1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሲና፤ ሽብር እና ብቀላ

ሰኞ፣ ኅዳር 18 2010

በግብፅ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ባንድ ቀን፤ አንድ ሥፍራ፤ያልታጠቁ የዋሕ ምዕመናን መስጊድ ዉስጥ ሲያልቁባት ግን የአርቡ የመጀመሪያዉ ነዉ።የግብፁ የማስታወቂያ አገልግሎት ኃላፊ ሪአድ ረሽዋን እንደሚሉት ደግሞ  የአርቡ ጥቃት በዘመናይዋ ግብፅ የ200 ዓመት ታሪክ ዉስጥ አቻ የለዉም።

https://p.dw.com/p/2oLsk
Ägypten Sinai Al Arish Anschlag auf Rawda Moschee
ምስል picture-alliance/AA

ሲና፣ ሽብር እና ብቀላ

አሸባሪዎች ሲናን እንደገና አጠቁ።ሕፃን-ካዋቂ፤ ሴት-ከወንድ ሳይለዩ ሰወስት መቶ ግብፆችን ገደሉ።፤ የፆም፤ ፀሎት፤ፈጣሪን መማለጃዉን፤ ጡሐራዉን ሥፍራ በደም አበላ አጨቀዩት።በአስከሬን አጎደፉት።ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አልሲሲም ከፖለቲከኛነታቸዉ ይልቅ እንደ ጄኔራልነታቸዉ ፉከሩ።ጦራቸዉ ደም ጠጥቶ ደም የሚጠማዉን አስከሬን ቀብሮ-አስከሬን የሚቆጥረዉን ያን ምድር በጄት-ሔሊኮብተር ቦምብ፤ሚሳዬል አረር እንደገና ያጋየዉ ገባ።እንደ አብዛኛዉ የአይሁድ-አረብ ሐገር ሁሉ ሲና ድሮ-እንደ ጥንቱ ነበር። ዘንድሮም-እንደ ድሮዉ።የመገዳደል፤መበቃቀሉን ዑደት ቀጥሏል ።

አጠገቡ ከተደረደሩት አስከሬኖች ሁሉ አጭሩ ወይም ትንሽ ነዉ።በነጩ ከፈን ላይ ሱሌይማን አብደላሕ የሚል ተፅፎበታል።ሱሌይማን-እንደ ሙስሊሞቹ ወግ፤ በሙስሊሞች ቅዱስ ቀን አባቱን ተከትሎ መስጊድ ሔደ-ፈጣሪን ሊማፀን።በዚያዉ ቀረ።እንደ ሱሌይማን አስበዉ፤ እንደ ሱሌይማን አድርገዉ እንደሱ በሰገዱበት መስጊድ አስከሬናቸዉ ከተለቀመዉ 26ቱ ክፉ-ደጉን በቅጡ ያለዩ የሱሌይማን የዕድ አሜ አቻ ታዳጊ ወጣቶች ናቸዉ።

ሲና።እንደ ብዙዉ የአካባቢዉ ግዛት ሁሉ ፈርኦኖች፤ አሲሪያዎች፣ ፋርሶች፤ሮሞች፤ ቤዛንቲኖች፤ አዩቢዶች፤ መምሉኮች፤ ኡስማኒያዎች፤ ብሪታንዎች፤አረቦች፤ እስራኤሎች በየዘመናቸዉ ቀዳሚያቸዉን ገድለዉ፤ ገዝተዉ፤ ገንብተዉ፤ ተገድለዉ ተገዝተዉበታል።

የጎሳ፤ የፖለቲካ፤ የግዛት ይባል የኃይማኖት ጦርነት፤ ግጭት፤ ግድያ እና ጥፋትን ኖራበታለች። በግብፅ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ባንድ ቀን፤ አንድ ሥፍራ፤ያልታጠቁ የዋሕ ምዕመናን መስጊድ ዉስጥ ሲያልቁባት ግን የአርቡ የመጀመሪያዉ ነዉ።የግብፁ የማስታወቂያ አገልግሎት ኃላፊ ሪአድ ረሽዋን እንደሚሉት ደግሞ  የአርቡ ጥቃት በዘመናይዋ ግብፅ የ200 ዓመት ታሪክ ዉስጥ አቻ የለዉም።

Mideast Egypt Sinai
ምስል picture alliance/AP Photo

                       

«መሐመድ ዓሊ ፓሻ ከ200 ዓመት በፊት በጀመሩት በግብፅ ዘመናይ ታሪክ ዉስጥ መስጊድ ላይ ያነጣጠረ ይሕን መሰል ጥቃት ሲደርስ የመጀመሪያዉ ነዉ።»

ታሪካዊቱ ሐገር አዲስ ታሪክ ጨመረች።ሴት-ወንድ፤ ልጅ-አዋቂ ሳይለይ 305 የዋሐን በቦብ እና ጥይት  ያለቁበት ዘግናኝ ታሪክ፤ ከአንድ መቶ በላይ አካላቸዉን ያጡበት አሳዛኝ ታሪክ።አሳሳቢ እዉነት።

በጣም አሳሳቢዉ የአ(ል)-ረዉዳ መስጊድን ወደ ደም ኩሬነት፤ ወደ አስከሬን ክምርነት፤ ወደ ምፅዓት ሥፍራነት የቀየሩት ወገኖች ማንነት፤ ዓላማ ፍላጎታቸዉ እስካሁን በዉል አለመታወቁ ነዉ።የግብፅ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታሕ አልሲሲ ግን ተክፊሪ (ከሐዲ ወይም እምነት የለሽ) ያሏቸዉን ወገኖች ጦራቸዉ እንደሚያጠፋቸዉ ዝተዋል።

«ጦሩ እና ፖሊስ በሙሉ ኃይላቸዉ (እርማጃ ወስደዉ) ባካባቢዉ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ፀጥታ እና መረጋጋት ያሰፍናሉ።እንበቀላለን።ይሕን ጥቃት፤ እነዚሕን ፅንፈኛ አሸባሪዎች፤ እኒሕን ተክፊሮች በምሕረት የለሽ ጥንካሬያችን እንበቀላለን።»

ጥቃቱን ያደረሱት ወገኖች  የአል ሲሲ መንግስትን የሚቃወሙ የአካባቢዉ ጎሳ ታጣቂዎች ናቸዉ የሚሉ አሉ።የሱፊ ሐራጥቃን የሚጠሉ ኃላት ናቸዉ ባዮችም አሉ።ጥቃቱ ሲፈፀም መስጊዱ አካባቢ ነበርን የሚሉ ሰዎች ደግሞ አጥቂዎቹ እራሱን የኢራቅ እና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) ብሎ የሚጠራዉን ቡድን አርማ ሲያዉለበልቡ አይተናል ይላሉ።

ፕሬዝደንት አል ሲሲም ሆኑ ሌሎቹ የአጥቂዎቹን ማንነት፤ዓላማ እና ፍላጎት በዉል አያዉቁም።አል ሲሲ እንደ ግን እንደ ዛቱት ዛቱት ጦራቸዉን ለብቀላ አዘመቱ።ጦሩም የአሸባሪዎች ይዞታ ያለዉን አካባቢ፤የጦር ማከማቻ እና መጋዘን በዘመናይ ተዋጊ ጄቶች እና ሔሊኮብተሮች ማዉደሙን አስታወቀ።ማንነቱ የማይታወቅ ጠላት ይዞታ በሰዓታት ልዩነት ታዉቆ የብቀላ ጥቃት ዒላማ መሆኑ ግራ ነዉ።

Griechenland Ägyptischer Präsident Al-Sisi
ምስል Reuters/Y. Kourtoglou

በነቲንገሐም፤ ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ የፀጥታ እና የአሸባሪነት ጉዳይ አጥኚ ፕሮፌሰር አፍዛል አሽረፍ ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ  እንደነገሩት ደግሞ የግብፅ ጦር አወደመዉ የተባለዉ የአሸባሪዎች መሳሪያ እና ይዞታ የሚታወቅ ከነበረ አሸባሪዎቹ በጠራራ ፀሐይ ያን ሁሉ ሰዉ ከመፍጀታቸዉ በፊት እርምጃ ያልተወሰደባቸዉ ምክንያት አነጋጋሪ ነዉ። አጠቃላይ ስልት-ዉጤቱም አሳሳቢ።

                                    

«ከሚያሳስቡኝ ነገሮች አንዱ የግብፅ ጦር ባለፉት ሰዓታት የጦር መሳሪያ ማከማቻ እና ሌሎች ይዞታዎችን አዉድሜያለሁ ማለቱ ነዉ።መንግሥት ሥለነዚሕ ይዞታዎች የሚያዉቅ ከነበረ (አሸባሪዎቹ) ጥቃት እስከሚያደርሱ ድረስ መጠበቅ አልነበረበትም።እርምጃዉ የዛቻ እና መግለጫ መሸፈኛ መሆን የለበትም።የግብፅ ጦር እና መንግሥት ከሚፈለገዉ በላይ እርምጃ ላለመዉሰድ መጠንቀቅ አለባቸዉ።እርምጃዉ ተመጣጣኝ መሆን አለበት።ይሕም ቢሆን ከብቀላ ይልቅ ፍትሕ መሆን አለበት።»

እርግጥ ነዉ ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች ከተጠቃችበት ከመስከረም 1994 ወዲሕ መንግስታት አሸባሪ በሚሏቸዉ ኃይላት ላይ የሚወስዱት እርምጃ ሁሉ የጦር ኃይል እንጂ የዲፕሎማሲ አይደለም።ብቀላ እንጂ ፍትሕ አይደለም።አሸባሪ የሚሏቸዉ ቡድናት ወይም ስብስቦች «አሸባሪ» ለመሆናቸዉ ማረጋገጪያ ሰጪዎችም፤ ከሳሾችም፤ ፈራጆችም ፍርድ አስፈፃሚዎችም እራሳቸዉ መንግስታት ናቸዉ።የግብፅ መንግስትም ከድፍን ዓለም የተለየ ሊሆን አይችልም።

Ägypten Die Inseln Sanafir und Tiran
ምስል Getty Images/AFP/Str

ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ፤ከሶማሊያ እስከ ሊቢያ፤ ከናይጄሪያ እስከ ሶሪያ መንግሥታት የወሰዱ እና የሚወስዱት የብቀላ እርምጃ ግን አሸባሪዎች ሥም፤አቋማቸዉን እየቀያየሩ በመላዉ ዓለም እንዲሰራጩ፤ በየስፍራዉ እንዲያሸብሩ እና እንዲገድሉ ከማድረግ ባለፍ የተከረዉ ነገር አለመኖሩ ነዉ-እንቆቅልሹ።

የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈዉ ሳምንት የሶሪያዉን አቻቸዉን በሽር አልሰድን ሲያነጋግሩ እንዳሉት የሁለቱ ሐገራት ጦር ሶሪያ ዉስጥ በመሸጉ አሸባሪዎች ላይ የከፈተዉን ጦርነት በቅርቡ በድል ያጠናቅቃል።ይሁን እንጂ ፑቲን አክለዉ እንዳሉት ለአሸባሪነት መፈጠር ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች በመላዉ ዓለም ሥላሉ አሸባሪዎች ዳግም መፈልፈላቸዉ አይቀርም።

«እድሜ ለሩሲያ ጦር ትግል፤ ሶሪያ እንደ መንግስት ከመጥፋት ድናለች።የሶሪያን ሁኔታ ለማረጋጋት ብዙ ነገር ተሰርቷል።ከአሸባሪዎች ጋር የሚደረገዉ ዉጊያ በቅርቡ አራት ነጥብ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ አለኝ።በዓለም፤በመካከለኛዉ ምሥራቅ እና ሶሪያም ዉስጥ አሸባሪዎች የሚፈለፈሉባቸዉ ብዙ ችግሮች ሥላሉ አዳዲስ አሸባሪዎች ብቅብቅ ማለታቸዉ አይቀርም። ዋናዉ ምግባራችን ግን ከፍፃሜዉ ላይ ደርሷል።»

የግብፁ ፕሬዝደንትም አሸባሪዎች ሐገራቸዉን የሚያጠቁት በአካባቢዉ በጦርነት፤ ግጭት እና ሽብር ከሚተራመሱት ሐገራት ለመቀየጥ ነዉ ባይ ናቸዉ።ፑቲን እንዳሉት አሸባሪዎች የሚፈለፈሉበት ችግር ሶሪያም፤ መካከለኛዉ ምሥራቅም፤ በመላዉ ዓለምም አሁንም ካለ ከ1994 ጀምሮ ኃላን መንግስታት በጣሙን ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራዉ ዓለም አቀፍ  ፀረ ሽብር ዘመቻ የሽብርን ዑደት ለማስቀረት ያመጣዉ ዉጤት የለም ማለት ነዉ።

አልሲሲ እንዳሉት የአሸባሪዎቹ ዓላማ ግብፅን እንደ ጎረቤትዋ ሊቢያ፤ እንደ ቀድሞ ተጣማሪዋ ሶሪያ፤ ወይም እንደኢራቅ ለማድረግ ከሆነ ቃዛፊን ከሊቢያ፤አሰድን ከሶሪያ፤ ሳዳምን ከኢራቅ ያሰወገዱት እና ለማስወገድ የሚዋጉት ኃይላት ዓላማ ምንነት ያጠያይቃል ማለት ነዉ።

ግብፅ ባጠቃላይ ሲና በተለይ በአሸባሪዎች ስትጠቃ ያሁኑ ከፍተኛዉ እንጂ የመጀመሪያዉ አይደለም።በተለይ ጄኔራል አልሲሲ በሕዝብ የተመረጡትን ፕሬዝደንት መሐመድ ሙሪስን በኃይል ከስልጣን አስወግደዉ የመሪነቱን ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ወዲሕ ጥቃቱ ተደጋግሟል።መንግሥት ጥቃት በደረሰ ጊዜ ሁሉ አጥቂዎቹን ለማጥፋት ያልዛተ-ያልፎከረበት የኃይል እርምጃ ያልወሰደበት ጊዜም የለም።አሸባሪ እና ሽብር ግን ቀጠለ ምናልባትም ጨመረ እንጂ አልቀነሰም።

Anschlag Ägypten Sinai Verwandte Opfer
ምስል AFP/Getty Images/M. El Shahed

ብዙዎች እንደሚሉት ግብፅ ይሁን ሌላ ሥፍራ ለአሸባሪዎች መፈልፈል ዋና ከሚባሉ ምክንያቶች አንዱ ጭቆና ነዉ።የበርሊኑ ፍሪ ዩኒቨርስቲ አጥኚ አሕመድ በዳዊ እንደሚሉት ጭቆና ካለ ኃይል የተቀየጠበት አመፅ እና ሽብር አይቀርም።

                                  

«በፖለቲካዉ ረገድ ጭቆና ሁሉንም እየነካ ነዉ።ግብፅ ዉስጥ እንደምናየዉ እስርቤት ዉስጥ የሚማቅቁት ፅንፈኞች ብቻአይደሉም።ወጣቶች ናቸዉ።የተሻለ ኑሮ  የሚፈልጉ ወጣቶች ናቸዉ። እንደዚሕ ዓይነቱ ሁኔታ (አገዛዝ) እስካለ ድረስ ኃይል የተመላበት አፀፋ መኖሩ አይቀርም።ብዙ ጊዜ እንዲሕ ዓይነት የኃይል አፀፋ የሚወስዱት ፅንፈኞች ናቸዉ።ምክንያቱም (ባሁኑ ወቅት) እንዲሕ አይነቱን ቅሬታ እና ብሶትን ለመበቀል ጥቃት ማድረስ የሚችለዉ ብቸኛዉ ወገን ፅንፈኝነት ነዉ።»

የሰዉ ልጅ ማዕድን ከመሬት ማዉጣት የጀመረዉ እዚያ ነዉ።ሰወስቱን ትላልቅ ኃይማኖች መጀመሪያ ካስተናገዱ ጥቂት አካባቢዎች አንዷ ናት።ፈርኦኖች የተርኮይስ ምድር ያሏትም ለዚሕ ነዉ።ሒብሩ ተናጋሪዎች ሴኔሕ፤ ፋርሶች አበር ናሕራ-(የወንዝ ማዶ-ምድር)።የዘመኑ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሳይናይ ዓለም እኛ ሲና እንላታለን።አንዱም አልጠቀመታም።ሕዝቧ የድሆች ደሐ ነዉ።የአሸባሪዎች ዒላማ፤ የመንግስት ጦር ጥቃት ሰለባ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ