1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስርቆት ፈፃሚ ወጣቶች እና መሠረታዊ ችግሮች

ዓርብ፣ ሰኔ 12 2007

መቼም ሁላችንም ንብረታችንን ተሰርቀን ወይም የተሰረቀ ሰው እናውቃለን። ሰዎች በተለይ ወጣቶች ለምን ይሰርቃሉ? የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በተለይ በተደጋጋሚ ስርቆት ፈፃሚ ወጣቶች ላይ ያተኩራል።

https://p.dw.com/p/1FjMZ
Taschendieb Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa

ስርቆት ፈፃሚ ወጣቶች እና መሠረታዊ ችግሮች

ወጣት በመሆኑ አንተ መባልን የመረጠው ክቡር እንግዳወርቅ ፤ በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የማህበረሰባዊ ጥናት (ሶሲዮሎጂ)ትምህርት ክፍል መምህር ነው። በተለይ በተደጋጋሚ ስርቆት ፈፃሚዎች ላይ ጥናት አካሂዷል። ለዚህም ጥናት ሲል ለሳምንታት ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመጓዝ ፤ ታራሚዎችን በቅርበት በማነጋገር ከነሱ ባገኛቸው መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ ወደ ስርቆት ለመግባት መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው ያላቸውን ዘርዝሯል።

ከነዚህ ምክንያቶች መካከል በስርቆት የተሰማራ ጓደኛ ግፊት ዋና ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ክቡር ካነጋገራቸው ታራሚዎች ለመረዳት ችሏል። ክቡር ከሁለት አመት በፊት ይህን ጥናት ሲያደርግ ሰዎች ለምን ይሰርቃሉ? የሚለው ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ለምን በተደጋጋሚ ስርቆት ይፈፅማሉ የሚለውም ጥያቄ አሳስቦት ነበር።

በክቡር ጥናት የተሳተፉት ወጣቶች በብዛት ተንቀሳቃሽ ስልክ ፣ የኪስ ገንዘብ በመስረቅና ከዚያም አልፎ ቤት ሰብሮ በመግባት ንብረት እስከመውሰድ አይነት ወንጀል የፈፀሙ ሲሆን፤ ከታራሚዎች መካከል ረዥም ጊዜ ቅጣት የተፈረደበት ግን 1 ዓመት ከ 6 ወር እንደነበር ክቡር ይገልፃል።

Symbolbild Einbrecher
ምስል Fotolia/Sergey

ሰዎች ደጋግመው ጥፋት እንዲፈፅሙ መንገድ የፈጠረላቸው ነገር በማረሚያ ቤቱ ያለው የአቅም ድክመት እና የወንጀል ፈፃሚዎቹ ብልጥነት እንደሆነ የማህበረሰባዊ ጥናት ባለሙያው ታዝቧል።የክቡር ጥናት በ30 ታራሚዎች ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ አጠቃላይ የመፍትሄ ሀሳብ ለመስጠት ከባድ እንደሆነ እና ተጨማሪ ጥናት እንደሚያሻ ገልጾልናል። ይሁንና ከማህበረሰቡም ይሁን ከመንግሥት በኩል ሊፈፀሙ የሚችሉ ሀሳቦችን ክቡር ይጠቁማል።

ስርቆት ፈፃሚ ወጣቶች እና መሠረታዊ ችግሮች ላይ ፤እንዲሁም ወጣቶች ለምን በተደጋጋሚ ስርቆት እንደሚፈፅሙ ሙሉ ዝግጅቱን በድምፅ በማድመጥ ከማህበረሰባዊ ጥናት ባለሙያ ክቡር እንግዳወርቅ ጋር የነበረንን ቆይታ መከታተል ይቻላል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ