1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ በ 2014 ጎ. ዓመት

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 9 2007

ፍጥረተ -ዓለም ፣ ለመከሠት የበቃበትንና ሥርዓት የያዘበትን ሁኔታ ተመራምሮ ለመገንዘብ መጣር ከዋናዎቹ የሳይንስ ተግዳሮቶች አንዱ ነው። ምንም ያህል ምርምር ያድርጉ፣ የሥነ ፈለክ ጠበብት እስካሁን ከዚህ እስከዚያ የሚባል አጽናፍ ስለሌሉት ሕዋ የሚያውቁት እጅግ ውስን እንደሆነ አይክዱም።

https://p.dw.com/p/1E6UP
ምስል picture-alliance/dpa/Illustris Collaboration
Hubble Bilder Bislang tiefstes Bild vom Universum
ምስል AP

ባለፈው ኅዳር 22 , 2007 ፌራራ ፣ ኢጣልያ ውስጥ ተሰብሰበው የነበሩ ዓለም አቀፍ የሥነ ፈለክ ጠበብት ፣ ፍጥረተ ዓለም ፤ 13,8 ቢሊዮን ዓመት ዕድሜ እንዳለው፤ 4,9 ከመቶው በአቶም ቁስ አካል፤ 26,6 ከመቶው በ«ጽልመታዊ ቁስ አካል» (dark matter) 68,5 ከመቶው ደግሞ በ«ጽልመታዊ የኃይል ምንጭ» (dark energy) የተገነባ መሆኑን የሚገልጽ ዘገባ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው ። ግን ጽልመታዊ ቁስ አካልና ጽልመታዊ የኃይል ምንጭ ምን እንደሆኑ በተጨባጭ ሁኔታ እስካሁን ማስረዳት እንዳልተቻለም ነው ጠበብቱ የሚናገሩት። ለዚህም ነው በቤተ ሙከራ፤ ስለፍጥረተ -ዓለም ፤ የቁስ አካል መነሻ ኢምንት ቅንጣት( ሂግስ ቦሰን) ወይም («የእግዚአብሔር ቅንጣት») ምንነት እንዲሁም ስለ«ጽልመታዊ ቁስ አካልና ጽልመታዊ የኅይል ምንጭ»ለማወቅ ምርምሩ የቀጠለው።

በፈረንሳይና ስዊትስዘርላንድ ድንበር በከርሠ-ምድር 100 ሜትር ጥልቀት ላይ 27 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያለው የምርምር ክብ መሿለኪያ የዘረጋው፣ የአውሮፓ የኑክልየር ምርምር ም/ቤት ፣ ከ 2 ዓመት ገደማ በፊት «የአቶም ጨፍላቂ«( Large Hadron Collider ) በተሰኘው መሣሪያ አማካኝነት ፕሮቶን ከሞላ ጎደል በብርሃን ፍጥነት እንዲጋጭ በማድረግ «ሂግስ ቦሶን»ን ለማግኘት እንደተቻለ ማስታወቁ አይዘነጋም። ይኸው የምርምር ተቋም ፤ ያኔ ከ 7 እስከ 8 (TeV)Teraelectronvolts የኃይል መጠን ሳይጠቀም አልቀረም ። ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ዕረፍት በኋላ ፣ በመጪው መጋቢት ወር አዲሱ LHC ከዚያ በፊት ባልተሞከረ፤ ኃይል 13 TeV እንደሚጠቀም ይጠበቃል። ጀርመናዊው ፣ የአውሮፓ የኑክልየር ምርምር ተቋም(CERN) ዋና ሥራ አስኪያጅ ሮልፍ ሆየር--

Raumfahrt ESA Weltraumsonde Rosetta verlässt Tschurjumow-Gerassimenko Komet
ምስል ESA

«በትክክል አዲስ ማሺን ነው። ሥራውን ስናስጀምረው፤ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። በከፍተኛ የኃይል ምንጭ ነው የምንጠቀመው። ይህም ከፍ ያለ ቁስ አካል ላላቸው ነገሮች ምርምር አዲስ በር ይከፍታል። ምናልባት መደበኛ የኃይል ምንጭ መለኪያ (ዳይግሜትር)ለመወሰን ይበጅ ይሆናል። ዋናው ጉዳይ ግን የሂግስ ቦሰንን ባሕርያት በዝርዝር እንድናውቅ ይረዳን ይሆንል። ምክንያቱም በሒግስ ቦሰን ባሕርያት በዛ ያለ አዳዲስ ፊዚክስም ያጋጥም ይሆናልና! ይህ ውጤት ደግሞ፤ በማጋጨት ነው የሚገኘው። በማጋጨት ፤ በማጋጨት!»

Philae auf Komet 67P/Tschurjumow-Gerassimenko ILLUSTRATION
ምስል ESA via Getty Images

ስለፍጥረተ ዓለም በደፈናው ብሎም ስለእኛይቱ ፕላኔት አፈጣጠር ፤ ውሃም ከየት እንዳገኘች ለማወቅ ይረዳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ተልእኮ ፣ ዘንድሮ ነው የተሣካው። የአውሮፓ የኅዋ ምርምር ድርጅት ፤ ከ 10 ዓመት ከ ዘጠኝ ወር ገደማ በፊት፣ ያመጠቃት፤ የምርምር መሣሪያ ጭና የተጓዘችው ሮዜታ የተባለችው መንኮራኩር፤ ከ 510 ሚሊዮን ኪሎሜትር በላይ ከተጓዘች በኋላ « ቹርዩሞቭ-ጌራሲሜንኮ» በተባለችው ስባሪ ኮክብ ፣ «ፊሌ» የተሰኘውን የምርምር መሣሪያ፣ ኅዳር 3 ቀን 2007 በተመደበለት፤ «አጊልኪያ» በተባለው ቦታ በተሳካ ሁኔታ ለማሳረፍ የበቃችበት ሁኔታ እፁብ ድንቅ ! ተብሏል። ሰው ሠራሽ መንኮራኩር ፣ ከአንድ ስባሪ ኮከብ ከባቢ አየር ሲደርስና የምርምር መሣሪያ ሲያስቀምጥ ሮዜታ የመጀመሪያዋ ናት። ዋና መሥሪያ ቤቱ በዳርምሽታት ጀርመን የሚገኘው የአውሮፓ የሕዋ ምርምር ድርጅትም በተልእኮው መሣካት ኩራት ተሰምቶታል። ምድራችን ፣ ውሃ ያገኘችው ከስባሪ ኮክብ ነው የሚለውን ነባቤ ቃልም «ፊሌ» ውድቅ አድርጎታል። በዚያ የተገኘው በረዶም ሆነ ውሃ የሃይድሮጂን መጠኑ በምድራችን ካለው በ 3 እጥፍ የላቀ በመሆኑ ፍጹም ተመሳሳይነት የለውም።

በሌላ በኩል ፕላኔቶችንና ጨረቃዎችን ለማሰስ በሚደረግ እሽቅድድም ፤ ሕንድ፣ ባለፈው ዓመት በጥቅምት ፤ ወደ ማርስ ያመጠቀቻት ፣ በህንድ ቋንቋ « ማንጋሊያን»(የማርስ መንኮራኩር) የተባለችው መረጃ ሰብሳቢ መንኮራኩር ፤ ባለፈው መስከረም 14 ፤ 2007 በተሣካ ሁኔታ ከማርስ ማሕዋር መድረሷ ተረጋግጧል። በ 74 ሚሊዮን ዶላር ወጪ፣ ያላንዳች ሳንክ የተከናወነ የመጀመሪያ ተልእኮ ነው። ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ «ግራቪቲ » ለተሰኘ ፊልም 100 ሚሊዮን ዶላር ነው ያወጡት።

ወደ ኅዋ ሰውና ዕቃ ለማጓጓዝ በአሁኑ ወቅት የሩሲያ ጥገኛ እንደሆነ የሚገኘው ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የበረራና የኅዋ ምርምር አስተዳደር (NASA) እ ጎ አ ከ 2017 አንስቶ፤ «ቦይንግ» ና «ስፔስ X»የተሰኙት ሁለት ኩባንያዎች ተልእኮውን ያሳኩለት ዘንድ ባለፈው መስከርም 6,2007 ተዋውሏል።

ሩሲያ በበኩሏ እርሷንና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ 15 ሀገራት በሕብረት ካቋቋሙት ዓለም አቀፍ የሕዋ ምርምር ቤተ ሙከራ(ISS) ራሷን በማግለል በሕዋ በግል የራሷን የምርምር ቤተ ሙከራ እንደምታቋቁም ፣ የኅዋ ምርምር ድርጅቷ ፤ «ሮስኮስሞስ» ይፋ አድርጓል። ለትብብሩ መሰናክል የሆነው በዩክሬይን ሳቢያ የአሜሪካና የሩሲያ አለመጣጣም ነው።

ታሕሳስ 1,2007 በእስቶክሆልም ፣ ስዊድን ፤በ 3 የተለያዩ በሳይንስ ዘርፎች በመድኃኒት ምርምርም ሆነ ሕክምና እንዲሁም በፊዚክስና ሥነ ቅመማ እ ጎ አ የ 2014 ኖቤል ውድድር አሸናፊዎች ተሸልመዋል።

Präsident Hollande verfolgt die Landung von Philae
ምስል picture alliance / abaca

በፊዚክስ የሽልማቱ አሸናፊዎች የሆኑት፤ የ 85 ዓመቱ አዛውንት ኢሳሙ አካሳኪና ፤ የ 54 ዓመቱ ገልማሣ ፣ ሂሮሺ አማኖ! ከጃፓን፤ 3ኛውም ፣ በዜግነት አሜሪካዊ ይሁኑ እንጂ በትውልድ ጃፓናዊ ናቸው። የ 60 ዓመቱ የፊዚክስ መምህር ሹጂ ናካሙራ! 3 ቱም ተማራማሪዎች የመጀመሪያውን ሰማያዊ ብርሃን ፈንጣቂ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ መሳሪያ ግኝት ይፋ ያደረጉ እ ጎ አ በ 1986 ዓ ም ነው። ኤሌክትሪክ አስተላላፊና ብርሃን አንጸባራቂ ዱቄት መሰልም ሆኑ ጠጣር አካላት፤ ከተለመዱት ለመብራት ከሚያገለግሉ ፍም መሰልና ኃይል ቆጣቢ አምፑሎች በላቀ ሁኔታ ይበልጥ ኃይል ቆጣቢ ፣ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሹም ሆነ ሳይቃጠሉ የሚያገለግሉ፤ በተጨማሪም ለተፈጥሮ አካባቢ ተስማሚዎች መሆናቸው ነው የሚነገርላቸው።

ቀይ ፤ አረንጓዴ እና ሰማያዊ ፣ --እነዚህ ሦስት ቀለማት ደማቅ ፣ ፍንትው ያለ ብርሃን ነው የሚፈነጥቁት። ለተፈጥሮ አካባቢም እጅግ ተስማሚ ነው --ኃይል ቆጣቢ ነውና! እ ጎ አ በ 1986 ዓ ም የተሳካላቸው ግኝት፤ ከተለመደው የሚግል አምፑል የላቀ ብቃት ያለው ብርሃን ሰጪ ነው። የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ ባልደረባ ፔር ዴልሲንግ---

«ይህ የብርሃን ፈንጣቂ ቁስ (LED) ሥነ ቴክኒክ አሮጌ ቴክኖጂዎችን በመተካት ላይ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙዎች ይዘውት የሚዞሩ ሲሆን ቴክኖሎጂው በእርስዎ ኪስም ይገኛል።»

ዴልሲንግ ይህን ሲሉ፣ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የእጅ ስልኮችን --«ስማርትፎንስ» ን ማመላከታቸው ነው። ስማርትፎንስ ያለ LED ሊታሰቡ ባልቻሉ ነበር። የኖቤል ኮሚቴ እዚህ ላይ፤ በተለይ በዓለም ዙሪያ የኤልክትሪክ አገልግሎት የማያገኘውን ሕዝብ ይዞታ ማሰላሰሉ አልቀረም። ለዚያ ህዝብም ፣ ኃይል ቆጣቢው LED መብራት ከጨለማ አውጥቶ በብርሃን የሚያኖር ይሆናል።

ጃፓናውያኑ ሳይንቲስቶች እንዲገኝ ያበቁት ሰማያዊ መብራት ሙቀት የለውም፣ ይሁን እንጂ ሙቀትንና ብርሃንን ማጣመር የሚያዳግት አይደለም።

Falkland Inseln Magellan Pinguin
ምስል imago/blickwinkel

በህክምና የዘንድሮ የኖቤል አሸናፊዎች፣ የአእምሮ ተማራማሪ የሆኑት የዩናይትድ ስቴትሱ ጆን ኦ ኪፍና 2ቱ የኖርዌይ ተወላጆች ባልና ሚስት ተማራማሪዎች፣ ሜይ-ብሪት ሞዘርና ኤድቫርድ ሞዘር ናቸው። ለሽልማት አሸናፊነት ያበቃቸው፤ በአንጎል ውስጥ ሕዋሳት ቦታ ወይም አቅጣጫ የሚይዙበትን ሥርዓት በምርምር ለማሳወቅ በመቻላቸው ነው።

አንጎል ውስጥ የሠራ አካላትን እንቅሥቃሴና አቅጣጫ አመላካች የሆኑ ሕዋሳትን ተለይተው በመታወቃቸው፣ የማስተዋል ችሎታ የሚያሳጣውን ወይም የሚያሥረሳውን በሽታ (አልትስሃይመርን) ምንነትና ፈውሱንም ለመሻት በሚደረግ ጥረት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ነው የታሰበው። እ ጎ አ በ 2050 የአልትስሃይመር ሕሙማን ቁጥር አሁን ካለው 44 ሚሊዮን በ3 እጥፍ ገደማ እንደሚጨምርና 135 ሚሊዮን ገደማ እንደሚደርስ ነው የሚገመተው።

የማጉሊያ መንጽርን ማይክሮስኮፕ ተግባር ፣ በወሳኝ ለውጥ ይበልጥ አሻሻሎ ፣ በ«ፍሎረሰንስ ማይክሮስኮፒ« እንዲተካና በ«ናኖስኮፕ» ሥርዓትና ደረጃ ለምድርም ለሕዋም ጠቀሜታ መስጠት የሚያስችል ተግባር በማከናወናቸው ነው ለመሸለም የበቁት።

በ 2014 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተወሱ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ የኢንተርኔት አስተዳደር ጥያቄ ነበረ። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፣ የኢንተርኔት መክፈቻ ቁልፍ ስሞችንና በመረቡ ላይ የነበረውን የበላይ ኀላፊነት ያለማንገራገር እንደሚያቆም ከማስታወቁ ሌላ፤ ቴክኒካዊ አሠራርንም ሆነ አመራር በዛ ያሉ ዓለም አቀፍ ውክልና ያላቸወ ወገኖች ፤ የመረጃ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች፤ የንግድ አካላትና መንግሥታት፤ የሲብሉ ማሕበረሰብ ቡድኖች፤ እንዲሁም የአካዳሚ ባለሙያዎች እንዲረከቡ ተስማምቷል። Internet Corporation For Assigned Names And Numbers (ICANN) የተሰኘው በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ለትርፍ እንደማይሠራ የሚነገርለት ድርጅት የውል ጊዜው እ ጎ አ በመስከረም ወር 2015 ሲያከትም ፤ እንደተባለው፣ አዲሱ አስተዳደር ዓለም አቀፋዊ መልክ ይኖራዋል ነው የተባለው። ኮምፒዩተሮች በኢንተርኔት መረብ መረጃ ሁሉ እንዲተላለፍ የሚያደርጉት የኢንተርኔት ፕሮቶኮል 4ኛው ምዓራፍ IPv4 በመጣበቡ፤ IPv6 እንዲተካው በመደረግ ላይ ነው። IPv4 በኢንተርኔት ሰነዶችን መመዝገብ የሚችልበት ቦታ በ 4 , 3 ቢሊዮን የተገደበ ሲሆን፤ IPv6 በአንጻሩ በትሪሊዮን የሚቆጠር የቁጥርና የአድራሻ ቦታ እንዳለው ይነገርለታል።

US-Navy LaWS Laser Weapon System
ምስል U.S. Navy/John F. Williams

ለመረጃ ልውውጥ ለዕውቀት ማዳበሪያ፤ ለትምህርት ማስፋፊያና ለመሳሰለው ሰፊ አገልግሎት የሚሰጠው ኢንተርኔት፤ መጠቀም ለሚችሉ ሁሉ እንደመሠረታዊ ሰብአዊ መብት ሊወሰድ እንደሚገባ በዓለም ዙሪያ በ 24 አገሮች የተካሄደ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ መጠይቅ አንጸባርቋል።

በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ 7,2 ቢሊዮን ገደማ ከደረሰው የዓለም ሕዝብ 4,4 ቢሊዮን ገደማው በአመዛኙም የአዳጊ አገሮች ዜጎች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አይደሉም። ደንማርክ፤ ፊንላንድና ኖርዌይ፤ በኢንተርኔት አጠቃቀም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ሲሆኑ፤ መጨረሻ ደረጃ ላያ ያሉት የመን ፣ ምያንማርና ኢትዮጵያ ናቸው። የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳይስፋፋ ብቻ ሳይሆን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችንና የተቃውሞ ፖለቲከኞችን ፣ ጋዜጠኞችንና የመሳሰሉትን ለመሰለል የሚያውሉት መንግሥታት በመኖራቸው፣ ክትትል እየተደረገ መሆን አለመሆኑን ለማወቅና ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ ፤ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት( AI )ባዘጋጀው DETECT በተሰኘው ሶፍትዌር ፤ ከድረ ገጹ መመሪያውን በማየት በነጻ መጠቀም እንደሚቻል ምክሩን የለገሠው ባለፈው ወር ነበር።

ከ 30 ሴኮንድ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ባትሪ መሙላት የሚቻልበት ሥነ ቴክኒክ ቴል አቪብ ፣ እሥራኤል ውስጥ ለዐውደ ርእይ መቅረቡ የተነገረው ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።

በ 2 ደቂቃ ውስጥ 70 ከመቶ ባትሪ መሙላት የሚቻልበት፤ የባትሪው የአገልግሎት ዘመንም 20 ዓመት ድረስ መዝለቅ እንደሚችል ያረጋገጠ የቴክኒክ ትርዒትም ባለፈው ጥቅምት መታየቱ ታውቋል።

በዓለማችን ፤ የግብርናን ሳይንስ በመጠቀም፤ አያያዝን በማሻሻልና ተገቢ ጥንቃቄ በማድረግ በቂ ምግብ የማያገኝ 2 ብቻ ሳይሆን 3 ቢሊዮን ሕዝብ መመገብ ይቻላል የሚል ዘገባ የቀረበው ባለፈው ሐምሌ ነበር።

የዩናይትድ ስቴቴeስ ባሕር ኃይል፣ መርከቦችን ለመጠበቅ፤ ጥይት ሳይጮኽ፤ መድፍ ሳይተኮስ በሰው ሠራሽ የጨረር ኃይል ፣ ተጻራሪን ማንጨርጨር እንደሚቻል የገለጠው በዚህ በያዝነው ወር ነው።

ከ 2014 ከፊል ዐበይት የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ውጤቶች ፣ ከፊሉን የተመለከትንበት የዛሬው ሳይንስና ሕብረተሰብ ዝግጅት በዚሁ ይጠቃለላል ።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ