይስተር ሲቲ ዳግም ሽንፈት ተከናንቧል። ቸልሲ ግስጋሴውን እንደቀጠለ ነው።

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ አዳማ ከተማ በ24 ነጥብ መሪነቱን አስጠብቋል። ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ23 እና 22 ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በ12ኛ ሳምንቱ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ጅማ አባቡና ትናንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው ግጥሚያ አንድ እኩል አቻ ተለያይቷል። ከአሰልጣኙ ደረጄ በላይ ጋርም መለያየቱ ታውቋል። ጅማ አባቡና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌን በምትኩ መቅጠሩ ተዘግቧል። የጅማ አባቡና የቀድሞው አሠልጣኝ አቶ ደረጄ በላይን በስልክ እንደገለጡልን ከሆነ አንዳንድ በቡድኑ ዙሪያ ያሉ ሰዎች «ነጻነት ስላልሰጡኝ» በተጨማሪም «ጫናው ሲበዛብኝ» ከቡድኑ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር «እዚህ ውሳኔ ላይደርሻለሁ» ብለዋል። «እዚያ አካባቢ ያለው ጥቂት ደጋፊዎች በቃ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ እኔ እንድኖር አልፈቀዱም፤ አልፈለጉም። በኋላ ሕዝቡ ውውስጥ አስገብተውበቃ ለኔ ምንም ነፃነት ስላልሰጡኝ መለየቱን ፈለኩኝ።» ከትናንት በስትያ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና በ17 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

Fußball | Africa Cup 2017 | Gabun vs Guniea Bissau
ምስል Getty Images/AFP/G. Bouys

የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ የተሰለፈበት የጋቦን ቡድን እና ጊኒ ቢሳዎ ከወዲሁ መሰናበታቸውን አውቀዋል። አንድ ነጥብ ይዛ የምትንገታገተው አልጀሪያን ዛሬ የምትገጥመው ሴኔጋል ሁለት ጨዋታዎችን አከናውና ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ ከምድቡ አንደኛ ሆናለች። በተመሳሳይ ሰአት ተመሳሳይ አንድ ነጥብ ብቻ ያላት ዚምባብዌ 3 ነጥብ ካላት ቱኒዝያ ጋር ትጋጠማለች። 

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትውልደ ኤርትራዊው ስዊድናዊ የ17 ዓመት አጥቂን ዛሬ በ10 ሚሊዮን ዩሮ ከስዊድኑ AIK ቡድን ማስፈረሙን ገልጧል። አሌክሳንደር ይሳቅ ከሁለት ሳምንት ግድም በፊት ስዊድን ስሎቫኪያን 6 ለ0 ባሸነፈችበት ግጥሚያ ግብ አስቆጥሯል። አሌክሳንደር ስዊድን በስቶኮልም ከተማ አጎራባች ከኤርትራውያን ቤተሰቦች ነው የተወለደው። ብዙዎች አሌክሳንደር ይሳቅን ቀጣዩ ዝላታን ኢብራሒሞቪች ሲሉ ያደንቁታል። የቦሩስያ ዶርትሙንድ አጥቂ ፒየር ኤመሪክ አውባመያንግ ቡድኑን የዘንድሮ ውድድር እንዳለቀ ሊተው እንደሚችል ተገልጧል።   

Fußball Alexander Isak Borussia Dortmund
ምስል picture-alliance/dpa/BVB/A. Simoes/Borussia Dortmund

በነገው ዕለት ቶጎ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ትጫወታለች።  ቶጎ ባለፈው ዐርብ ከሞሮኮ ጋር ባደረገችው ግጥሚያ 3 ለ1 በመረታቷ የተበሳጩ የቶጎ ደጋፊዎች የግብ ጠባቂውን መኖሪያ ቤት አጥቅተዋል። የ38 ዓመቱ የቶጎ ግብ ጠባቂ ኮሲ አጋሳ በወሳኙ ግጥሚያ 3 ግብ እንዴት ይገባበታል በሚል ነው ደጋፊዎች በመዲናዪቱ ሎሜ የሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ላይ ጥቃት ያደረሱት። «ፍርሃት» እንዳደረበት የገለጠው የቶጎ ግብ ጠባቂ ኮሲ አጋሳ በወሳኙ የነገው ግጥሚያ ወደሜዳ የሚገባው በልበ-ሙሉነት  ባለመሆኑ የቡድኑ የማሸነፍ ጉዳይ የበለጠ አጠራጣሪ ሆኗል። ሆኖም በዶይቸ ቬለ የፈረንሳይ ክፍል ባልደረባ ጋዜጠኛ ኮሲቪ ቲያሱ ግን በሀገሩ በቶጉ ቡድን ተስፋ አልቆረጠም።

«የነገው ጨዋታ ለቶጎም ሆነ ለኮንጎ ከባድ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የሚጫወቱ ወጣት ተጨዋቾች አሏቸው። ምንም እንኳን ቶጎ ከሞሮኮ ጋር ባደረገችው ያለፈው ጨዋታ 3 ለ1 ብትሸነፍም  ቡድኑ ቁርጠኛ ነው። ደግሞ ገና ከመነሻው ቶጎዎች እሲህ የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ውስጥ ይገባሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ማጣሪያውን ማለፋቸው እንኳን ብዙዎችን ያስደመመ ነበር።»

ጋዜጠኛ ኮሲቪ በማጣሪያው ወቅት ቶጎ በውድድሩ መኖሯ እንኳን ሳይታወቅ በስተመጨረሻ ድንቅ ጨዋታ በማድረግ ማጣሪያውን ማለፏን አድንቋል። አሁንም ይህ በነገው ዕለት ይደገማል ሲል ለሀገሩ ተስፋ ሰንቋል። «ምንም ድጋፌ ለሀገሬ ቢሆንም ማን እንደሚያሸንፍ ግን መገመት ይከብደኛል»ም ብሏል።

Afrika Cup 2017 Guinea-Bissau gegen Kamerun
ምስል Getty Images/G.Bouys

ሌላኛው የፈረንሳይ ክፍል ባልደረባ ጋዜጠኛ ቦብ ባሪ የትናንትናውን ካሜሩን ከጋቦን ያደረገችውን ጨዋታ ተከታትሏል። ጋቦኖች ወደ ሜዳው የገቡት ጠባብ በሆነ የማለፍ ዕድል ነበር። ጋቦን ካሜሩንን ካላሸነፈች በቀር በውድድሩ የመቆየት ዕድሏ እንደሚያከትም የታወቀ ነበር። እናም ጋቦኖች በፈጣን የማጥቃት ስልት ድንቅ ጨዋታ ቢያከናውኑም ካሜሮኖች ላይ ግን የተመኙትን አንድም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በዛው መጠን ካሜሮኖችም ጠንካራ ሆነው ታይተዋል። ጋዜጠኛ ቦብ ባሪም የካሜሮኖች ኃያልነት አስደምሞታል።

«ካሜሮኖችም ሲበዛ ድንቅ ሆነው ነው ያገኘኋቸው። በሚገባ ሜዳውን ተጠቅመውበታል። የተከላካይ መስመራቸውም እጅግ ጠንካራ ነበር። ግብ ለማግባት በተደጋጋሚ ሞክረዋል። ካሜሮኖች አስተማማኝ ግብ ጠባቂ ስላላቸው ዕድለኞች ናቸው። በርካታ ኳሶችን ግብ ከመሆን ታድጓል። ካሜሮኖች እንዲያልፉ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።  ጨዋታውልክ የዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ይመስል ነበር፤ በተለይ ለጋቦኖች።»

እንዲያም ሆኖ ግን ጋቦኖች ግብ ማስቆጠር ባለመቻላቸው በእሁዱ ጨዋታ በጊዜ ከአፍሪቃ ዋንጫ ተሰናብተዋል። የጋቦኑ አጥቂ ፒየር ኤመሪክ አውባመያንግ ቡድኑ በጊዜ በመሰናበቱ ቢበሳጭም በጊዜ ግን ለጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ይደርሳል ማለት ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በትዊተር ገጹ በጉጉት የሚጠብቀው ፒየር ኤመሪክ አውባመያንግን «አይዞህ አትበሳጭ» ብሎታል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ቬርደር ብሬመንን 2 ለ1 ቢረታም፤ በጀርመን ቡንደስሊጋ በዘንድሮ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመዋዠቅ ሁኔታ ታይቶበታል። ዶርትሙንድ እስካሁንም በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ነው። 

Africa Cup 2017 Gabun vs Burkina Faso
ምስል Getty Images/AFP/G. Bouys

አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 3 ለ0 አሰናብቶ ቅዳሜ ዕለት በሰበሰበው 3 ነጥብ አሁንም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲግ 39 ነጥብ አለው። ከመሪው ባየር ሙይንሽን በ3 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይገኛል። አውስቡርግን ከትናንት በስትያ 2 ለባዶ ያሸነፈው ሆፈንሀይም በ31 ነጥብ ሦስተኛ ነው።   ትናት ባየር ሌቨርኩሰን ሔርታ ቤርሊንን 3 ለ1 ቢረታም በ24 ነጥቡ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከማይንትስ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቶ ነጥብ የተጋራው ኮሎኝ በ26 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ይዟል። ማይንትስ 21 ነጥብ ይዞ 11ኛ ደረጃ ላይ ይዋትታል። ኢንግሎሽታድት እና ዳርምሽታድት አምና ወደመጡበት ለመመለስ ወራጅ ቃጣናው ላይ ይንገታገታሉ።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት በርንሌይን 2 ለ1 የረታው የአርሰናል ቡድን  አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ይቅርታ ጠየቁ። አርሰን ቬንገር ትናንት ከሜዳ ሲሰናበቱ አራተኛው ዳኛን ገፍትረው ነበር። የ67 አመቱ አሰልጣኝ ትናንት ቡድናቸው ባለቀ ሰአት ግብ ተቆጥሮበት በጭማሪው ሰአት ነበር ከሜዳ የተሰናበቱት። ምናልባትም ተጨማሪ ቅጣት ሊጠብቃቸው እንደሚችል ተገልጧል።

ትናንት ሁል ሲቲን 2 ለ0 ድል ያደረገው መሪው ቸልሲ በ55 ነጥብ እየገሰገሰ ነው። አርሰናል በ47 ይከተላል። ቶትንሀም 46 አለው ሊቨርፑልን አስከትሏል። አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል በተደጋጋሚ አቻ በመውጣት ነጥብ በመጣሉ በ45 ነጥብ ወደ አራተኛ ደረጃ ላይ ለመውረድ ተገዷል። ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በ43 እና በ41 ነጥብ 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ