1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሴኔጋል እና የሕገ መንግሥቱ ለውጥ

ሐሙስ፣ መጋቢት 15 2008

የሴኔጋል ፕሬዚደንት ማኪ ሳል ከአምስት ዓመት በላይ በስልጣን እንደማይቆዩ ቃል በመግባታቸው ነበር እጎአ በ2012 ዓም ፕሬዚደንታዊውን ምርጫ ያሸነፉት።

https://p.dw.com/p/1IIPB
Macky Sall Präsident Senegal
ፕሬዚደንት ማኪ ሳልምስል picture alliance/augenklick/Minkoff

[No title]

በሕገ መንግሥቱ ላይ የሀገሪቱን መሪ የስልጣን ዘመን ለመቀነስ እና ሌሎች ማሻሻያዎችን ለማስደረግ ባለፈው እሁድ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ድል አስመዝግበዋል። ሆኖም፣ ሕዝቡ አሁንም ቅር እንደተሰኘባቸው ይገኛል።

የሴኔጋል ዜጎች በመሪዎቻቸው ቅር ሲሰኙ ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከማኪ ሳል በፊት ሀገሪቱን የመሩት አብዱላይ ዋድ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው እጎአ በ2011 ዓም ሊያበቃ ሲቃረብ፣ በአምስት ዓመት ፈንታ ሰባት ዓመት በስልጣን ለመቆየት በማሰብ ባስቸኳይ በሕገ መንግሥቱ ላይ ለውጥ ማስደረጋቸው ይታወሳል። ከዚያም ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ የፕሬዚደንቱን የስልጣን ዘመን በሁለት ቢገድብም፣ ዋድ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በተወዳዳሪነት በመቅረባቸው ሕዝቡን አስቆጥተዋል። ከምርጫው ቀደም ሲል በነበረው ጊዜም በሀገሪቱ የታየው ሁኔታ ሴኔጋልን ወደርስበርስ ጦርነት እንዳያስገባት አስግቶ ነበር። በዚሁ ጊዜ ነበር የተቃዋሚው ቡድን እጩ ማኪ ሳል የርዕሰ ብሔሩን የስልጣን ዘመን በአምስት ዓመት እንደሚገድቡ በገቡት ቃል የመራጩን ልብ መሳባቸውን በወቅቱ ዋነኛ ተቺያቸው የሆነው የራፕ ሙዚቃ ተጫዋች ቲያ የገለጸው።
« ማኪ ሳል የስልጣን ዘመናቸውን እንደሚያሳጥሩ ቃል በመግባታቸው ነበር ከ60% የሚበልጥ መራጭ ሕዝብ ድምፁን የሰጣቸው። ያኔ መላ ዓለምም አድንቋቸዋል። »
እርግጥ ባለፈው እሁድ በተካሄደው ሬፈረንደም፣ በሀገር አስተዳደር ሚንስቴር መግለጫ መሰረት፣ ከሴኔጋል መራጭ ሕዝብ መካከል 63% በሕገ መንግሥቱ ላይ በርካታ፣ በርዕሰ ብሔሩ የስልጣን ዘመን ይቀነስ በተባለበት ሀሳብ ላይ ጭምር ለውጦች እንዲደረጉ መወሰን ችሏል። ይሁንና፣ ለውጡ የፕሬዚደንት ማኪ ሳልን የወቅቱን የስልጣን ዘመን አይመለከትም፣ ሲመረጡ። ለውጡ ከቀጣዩ ምርጫ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን ነው የተነገረው። በዚህም የተነሳ፣ ሬፈረንደሙ ለይስሙላ የተደረገ ነው ሲል «በቃ» የተሰኘው ቡድን አባል የሆነው የራፕ ሙዚቃ ተጫዋቹ ቲያ በቡድኑ ስም ትችት አሰምቶዋል።
« ማኪ ሳል የገቡትን ቃልም አልጠበቁም። የሴኔጋልን ሕዝብ ክደዋል፣ ቃላቸውንም አጥፈዋል። »
ፕሬዚደንቱ የስልጣን ዘመናቸውን አሁኑኑ ከሰባት ወደ አምስት ዓመት ማሳጠር ቢፈልጉም በፕሬዚደንቱ የተሰየሙ አምስት አባላት ያሉት ሕገ መንግሥታዊው ምክር ቤት እንዳከላከላቸው በተደጋጋሚ በመግለጽ ኃላፊነቱን ከራሳቸው ለማውረድ ሞክረዋል፣ ይሁንና፣ የሴኔጋል ሕዝብ ይህንን ምክንያታቸውን አሳማኝ ሆኖ ባለማግኘቱ አልተቀበላቸውም።

በዳካር የሚገኘው የጀርመናውያኑ የኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ አንድሬያ ኮልብም ማኪ ሳል ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው ሕዝባቸውን ቅር እንዳሰኙ ታዝበዋል።
« ብዙው ሕዝብ ፕሬዚደንቱ ሕዝቡን እንዳታለሉ ነው የተሰማው። በስልጣን ለመቆየት አስበው ያደረጉት ስልት ነው ብሎ ነው የሚያምነው። በዚህም የተነሳ ምንም እንኳን በሕገ መንግስቱ ላይ ለውጦች ይደረጉ መባሉ አዎንታዊ ቢሆንም፣ አሉታዊ ስሜት መፍጠሩ አልቀረም። »
ይሁን እንጂ፣ የሴኔጋል መንግሥት በለውጥ ለውጦቹ አማካኝነት መልካም አስተዳደርን ለማስፋፋት ቆርጦ መነሳቱን እንዳሳየ የፕሬዚደንት ማኪ ሳል ፓርቲ ትብብር ለሬፓብሊክነት የተሰኘው ገዢው ፓርቲ ቃል አቀባይ ሴይዱ ጌይ ገልጸዋል።
« ሬፈረንደሙ የሴኔጋልን ዴሞክራሲ፣ በሀገሪቱ ያሉትን ተቋማት እና የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር የታሰበ ነው። »

Senegal Referendum
ምስል picture-alliance/dpa/A. Mbaye
Rap-Sänger THIAT
ቲያምስል DW/D.Köpp

ማድሌን ማየር/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ