1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስካይፕ በኢትዮጵያ ተከልክሏል?

ዓርብ፣ ሰኔ 22 2004

የወጣቶች መድረክ። በኢንተርኔት የስልክ እና የቪዲዮ ንግግር መገናኛዎች ማለትም ስካይፕ፣ ያሁ መሴንጀር እና በመሳሰሉት መጠቀም በወንጀል ያስቀጣል የሚል አዋጅ ፀድቋል ሲሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትችት በማቅረብ ላይ ናቸው። መንግስት በበኩሉ አዋጁ እነዚህን አይከለክልም ሲል ማስተባበያ ሰጥቷል።

https://p.dw.com/p/15OKm
የስካይፕ ካሜራምስል Alterfalter - Fotolia.com

በእርግጥ በኢትዮጵያ ስካይፕን ጨምሮ የኢንተርኔት የድምፅና ምስል መገናኛዎች ተከልክለዋል? የቴሌኮም ማጭበርበር ሕግ መተላለፍ በሚል ለኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 16 ቀን 2004 ዓ ም እንደቀረበ የተነገረለት አዋጅ ሰሞኑን በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኗል። ሕጉ እንደ ስካይፕ እና ያሁ መሴንጀር ያሉትን በኢንተርኔት የስልክ እና የቪዲዮ ንግግር መገናኛዎች መጠቀምን ይከለክላል ሲሉ በርካቶች ስጋታቸውን እየገለፁ ነው። ከመከልከልም ባሻገር እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ያስከትላል ሲሉም ያክሉበታል። መንግስት በበኩሉ የቴሌኮም ማጭበርበር ሕግ መተላለፍን የተመለከተው አዋጅ ስካይፕ እና መሰል መገናኛዎችን አይከለክልም ሲል እየተሰማ ነው። ዝርዝር መረጃዎችን ይዘናል። ቆይታችሁ ከእኛ ጋር ይሁን።

ሙዚቃ፥

ስካይፕ በኢንተርኔት የትኛውም ዓለም የሚገኝ ሰውን እየተያዩ ለማናገር የሚያስችል ውድ ያልሆነ የመገናኛ ዘርፍ ነው። አውሮጳ እና አሜሪካ የኢንተርኔት መስመሩ ያለው ማንኛውም ሰው ስካይፕንም ሆነ መሰል መገናኛዎችን ለኢንተርኔት መጠነኛ ክፍያ ብቻ በመክፈል መጠቀም ይችላል። ይህ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ተከለከለ መባሉን ተከትሎ ካነጋገርናቸው ወጣቶች መካከል አንዱ አዋጁን አግኝቶ እንዳነበበው ገልፆልናል።

ባል ሚስትና ልጅ በስካይፕ ሲነጋገሩ
ባል ሚስትና ልጅ በስካይፕ ሲነጋገሩምስል Flickr.com

ድምፅ፥

እንደ ስካይፕ እና ያሁ መሴንጀር ያሉትን በኢንተርኔት የስልክ እና የቪዲዮ ንግግር መገናኛዎችን መጠቀም የተባበሩት መንግስታት ከሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች እንደ አንዱ ነው የሚወስዳቸው። ብዙዎች እነዚህ ኢንተርኔትን ከመጠቀም መብት ጋር የሚዛመዱት አገልግሎቶች በአዲሱ አዋጅ ኢትዮጵያ ውስጥ መከልከላቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ይሰማል። የፍትህ ሚንስቴር ዴኤታው አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ስካይፕ እና ተመሳሳይ የመገናኛ ዘርፎች በስፋት እንደሚነገረው በኢትዮጵያ ተከልክለዋል ወይንስ አልተከለከሉም ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ።

ድምፅ፥

ይህ የቴሌኮም ማጭበርበር ሕግ መተላለፍ በሚል የወጣው አዋጅ አሻሚ ሀረጎችን እንዳካተተም ይነገራል። በተለይ በአዋጁ ክፍል 2 አንቀፅ 6 የሰፈረው ሀሳብ በርካቶችን ሳያሳስብ አልቀረም። በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ማንኛውንም የቴሌኮሙኒኬሽን መረብ ወይንም መሳሪያ በመጠቀም በፀረ ሽብር አዋጁ ቁጥር 652/2009 ወይንም በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በወንጀል የሚያስቀጡ ሽብር ነዢ መልዕክቶችን ማሰራጨት ሕግን እንደመተላለፍ ይቆጠራል ይላል። በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ የሰፈረው ሀሳብ ደግሞ በቴሌኮሙኒኬሽን የሚቀርበውን አገልግሎት ለማንኛውም ሌላ የወንጀል ተግባር መጠቀም ሕግ ወጥ ነው ሲል በጥቅሉ ያስቀምጠዋል።

በስካይፕ ሲደውል
በስካይፕ ሲደውልምስል Picture-Alliance/KEYSTONE

ድምፅ፥

አዋጁን የበለጠ አነጋጋሪ ያደረገው በእንግሊዘኛው ምህፃሩ VOIP ወይንም voice over internet protocol የሚባለውን ጉዳይ የሚመለከተው እንደሆነ ብዙዎች ይገልፃሉ። ቮይፕ ከመደበኛው የመስመር ስልክ በተለየ ፈጣን የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ግንኙነትን በመጠቀም ከተለያየ ሰው ጋር በየትኛውም የዓለም ክፍል የድምፅ ጥሪ እና የቪዲዮ ንግግር ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው። ስካይፕ፣ ያሁ መሴንጀር፣ ጎግል ቱልስ፣ ፌስቡክ እና የመሳሰሉት ማኅበራዊ መገናኛዎች ይህን አገልግሎት በነፃ አለያም እጅግ ርካሽ በሆነ የአገልግሎት ክፍያ ይሰጣሉ። ከተጠቃሚው የሚፈለገው ፈጣን ማለትም ብሮድባንድ የኢንተርኔት አገልግሎት እና ኮምፒውተር ወይም ላፕቶፕ አለያም ኢንተርኔት የሚቀበል ዘመናዊ የእጅ ስልክ ብቻ ነው። ከእነዚህ አንዱ ያለው የኢንተርኔት መስመር በመጠቀም ከመላው ዓለም ጋር በቀላሉ መገናኘት ያስችለዋል ማለት ነው። ይህ አገልግሎት ተከልክሎዋል መባሉ ይላሉ አቶ ብርሃኑ፥

ድምፅ፥

የኢንተርኔት አጠቃቀምን አስመልክቶ ከአንድ ዓመት በፊት በተባበሩት መንግስታት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የቀረበ ባለ 22 ገፅ ልዩ ሰነድ ኢንተርኔትን ከሠብዓዊ መብቶች እንደአንዱ ይጠቅሰዋል። ሰነዱ የግል ሚስጥር አጠባበቅ መብት በዓለም አቀፍ የሠብአዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀፅ 12 እና በዓለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት አንቀፅ 17 ላይ የተረጋገጠ እንደሆነ ያትታል። ይህ ሰነድ ኢንተርኔት ለአንድ ሀገር እድገት ቁልፍ አጋዥ ከመሆኑም ባሻገር እውቀትን በቀላሉ ለማግኘትም ይረዳል ሲል ያብራራል።

የስካይፕ አርማ
የስካይፕ አርማምስል picture alliance/empics

ድምፅ ፥

የተባበሩት መንግስታት የሠብአዊ መብቶች ካውንስል ልዩ ሰነድ ሰዎች ራሳቸውን በነፃነት እንዲገልፁ የግል መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል ይላል። ይህ ልዩ ሰነድ ለብሔራዊ ደህንነት ወይንም አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ግለሰቦችን የሚስጥር አጠባበቅ መብት የሚጥሱ መንግስታት ያሳስቡኛል ሲልም አፅንኦት ሰጥቶበታል። የቴሌኮም ማጭበርበር ሕግ መተላለፍ በሚል ለኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ወር በፊት የቀረበውን አዋጅ አስመልክቶ የፍትህ ሚንስቴር ዴኤታው አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ሲገልፁ፥

ድምፅ፥

በኢንተርኔት የስልክ እና የቪዲዮ ንግግር መገናኛዎች ማለትም ስካይፕ፣ ያሁ መሴንጀር እና በመሳሰሉት መጠቀም በወንጀል ያስቀጣል የሚል አዋጅ ኢትዮጵያ አርቅቃለች በሚል የተነሳውን መነጋገሪያ ጉዳይ ተከትለን ወጣቶችን እና የፍትህ ሚንስቴር ባለስልጣንን ያነጋገርንበት ጥንቅር በዚህ ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ