1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት መጋቢት 5 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.

ሰኞ፣ መጋቢት 5 2008

አርሰናል በፕሬሚየር ሊጉ 14ኛ ደረጃ ላይ በሚገኝ ቡድን ተሸንፎ ከእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ተሰናብቷል። ቅዱስ ጊዮርጎስ ባሕር ዳር ውስጥ አቻ ወጥቷል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ውድርድር 2 ሰዎች በልብ ድካም ተዝለፍልፈው አንደኛው ሕይወታቸው አልፏል። የሜዳ ቴኒስ ዕውቁ ራፋኤል ናድል የፈረንሳይ የቀድሞ የስፖርት ሚንስትርን ለመክሰስ ዝቷል።

https://p.dw.com/p/1ID2p
Deutschland Europa League, Borussia Dortmund - Tottenham Hotspur
ምስል Reuters/W. Rattay

የስፖርት መጋቢት 5 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.

የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ሩብ ፍጻሜ የሣምንቱ መጨረሻ ውድድር ልብ አንጠልጥሎ ተጠናቋል። በእርግጥ ማንቸስተር ዩናይትድ ከዌስት ሐም ዩናይትድ ጋር አንድ እኩል አቻ በመውጣቱ በድጋሚ መጫወቱ እንዳለ ማለት ነው። ኤቨርተን፤ ክሪስታል ፓላስ እና ዋትፎርድ ለግማሽ ፍጻሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። የአርሰናሉ አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር ግን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

ማንቸስተር ዩናይትድ፤ ቸልሲ እና ሊቨርፑል የቀድሞ ግስጋሴያቸው በተገታበት፤ ቶትንሐም እና ማንቸስተር ሲቲም የመሪነቱን ቦታ ለአዲስ መጤው በለቀቁበት ሁኔታ አርሰናል አንድም የፕሬሚየር ሊጉን አለያም የኤፍ ኤ ካፑን ወይንም ደግሙ የሁለቱንም ዋንጫዎች የማንሳት እድል ያለው ይመስል ነበር። ከመምሰል ብቻ ግን አላለፈም። አርሰናሎች በሜዳቸው ያከናወኗቸውን ሦስት ጨዋታዎች በሽንፈት ለማጠናቀቅ ተገደዋል። 58 ሺህ ግድም ተመልካቾች በታደሙበት የኢሚሬት ስታዲየም መድፈኞቹ አርሰናሎች የ2 ለ1 ሽንፈት የቀመሱት በዋትፎርድ ነው።

ኦዲዮን ኢግሎ በ50ኛው እንዲሁም አድሌን ጓዲዮራ በ63ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች አርሰናሎች ሲመሩ ቆይተው፤ መደበኛው ጨዋታ ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀረው በባዶ ከመሸነፍ ጉድ የወጡት ዳኒ ዌልቤክ ከመረብ ባሳረፋት ግብ ነው። አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ሽንፈት ኅልውናቸው አደጋ ላይ የወደቀ ይመስላል። እሳቸው ግን ያን የተቀበሉት አይመስልም። የተከላካይ ጥፋቶች እና የግብ ዕድሎች መምከናቸው ለሽንፈታቸው ሰበብ እንደሆኑ ገልጠዋል።


ሌላኛው የኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታ ቸልሲ ከኤቨርተን ጋር ያከናወነው ነው። ቸልሲዎች ለረዥም ጊዜያት ተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠውት የነበረው የቀድሞ አጥቂያቸው ሮሜሉ ሉካኩን ለሌላ ቡድን በመልቀቃቸው ሊጸጸቱ ይገባል። ቤልጂጋዊው አጥቂ ስታምፎርድ ብሪጅ ከመጣበት እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ የመጀመሪያ የጨዋታ ዘመኑን ያሳለፈው የተቀያሪ ወንበር እያሞቀ ነበር። ቋሚ ቡድን እስኪያገኝ ድረስም አርሰናል ሮሜሉ ሉካኩን በተደጋጋሚ በውሰት ለሌላ ቡድን ልኮታል። ቅዳሜ እለት ግን እንዲያ በአግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ በእልህ ሲብሰከሰክ የከረመው ሮሜሉ ሉካኩ በ77 እና 82ኛው ደቂቃዎች ላይ ተከታታይ ግቦችን ቸቀድሞ ቡድኑ ቸልሲ ላይ በማስቆጠር ቁጭቱን የተወጣ ይመስላል።

እናም 10 ቁጥሩ ቤልጂጋዊ አጥቂ የመጀመሪያውን ግብ አራት ተጨዋቾችን ለብቻው አልፎ ካስቆጠረ በኋላ በደስታ እንባ ተውጦ መሬቱ ላይ በግንባሩ ተደፍቶ ታይቷል። ሮሜሉ ሉካኩ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ አክርሮ የመታት ኳስ በግብ ጠባቂው እግሮች ስር አልፋ መረቡ ላይ በማረፍ ሁለተኛ ግብ ኾናለች።

በቅዳሜው ጨዋታ ዲዬጎ ኮስታ ከጋሬት ባሪ ጋር ግብግብ በመፍጠሩ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል። ቆየት ብሎም ዲዬጎ ኮስታን ከሜዳ እንዲወጣ ያስደረገው ጋሬት ባሪ በተመሳሳይ ሁለት ቢጫ አይቶ ከሜዳ ተሰናብቷል። ውጤቱ ግን አልተቀየረም። ኤቨርተን 2 ቸልሲ ዜሮ።

በፕሬሚየር ሊጉ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚንገታገተው ክሪስታል ፓላስ ቅዳሜ እለት ሪዲንግን 2 ለባዶ ረትቷል። ክሪስታል ፓላስ በኤፍ ኤ ካፕ ውጤቱ ለግማሽ ፍፃሜ ሲደርስ፤ በፕሬሚየር ሊጉ ግን ከሞት ሽረት ምድብ በስምንት ነጥብ ብቻ ርቆ ይገኛል። እንግዲህ የፊታችን ቅዳሜ ከፕሬሚየር ሊጉ መሪ ላይሰስተር ሲቲ ጋር ሲገናኝ የኤፍ ኤ ካፕ ድል
ያነነቃቃው ሞራሉ ይረዳው እንደሆነ የሚታይ ነው።

ማንቸስተር ዩናይትድ ከዌስት ሐም ዩናይትድ ጋር ባደረገው የትናንቱ የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ 68ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚዋን ግብ ለዌስት ሐም ያስቆጠረው ዲምትሪ ፓዬ ነው። የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ሉዊ ቫን ጋል ፈረንሳዊውን ወጣት አንቶኒ ማርሺያልን ሊያመሰግኑ ይገባል። በ83ኛው ደቂቃ ላይ ቡድናቸውን አቻ አድርጎ ከኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ከመሰናበት ታድጓል።

ወደ ፕሬሚየር ሊግ፤ ቡንደስሊጋ እና ላሊጋ ጨዋታዎች ቅኝት ከማለፋችን በፊት የአፍሪቃ የእግር ኳስ ቡድኖች የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎችን እንመልከት። ቅዱስ ጊዮርጎስ ትናንት ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ባከናወነው የመጀመሪያ ዙር ፍልሚያ ከኮንጎ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ቱ ፕዊሳ ማዜምቤ ጋር አቻ ወጥቷል። ቱ ፕዊሳ ማዜምቤ ማለትም ኃያሉ ማዜምቤ በጉዳት የተነሳ አማካዩ ራይንፎርድ ካባላን ሳይዝ ወደ ሜዳው ቢገባም ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ችሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ 11ኛው ደቂቃ ላይ ለአስተናጋጁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው በኃይሉ አሰፋ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲመራ ቆይቶ በመጀመሪያው አጋማሽ የባከነ ሰአት ጭማሪ ላይ ዳኒኤል ኒ አጄ ከመረብ ባሳረፋት ኳስ ኃያሉ ማዜምቤ ለእረፍት የወጣው በአቻነት ነበር። ከእረፍት መልስ በደቂቃ ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በራሱ ላይ በማስቆጠሩ መሪነቱ ለጊዜው የእንግዳው ቡድን ኾነ። በ59ኛው ደቂቃ ላይ ግን አዳነ ግርማ አቻ የምታደርገውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። በዚህም ጨዋታው 2 ለ2 ተጠናቋል።

ትናት የባሕር ዳሩን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪቃ ከተሞች ሰባት ግጥሚያዎች ተኪያሂደዋል። የግብጹ ዛማሌክ ወደ ካሜሩን አቅንቶ ኡኒዮን ዱዋላን 1 ለ0 በማሸነፍ 3 ነጥብ ይዞ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ቅዳሜ እለት ደግሞ ዘጠኝ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በአጠቃላይ የመጀመሪያ ውድርድራቸውን ያደሩግት 32 ቡድኖች ናቸው። የመልስ ጨወታዎች ከፊታችን ዐርብ እስከ እሁድ ድረስ ይከናወናሉ። ቅዱስ ጊዮርጎስ በፈረንሣዊው አሠልጣኝ ሑበርት ቬሉድ ከሚመራው ቱ ፕዊሳ ማዜምቤ ጋር የመልስ ጨዋታውን ለማከናወን በሚቀጥለው ሣምንት ወደ ሉቡምባሺ፤ ኮንጎ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ያቀናል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከማይንትስ ጋር ባደረገው ጨዋታ አሳዛኝ ነገር ተከስቷል። ከሰማንያ ሺህ በላይ ታዳሚዎች በተገኙበት ስታዲየም የነበሩ ሁለት ሰዎች የልብ ድካም ይዟቸው ሲዝለፈለፉ፤ አንደኛው ሕይወታቸው አልፏል። የ69 ዓመት ሰው ናቸው። እግር ኳስ ተጨዋቾቹ ግን ከደጋፊዎች መካከል በጨዋታው ወቅት አሳዛን ነገር ስለመከሰቱ አንዳችም የሚያውቁት ነገር አልነበረም።

«ሜዳ ላይ ምንም ነገር የምናውቀው ነገር አልነበረም። የሁለተኛው አጋማሽ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስታዲየሙ እንዲያ ረጭ ማለቱ ገርሞን ነበር። ከዳኛው ጋር ከአንዴም ሁለቴ ተገናኝተን ምንድን ነው የሆነው ብለው ጠይቀውኝ ነበር። <እንጃ፤ ምንም የማቀው ነገር የለም> ነበር ያልኳቸው። ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን የኳስ አስተዳደሮች ወደ እኛ መጥተው በጨዋታው ወቅት አንድ ሰው ላይ መጥፎ ነገር እንደተከሰተ ነገሩን። እጅግ በጣም ያሳዝናል። ጨዋታውም ከጀርባ ደብዝዟል። ውጤቱም ሁለተኛ ነገር ነው።»

ዶርትሙንድ ትናንት ማይንትስን 2 ለባዶ ነው ያሸነፈው። የደረጃ ሠንጠረዥ መሪው ባየር ሙይንሽን ቬርደር ብሬመንን 5 ለ0 አንኮታኩቶዋል። ቲያጎ የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሯል። ባየር ሙይንሽን በ66 ነጥብ እየመራ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአምስት ዝቅ ብሎ ይገኛል። ሔርታ 45 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ነው። 42 ነጥብ ያለው አይንትራኅት ፍራንክፉርት የሞት ሽረት ቃጣና ውስጥ ነው። ከሱ በታች ሆፈንሃይም እና ሐኖቨር በ24 እና 17 ነጥብ 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 30ኛ ጨዋታውን ትናንት ያደረገው ቶትንሀም አስቶን ቪላን 2 ለ0 በማሸነፍ በ58 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃውን አስጠብቋል። ሊቨርፑል እና ቸልሲ ትናንት እንዲሁም አርሰናል እና ዌስት ብሮሚች ቅዳሜ እለት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ የተነሳ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ዛሬ መሪው ላይሰስተር ሲቲ ከኒውካስል ጋር ይጋጠማል። 29 ጨዋታዎችን ያከናወነው ላይሰስተር ሲቲ በ60 ነጥብ መሪነቱን አስጠብቋል። ኒውካስል በ28 ጨዋታዎች 24 ነጥብ ይዞ 19ኛ ወራጅ ቃጣና ላይ ይገኛል።

የሜዳ ቴኒስ የዓለም ምርጡ ራፋኤል ናድል
የሜዳ ቴኒስ የዓለም ምርጡ ራፋኤል ናድልምስል Getty Images/M. Dodge
የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋቾች ሐዘናቸውን ሲገልጡ
የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋቾች ሐዘናቸውን ሲገልጡምስል Reuters/I. Fassbender
የቤልጂጉ አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩ
የቤልጂጉ አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩምስል Reuters
Fußball Bundesliga 26. Spieltag Hannover 96 - 1. FC Köln
ምስል picture-alliance/Citypress24/Hay

በስፔን ላሊጋ ዛሬ ግራናዳ እና ኢስፓኞላ ይጋጠማሉ። ትናንት ሪያል ማድሪድ ላፓልማን 2 ለ1 እንዲሁም ሴቪላ ቪላሪያልን 4ለ2 ድል አድርገዋል። አትሌቲኮ ቢልባዎ ቤቲስን 3 ለ1፤ ወራጅ ቃጣናው 20ኛ ላይ የተዘረጋው ሌቫንቴ ቫሌንሺያን 1 ለባዶ ማሸነፍ ተሳክቶለታል። ባርሴሎና በ75 ነጥብ ይመራል። አትሌቲኮ ማድሪድ 67 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ነው። ሪያል ማድሪድ 63 ነጥብ አለው ፤ ሦስተኛ ነው።

የሜዳ ቴኒስ

ኖቫክ ጄኮቪች፤ ራፋኤል ናዳል እና በሴቶች ሴሬና ዊሊያምስ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል። ኖቫክ ጄኮቪች6-1 6-2 ያሸነፈው አሜሪካዊው ቢጆርን ፍራታንጌሎን ነው። ራፋኤል ናድል ጊል ሙይለርን 6-2 6-4.አሸንፎታል። ሴሬና ዊሊያምስ በሦስት ዙር 7-6 (7-2) 6-0 ዩሊያ ፑቲንስቴቫን ድል አድራጋለች።

ራፋኤል ናድል ለሰባት ወራት ከውድድር ርቆ የነበረው በኃይል ሰጪ መድኃኒት ማለትም ዶፒንግ ምክንያት ነው ሲሉ የተቹትን የፈረንሣይ መንግሥት የቀድሞ የጤና እና የስፖርት ሚንሥትር እንደሚከስ ዝቷል። የፈረንሣይ መንግሥት ሚንሥትሯ ሮዜሊን ባቼሉም ኾኑ ማንኛውም ሰው እንዲህ ያለ ነገር ቢናገረኝ እከሳለሁ ሲል አስጠንቅቋል። «ይኽ የመጨረሻው ነው። ምክንያቱም ሴትዮዋን እከሳቸዋለሁ። በዚህ ጉዳይ በቅቶኛል። ባለፉት ጊዜያት ዝም ብዬ ነበር። ከእንግዲህ በቃ» ሲል ማምረሩን ገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ