1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኪርን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ወቀሱ

ቅዳሜ፣ የካቲት 4 2009

የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በየርስ በርስ ጦርነት የታወከችውን አገር ወደ የጎሳ ወገንተኝነት በመክተት እና «ተቀባይነት የሌለው የኹከት አዙሪት ውስጥ በመጣል» ራሳቸውን አራክሰዋል ሲሉ ወቀሱ።

https://p.dw.com/p/2XOoh
Sudan 5. Jahrestag Friedensabkommen
ምስል picture-alliance/dpa/T. Mckulka

ሉቴናንት ጄኔራል ሲሪሎ ስዋካ ይኽን ያሉት ለፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት ባስገቡት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ነው። ስዋካ በደብዳቤያቸው ፕሬዝዳንቱ የአንድ ጎሳ የበላይነት ፖሊሲ በመከተላቸው የኪር ዲንካ ጎሳ አባላት በወንድም እና እህቶቻቸው ተጠልተዋል ሲሉም ፅፈዋል። የጸጥታ አስከባሪዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጽሙትን የመብት ጥሰት እና የአንድ ጎሳ የበላይነት አብዝተው የወቀሱት ሉቴናንት ጄኔራል ቶማስ ሲሪሎ ስዋካ ኃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል። የጦር መኮንኑ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተከበሩ እንደነበሩ ሬውተርስ ዘግቧል። በስልጣን  ላይ ያለው መንግሥት «በጎሳዎች መካከል ጦርነት አቀነባብሯል» ብዬ አምናለሁ ያሉት ወታደራዊ መኮንኑ በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በኪር ሆን ተብሎ ተጥሷል ሲሉም ከሰዋል። ከዲንካ ውጪ ያሉ ጎሳዎች መዘንጋታቸውን፤ የዲንካ ጎሳ ወታደሮችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በሥልት በማዝመት የመሬት ወረራ እና የዲንካ የበላይነት የሚያቀነቅነው ፖሊሲ እንዲደግፉ መደረጉንም ሉቴናንት ጄኔራል ሲሪሎ ስዋካ ፅፈዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት በዚህ ላይ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። የደቡብ ሱዳንን የርስ በርስ ጦርነት የሸሹ ስደተኞች ቁጥር ከ1.5 ሚሊዮን መብለጡን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አርብ ዕለት ገልጦ ነበር። 

UN Blauhelme Süd Sudan Südsudan
ምስል Getty Images/A.G.Farran

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ