1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለስደተኞች የሚደረገው ክርክር

ማክሰኞ፣ ኅዳር 7 2008

ወደ አውሮጳ በመምጣት ላይ ካሉት ስደተኞች ጋር አሸባሪዎችም ተደባልቀው ሊገቡ ይችላል የሚለው ስጋት በአሁኑ ጊዜ ብዙ ጀርመናውያንን እያሳሰበ ነው።

https://p.dw.com/p/1H7IE
Griechenland Flüchtlingsnot auf Lesbos
ምስል Reuters/A. Konstantinidis

[No title]

ባለፈው ሳምንት በፓሪስ ፈረንሳይ ጥቃት ከጣሉት አሸባሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በጀርመን በኩል አድርገው ወደ ፈረንሳይ ገብተው ይሆን በሚል በወቅቱ በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ውይይቱ ቀጥሎዋል። ይኸው ስጋት በአውሮጳ እስልምና እንዳይስፋፋ እታገላለሁ የሚለው ፔጊዳ የተባለው ቡድን አዳዲስ ደጋፊዎች እንደሚያስገኙለት ተስፋ አድርጓል።

ራሱን እስላማዊ መንግሥት ወይም በምህፃሩ « አይ ኤስ» ብሎ የሚጠራው ቡድን በሚያካሂደው ሽብር ተግባር እና ምናልባት ከአንዱ በስተቀር፣ በስደተኞች መካከል አንዳችም ግንኙነት እንደሌለ እና የጀርመን ፍትሕ ሚንስትር ሀይኮ ማስ አስታውቀዋል።

« ስደተኞቹም በፓሪስ ለተጣለው ጥቃት ተጠያቂ ከሆኑት በሶርያ ካሉት ተመሳሳይ ሰዎች ነው የሚሸሹት። በመሆኑም፣ ካላንዳች ማስረጃ በሁለቱ ወገኖች መካከል ግንኙነት ለመፍጠር መሞከር ኃላፊነት የጎደለው አሰራር ነው። »

Sigmar Gabriel
ምስል Getty Images/A. Berry

የፀጥታ ጥበቃ ጠበብት እንደሚሉት፣ አሸባሪዎች ተቀላቅለው አይገቡም ለማለት በፍፁም አይቻልም። ይሁንና፣ አሸባሪዎች በአደገኛው የባህር ጉዞ ወይም በቦልካን በኩል አድርገው የመግባት ፍላጎታቸው በጣም አናሳ ነው።

Pegida marschiert in Dresden
ምስል Picture-alliance/dpa/A. Burgi

እርግጥ፣ አንዱ አጥፍቶ ጠፊ የሶርያ ፓስፖርት የነበረው እና በግሪክ በኩል አድርጎ አውሮጳ የገባ ስደተኛ መሆኑ ከእጅ አሻራው ለማወቅ መቻሉን ፈረንሳይ አመልክታለች።

ብዙዎች በዚህ ዓይነቱ ዜና ግራ በተጋቡበት ባሁኑ ጊዜ የጀርመን ምክትል መራሔ መንግሥት ዚግማር ጋብርየልን የመሳሰሉ ፖለቲከኞች፣ እንዲሁም፣ በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት የተወከሉት የገዢው እና የተቃዋሚፓርቲዎች እንደራሴዎች ሕዝቡ ስደተኞችን በጠቅላላ እንደ አሸባሪ እንዳይመለከት ከማሳሰብ አልቦዘኑም።

« የፓሪስ ጥቃት ሰለባዎች እና ስደተኞቹን የሚያዛምዳቸው ነገር ሁለቱም የ«አይ ኤስ» ሰለባዎች መሆናቸው ነው። ከሶርያ የሚሰደዱት ብዙዎቹም ከ«አይ ኤስ» ነው የሚሸሹት። ስደተኞቹን በሙሉ ተጠርጣሪ ናቸው ከሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ በሚያደርስ ግራ የተጋባ ፖለቲካዊ ውይይት ስር ማስቀመጥ አይገባም። »

በአውሮጳ እስልምና እንዳይስፋፋ እታገላለሁ የሚለው እና በየሰኞው ምሽት በምሥራቅ ጀርመናዊቷ የድሬዝደን ከተማ ስብሰባ የሚያካሂደው ፔጊዳ የተባለው ቡድን ዓላማ ግን ስደተኞችን ሁሉ እንደ አሸባሪዎች መመልከት ነው። ይህንን የፔጊዳን አካሄድ የተቃዋሚው የአረንጓዴ ፓርቲ በስደተኞች ስም ለራስ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል የሚደረግ አሳፋሪ ስልት ነው በሚል በጥብቅ ነቅፎታል። የባየር ፌዴራዊ ግዛት ገንዘብ ሚንስትር፣ ዘደርም የፓሪሱን ጥቃት ተከትሎ ቁጥጥር የሌለበት ፍልሰት ማብቃት አለበት ሲሉ ያሰሙት አስተያየት ከተለያዩ ፖለቲከኞች ወቀሳ ተፈራርቆበታል። የባየር ጠቅላይ ሚንስትር ሆርስት ዜሆፈርም ሳይቀሩ ስደተኞች እና ሽብርተኝነት ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች መሆኑን ማወቅ ተገቢ እንደሆን አስገንዝበዋል። «

« ሁለቱ የተለያዩ ጉዳዮች መሆናቸውን በሚገባ አለማወቅ በህብረተሰቡ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ይበልጡን ያሰፋዋል። »

ብዙዎቹ ፖለቲከኞች እንደሚያመለክቱት፣ በወቅቱ የሚያስፈልገው ሃገሪቱን አንድ የሚያደርግ ፖለቲካ መከተል ይሆናል።

ቤርንት ግሬስለር/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ