1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሴኔጋል ስደትና ፖለቲካ

ሐሙስ፣ የካቲት 15 1999

እንደሚገመተዉ ባለፈዉ የአዉሮጳዉያን አመት ሁለት-ሺሕ ስድስት መቶ ብቻ ሰላሳ-ሺሕ ያሕል ሰዎች የባሕር ማዶዉን እያዩ ባሕር ለመቅዘፍ ሞክረዋል።ስድስት ሺዉ ግን ካለሙት ሳደርሱ፣ ወደነበሩበትም ሳይመለሱ-እንደ ወጡ ቀርተዋል-ነዉ ግምቱ

https://p.dw.com/p/E0hH
ከፕሬዝዳት አብዱላሒ ዋዴ
ከፕሬዝዳት አብዱላሒ ዋዴምስል PA/dpa

የሴኔጋል ሕዝብ በመጪዉ እሁድ ፕሬዝዳንቱን ይመርጣል።ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሐገር ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ወዲሕ የከረረ የፖለቲካ ግጭትና ዉዝግብ አጋጥሟት አያዉቅም።የዕሁዱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም እንደ ከዚሕ ቀደሞቹ ሁሉ በሠላም ይጠናቀቃል ተብሎ ነዉ-የሚጠበቅ። ሴኔጋል ግን በርግጥ ከችግር ተዘፍቃለች። በየዕለቱ በርካታ የሴኔጋል ወጣት ወንዶች ሐገራቸዉን ጥለዉ በባሕር ወደ አዉሮጳ ይሰደዳሉ።ወይም ለመሰደድ ይሞክራሉ።ያን ቱሲንግ ሕይወትን ላደጋ ሥለሚያጋልጠዉ ድርጊትና ምክንያቱ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አሰባስቦታል።

«ለመጀመሪያ ጊዜ ሚያዚያ አንድ ከሐገር ወጣሁ።ቴነሪፍ እስክንደርስ አምስት ቀን ተጓዝን።»

ይላል ንዶንጎ ፋዬ።የሃያ-አምስት አመት ወጣት ነዉ።ሴኔጋል ርዕሠ-ከተማ ዳካር መዳራሻ የምገኝ ያራክሕ የተባለች ትንሽ የአሳ-አጥማጆች መንደር ተወላጅ ነዉ።---ቀጠለ ወጣቱ ቀጣይ ታሪኩን፣-

«ለሁለተኛ ጊዜ የተጓዝ ነዉ-እስከ ሞሮኮ ድረስ ብቻ ነበር።አስራ-ስምንት ቀን ባሕር ላይ ነበርን።በሰወስተኛዉ ጉዟችን እስከ ሞሪታንያ ድረስ ብቻ ነበር የተሳካልን።መጥፎ አየር ነበር ያጋጠመን።ታንኳችንም ተበላሽታብን ነበር።አስራ-አንድ ቀን ባሕር ላይ ቆየን።»

በጎስቋሏ እጁ ጎስቆል-ቆል ያለች ወረቀት ይዟል።ከስጳኝ ባለሥልጣናት የተሰጠዉ ሰነድ ነዉ።ቁጥር3807- የሚል ተፅፎቦታል-ሠነዱ።-የስጳኝ ባለሥልጣናት ቴንርፍ ላይ እየያዙ መልሰዉ ወደ ሴኔጋል ከላኳቸዉ የምዕራብ አፍሪቃዊቱ የባሕር ዳርቻ ሐገር-ዜጎች መካካል ንዶንጎ ፋዬ 3807ኛዉ ነዉ-ማለት ነዉ።
ሙዚቃ

ሴኔጋል ባሁኑ ወቅት በርካታ ዜጎችዋ ጥለዋት እየኮበለሉ ነዉ።በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ከባሕሩ ወዲያ ማዶ የመሻገር እድላቸዉን ለመሞከር ትናንሽ ጀልባዎች እየተሳፈሩ ይቀዝፋሉ።እንደሚገመተዉ ባለፈዉ የአዉሮጳዉያን አመት ሁለት-ሺሕ ስድስት መቶ ብቻ ሰላሳ-ሺሕ ያሕል ሰዎች የባሕር ማዶዉን እያዩ ባሕር ለመቅዘፍ ሞክረዋል።ስድስት ሺዉ ግን ካለሙት ሳደርሱ፣ ወደነበሩበትም ሳይመለሱ-እንደ ወጡ ቀርተዋል-ነዉ ግምቱ።ድምፃዊዉ ዑመር ፔኔ «ታላቅ የክብር-ጥፋት» ይለዋል።ከሴኔጋል ኮከብ አቀንቃኞች አንዱ የሆነዉ ዑመር ፔኔ ጥፋት-ያለዉን ጥፋት ለመከላከል ያዉ እንደ ድምፃዊነቱ እያንጎራጎረ ነዉ።

በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ስጳኝ ለመጓዝ መሞከር-በሕይወት መቀለድ ነዉ-ይላል ድምፃዊዉ።ለችግሩ በሒሳብ የሚያሰላዉ ምክንያትም አለዉ።

«ችግሩ እዚሕ በርካታ ሥራ-የሌላቸዉ ወጣቶች አሉን።በልማዱ የአሳ አስጋሪ ልጅ አሳ አስጋሪ ነዉ-የሚሆን።ግን አንድ አሳ-አስጋሪ በአማካይ ስድስት ልጆች ይኖሩታል።ማለቴ ብዙ ልጆች ይወልዳሉ።ያ ማለት ደግሞ ስድስት አዳዲስ ታንኳዎች መሠራት አለባቸዉ ማለት ነዉ።አስላዉ።ባሁኑ ወቅት ወደ አስራ-አምስት ሺሕ የሚጠጉ ታንኳዎች እና ስልሳ ሺሕ አሳ-አስጋሪዎች አሉ።እነዚሕ ስድስት-መቶ ሺሕ ሕዝብ ይቀልባሉ-ወይም ያስተዳድራሉ።»

የአንድ የሴኔጋል ዕለታዊ ጋዜጣ የምጣኔ-ሐብት አምድ አዘጋጅ የሆነዉ መሐመድ ጉዬ ደግሞ የችግሩን ምክንያት በሥልጣን ላይ ካለዉ ከፕሬዝዳት አብዱላሒ ዋዴ መንግሥት የምጣኔ ሐብት መርሕ ጋር ነዉ የሚያይዘዉ።ጋዜጠኛዉ እንደሚለዉ የዋዴ መንግሥት የአሳ-ሐብትን አጠቃቀም የሚመለከት ሕግና ደንብ የለዉም።መንግሥት ከትናንሹ የሴኔጋል አሳ-አስጋሪዎች ከሚያገኘዉ ገቢ ይልቅ በአለም ከታወቁ ትላልቅ የአሳ-ማዘጋጂያና ማሸጊያ ኩባንዮች የሚያገኘዉ ገቢ ይበልጥበታል።
በዚሕ ምክንያት የሐገሬዉን አሳ-አስጋሪዎች ችግር የሚያቃል እርምጃ አልወሰደም።

በጋዜጠኛዉ እምነት ከአለም በአሳ ሐብቷ የታወቀችዉ ሴጋል አሳዎችዋ በትላልቆቹ ኩባንዮች በገፍ ሲዛቁባት የአሳ-ሐብቷም እየነጠፈ-ትናንሽ አሳ-አስጋሪዎችም ችግር ካሁኑ እየከፋ-ነዉ-የሚሔድ።የምጣኔ ሐብትም-የማሕበራዊም ድቀት።በመጪዉ እሁድ የሚደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም የሚበየነዉ በሐገሪቱ ምጣኔ-ሐብታዊ ምርሕ ምክንያት ነዉ-ተብሎ ይጠበቃል።