1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳንና የሰላሙ ውል

ዓርብ፣ ግንቦት 20 1996

የሱዳን መንግሥት ካለፉት ሁለት አሠርተ ዓመታት ወዲህ የቀጠለውን የርስበርስ ጦርነት ለማብቃት ከትናንት በስቲያ ከደቡብ ሱዳን ዓማፅያን ጋር አንድ የሰላም ውል ተፈራረመ።

https://p.dw.com/p/E0kx
የሰላሙ ውል ፍረማን በጉጉት የተጠባበቁ ሱዳናውያን
የሰላሙ ውል ፍረማን በጉጉት የተጠባበቁ ሱዳናውያንምስል AP

ሦስት ክፍሎች የያዘው ስምምነትና በናይቫሻ ኬንያ የተፈረመው የሰላም ውል በአፍሪቃ ረጅሙን የርስበርስ ጦርነት ያበቃል የሚለውን ተስፋ አሳድሮዋል። ይሁንና፡ ውሉ በምዕራባዊው ሱዳን ለሚካሄደው ውጊያ መፍትሔ ባለመሻቱ፡ በዚሁ ሰብዓዊ መቅሠፍት ባሠጋበት አካባቢ ለሚኖረው የተቸገረው ሕዝብ ያስገኘው ፋይዳ የለም።
የሰላሙ ውል የሥልጣኑን ክፍፍልና የነዳጅ ዘይት ንጣፍ አላቸው ተብለው የሚገመቱት የሦስቱ አከራካሪ አካባቢዎችን አቋም አስተካክሎዋል። ይሁንና፡ ዘላቂ የተኩስ ኡም ደምብ የሚደረስበትን ሁኔታ አላዘጋጀም፤ በርካታ ጉዳዮችም ገና መልስ ላላገኙ ግልፁን መልስ አላገኙም። ውሉ በደቡባዊ ሱዳን የሰላሙን ተስፋ በፈነጠቀበት ባሁኑ ጊዜ በምዕራባዊው የሱዳን ከፊል ግን የረሀብና የሞቱ ጥላ እንዳንዣበበ ይገኛል። በደቡብ ሱዳን የቀጠለው የርስበርስ ጦርነት የሁለት ሚልዮን ሕዝብ ሕይወት አጥፍቶ ሌሎች አራት ሚልዮንን ለስደት ዳርጎዋል፤ በምዕራባዊው ሱዳን የሚካሄደውም ቶርነት ከአንድ ሚልዮን የሚበልት ሰው ከቤት ንብረቱ አፈናቅሎ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንዳያጠፋ አሥግቶዋል።
በናይቫሻ ኬንያ ከሁለት ዓመት አዳጋች ድርድር በኋላ የተፈረመው የሰላም ውል እንደ ትልቅ ርምጃ ቢታይም፡ ከብዙ ወራት ወዲህ ብዙ ማከራከር የያዙት ጥያቄዎች ገና መልስ ባለማግኘታቸው ለፈንጠዝያ ጊዜው ገና ብስል አይደለም። ይሁንና፡ ሰሜንና ደቡብ ሱዳናውያኑ በሚቀጥሉት ሣምንታት በሚካሄዱ ድርድሮች ይዘጋጃል የሚባለውን አጠቃላዩን የሰላም ውል ለመፈራረም እንዲህ እንዳሁኑ ተቀራርበው አለማወቃቸው ሲታሰብ በሰላሙ ውል አኳያ ጥርጣሬ መሰማቱ ለምን በሚል ማጠያየቁ አልቀረም።
በ 1975 ዓም በደቡብ ሱዳን በተጀመረው የርስበርስ ጦርነትና የካቲት 1995 ዓም በምዕራብ ሱዳን በፈነዳው ጦርነት መካከል ግንኙነት እንደሌለ ተገልፆዋል፤ ይህ ጥሩ ዜና ነው፤ ምክንያቱም፡ ሱዳን ባለፉት ሁለት አሠርተ ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ተዳቃ በመድማት ላይ ስለምትገኝ የደቡብ ሱዳን ጦርነት አሁኑኑ ማብቃት አለበት። ግዙፉ ዲፕሎማቲክ ግፊት፡ በተለይም ዩኤስ አሜሪካ ያሳረፈችው ተፅዕኖ የሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች በጦር ኃይሉ ዘዴ መፍትሔ እንደማይገኝለት ከብዙ ዓመታት ወዲህ ላወቁት የርስበርስ ጦርነታቸው ባፋጣን ፖለቲካዊውን መጽሔት እንዲያፈላልጉ አስገድዶዋቸዋል።
በሚቀጥሉት ሣምንታት በሚደረጉት ድርድሮች የሚዘጋጀው አጠቃላዩና የመጨረሻው የሰላም ውል በሚፈረምበት ጊዜ ሱዳን ውስጥ ስድስት ዓመት የሚቆይ የሽግግር መንግሥት ይቋቋምና የደቡብ ሱዳን ሕዝብም ከስድስት ዓመት በኋላ የራሱን ዕጣ፡ ማለትም፡ ነፃ መንግሥት ማቋቋም ወይም ከሱዳን ጋር እንደተጠቃለለ መቆየት አለመቆየቱን ራሱ የመምረጥ ዕድል ይኖረዋል። ከነዳጅ ዘይቱ ሀብት ሽያጭ የሚገኘውም ገቢ በተቀናቃኞቹ ወገኖች መካከል ይከፋፈላል፤ የሱዳን መንግሥትም በዚሁ አካባቢ ያሠማራውን ጦሩን፡ ከጥቂት ሺዎቹ በስተቀር ማንሣት ይኖርበታል።
ይሁንና፡ ይህንኑ ከደቡብ ሱዳን የሚያነሣውን ጦሩን ውዝግብ ወዳለበት ምዕራባዊው ሱዳን እንዳይልክ፡ በዚሁ አካባቢ በበሚኖረው ጥቁር አፍሪቃዊ ሕዝብ አንፃር የጭካኔ ተግባር የሚፈፅሙትን ዐረባውያን ሚሊሺያዎች እንዳይደግፍ እና አካባቢውን ለዓለም አቀፍ ርዳታ አቅራቢዎች ክፍት እንዲያደርግ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ ግፊቱን የማጠናከር ኃላፊነት አለበት።