ስለ አቶ መለስ የጤና ሁኔታ የመንግስት መግለጫ
ዓርብ፣ ሐምሌ 13 2004
በህመም ሳቢያ የዕረፍት ጊዜ እንዲወስዱ ሀኪም እንዳዘዘላቸው የተነገረላቸው የኢትዮጵያጠ/ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ በሌሉበት አገሪቱን የሚያስተዳድራት ማን ነው የሚል ጥያቄ መቅረቡን ፣ የፖለቲካ ተንታኞች በዛሬው ዕለት ገለጡ።
የአቶ መለስ መንግሥት ፣ የጎሣ ፌደራሊዝምን የፖለቲካ አመራር ዘይቤው ቢያደርግም፤ የማዕከላዊው አስተዳደር ጥብቅ ቁጥጥር፤ በገዥው ፓርቲ እጅ ነው ሲል AFP አስታውቋል። በህገ-መንግሥቱ መሠረት፣ ጠ/ሚንስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ ፣ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ናቸው ወክለው መሥራት የሚጠበቅባቸው።
ስለ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ጤንነት ይዞታ በተናፋሽ ወሬ ብዙ የሚባል ቢኖርም፤ ትናንት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፤ የ 57 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አቶ መለስ፤ ጤንነታቸው ተመልሶአል ወይም ተስተካክሏል ሲሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ የመገናኛ ዘዴዎች(Communication )ሚንስትር አቶ በረከት ስምዖን---
«የጤንነታቸው ይዞታ በጣም ጥሩና የተመለሰላቸው ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ፣ ጠ/ሚንስትሩ፣ ባለፉት ዐሠርተ-ዓመታት ፣ በመንግሥት ሥራ ጫና ፣ በተለይ በቅርብ ጊዜያት ፣ --እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ባላቸው ድርሻ ምክንያት፣ --ሀኪሞቻቸው፣ ሥራ አቁመው ዕረፍት ያደርጉ ዘንድ መክረዋቸዋል። ለአናንተ የምነግራችሁ የጤንነታቸው ይዞታ በጠሙን የተመለሰላቸውና በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኙ ነው። ከጥቂት ቀናት ፣ የሥራ መቅረት በኋላ፣ ወደ ጽ/ቤታቸው ተመልሰው የመንግሥት ተግባራቸውን ያካሂዳሉ።»
ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሃመድ