1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መጋቢት 11 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2009

ኒውዮርክ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር በአንደኛነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያዊው አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ በሪዮ ኦሎምፒክ ያሳየውን የመንግሥት ተቃውሞ በኒውዮርክም ደግሞታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእስካሁኑ ውድድር በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ የሆነው ሊቨርፑል ትናንት ዳግም ነጥብ ጥሏል።

https://p.dw.com/p/2ZaCx
Deutschland Borussia Mönchengladbach v Bayern München
ምስል Reuters/T. Schmuelgen

ስፖርት መጋቢት 11፤ 2009

ኒውዮርክ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ በአንደኛነት አጠናቋል። ፈይሳ በሪዮ ኦሎምፒክ ሁለተኛ በወጣበት ወቅት እጆቹን ከፍ አድርጎ በማመሳቀል ያሳየውን የመንግሥት ተቃውሞ በኒውዮርኩ ውድድር ላይም ደግሞታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእስካሁኑ ውድድር በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ የሆነው ሊቨርፑል ትናንት ዳግም ነጥብ ጥሏል። ተጋጣሚው ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ ቢጥልም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቶትንሀም የሚበለጠው በሁለት ነጥብ ብቻ ነው። መሪው ቸልሲ  ከግስጋሴው የሚገታው አልተገኘም። በ10 ነጥብ ርቀት ከበላይ ተኮፍሷል። ባየርን ሙይንሽን ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር ባደረገው ጨዋታ ፍራንክ ሪበሪ እና አርየን ሮበን ከሜዳ ተቀይረው ሲወጡ ብስጭታቸውን መደበቅ አልታየም። በተለይ የአርየን ሮበን ድርጊት የልጅ አይነት ነው ተብሎ ተተችቷል። 

ትናንት በኒውዮርክ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ በአንደኛነት ያሸነፈበት የ1 ሰአት ከ4 ሰከንድ ጊዜ በአምስት ዓመት ውስጥ ፈጣኑ ተብሎ ተመዝግቧል። በሪዮ ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ፈይሳ በትናንቱ ውድድር ወቅት እንደ ኦሎምፒኩ ሁሉ ሁለት እጆቹን ከፍ አድርጎ በማመሳቀል መንግሥት ላይ ተቃውሞውን አሳይቷል።  አትሌት ፈይሳን በ4 ሰከንድ ልዩነት ተከትሎ በመግባት ሁለተኛ የወጣው የብሪታንያው አትሌት ካሉም ሀውኪንስ ነው። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ተሾመ መኮንን  1 ሰአት ከ28 ሰከንድ ሮጦ በማጠናቀቅ ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። በሴቶች ፉክክር አንደኛ የወጣችው አሜሪካዊቷ ሞሊ ሀድል ናት። ከሴንትራል ፓርክ እስከታችኛው ማንሀተን ድረስ በተዘረጋው የሩጫ ርቀት 1 ሰአት ከ8 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ ጊዜ በመሮጥ ነው ለድል የበቃችው። 

Brasilien Olympische Spiele Rio 2016 21 08 - Marathon Feyisa Lilesa
ምስል Getty Images/AFP/O. Morin

አዲስ አበባ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተከናወነው የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በምኅጻሩ ካፍ የከፍተኛ አመራር ጉባኤ ወቅት ከፕሬዚዳንት ምርጫ ባሻገር የዲስፕሊን ጉዳይም ታይቷል። የቀድሞው የካፍ ፕሬዚዳንትን አጥብቀው ይተቹ እንደነበር የተነገረላቸው የዚምባብዌው እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ፊሊፕ ሺያንጋዋ የዲስፕሊን ጉዳይ ሒደት እንዲቀጥል ውሳኔው የተላለፈው ከምርጫው ሁለት ቀን በፊት ነበር። የክሱ ጭብጥ ምን እንደሆነ በግልጽ ባይነገርም ፊሊፕ ሺያንጋዋ ኢሳ ሃያቱን በመዝለፋቸው ነው የተከሰሱት ሲሉ አንዳንድ የዜና አውታሮች ዘግበዋል። የቀድሞው የካፍ ፕሬዚዳንትን ዘልፈዋል ተብለው የተተቹት ግለሰብ በአዲሱ አመራር ቦታ አግኝተዋል። በጉባኤው ተገኝቶ የነበረው የሶከር ኢትዮጵያ ዳት ኔት መራኄ ኤዲተር ዖምና ታደለ ክሱ ከመነሻው መሰረት የሌለው ነው ይላል። 

ትናንት በተከናወኑ የፕሬሚር ሊግ ጨዋታዎች ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ገጥሞ አንድ እኩል ተለያይቷል። 57 ነጥብ ይዞ ሊቨርፑልን በአንድ ነጥብ የሚበልጠው ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ሊቨርፑል ምንም እንኳን በርካታ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ከመሪው ቸልሲ ቢበልጥም በ13 ነጥብ ርቀት ተበልጦ ግን አራተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። 

በ69 ነጥብ በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲም ሆነ በ10 ነጥብ ርቀት የሚከተለው ቶትንሀም ቀሪ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል። ቶትንሀም ትናንት ሳውዝ ሐምፕተንን 2 ለ1 ሲረታ፤ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ዩናይትድ  ሚድልስቦሮውን 3 ለ1 ሸንቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ካሸነፈ ከሊቨርፑል በልጦ አራተኛ ደረጃን ይረከባል። ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝ ግን የማንቸስተር ሲቲ መሸነፍን የግድ መጠበቅ አለበት። 

ሁል ሲቲ ሚድልስቦሮው  እና ሠንደርላንድ ከ18ኛ እስከ መጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። እያንዳንዳቸው የሁለት ነጥብ አላቸው። 20 ነጥብ ይዞ የደረጃው ጠርዝ ላይ የሰፈረው ሠንደርላንድ ነው። 

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ትናንት በሜዳው መሪው ባየር ሙይንሽንን አስተናግዶ አንድ  ለባዶ በሆነ ጠባብ ልዩነት ተሸንፏል። በ23ኛው ደቂቃ ላይ ሮበን ወደ ግብ ሞክሮ የግራ አግዳሚው የመለሰበት ኳስ ለባየር ሙይንሽን በጥሩ አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው። ከአግዳሚው የተመለሰችውን ኳስ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ተወርውሮ በግንባር ቢመታም ግብ ጠባቂው በድንቅ ኹኔታ ተወርውሮ ግብ ከመሆን አትርፏታል። 

Deutschland Borussia Mönchengladbach v Bayern Muenchen - Bundesliga
ምስል Reuters/T. Schmuelgen

63ኛው ደቂቃ ላይ ቲያጎ ከርቀት ያሻማትን ኳስ ቶማስ ሙይለር በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ከመረብ አሳርፏታል። በትናንቱ ጨዋታ ፍራንክ ሪበሪ ተቀይሮ ሲወጣ ብዙም ደስተኛ አልነበረም። ሆኖም ጭንቅላቱን እያሻሸ ያጽናናው አርየን ሮበን በተራው እሱም ተቀይሮ ሲወጣ ግን ንዴቱን ፈጽሞ መቆጣጠር አልቻለም። አሰልጣኝ አንቼሎቲ ሊጨብጡት እጃቸውን ቢዘረጉም አመናጭቆ መሬቱን በእግሩ እየደቃ ከሜዳ ወጥቷል።

አሰልጣኙ ግን በሮበን ብዙም የተከፉ አይመስሉም፦ «እንደዛ ስላደረገ ምንም ችግር የለብኝም፤  አይደንቀኝም» ብለዋል። ሮበን ከሜዳ ሲወጣ የልጅ ጠባይ ቢያሳይም አሰልጣኙ ግን፦ «መበሳጨቱ ግልጽ ነው፤ እኔም ተጫዋች ሳለሁ እንደዛ ነበርኩ» ሲሉ አቃለውታል።  ትናንት በተከናወነ ሌላ ጨዋታ ሻልከ ማይንትስን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ አሸንፏል።

ከቡንደስሊጋ አጠቃላይ 306 ጨዋታዎች እስካሁን በተደረጉ 225 ግጥሚያዎች 610 ግቦች ተቆጥረዋል። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ 23 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ቀዳሚ ነው። የኮሎኙ አንቶኒ ሞዴስቴ በ22 ግቦች ይከተላል። የባየር ሙይንሽኑ ግብ አዳኝ  ሮበርት ሌቫንዶብስኪ በ21 ግቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አዜብ ታደሰ