ሰማያዊ ፓርቲ ለሜርክል የላከዉ ደብዳቤ
ሰኞ፣ ሰኔ 1 2007
የፓርቲዉ ሊቀመንበር ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት እንደተናገሩት ደብዳቤዉ መራሂተ መንግሥቷ እጅ ደርሷል።
ትናንት አረፋፈዱ ላይ ጀርመን ባቫርያ ግዛት በሚገኘዉ «ኤልማዉ» ጥንታዊ ቤተ-መንግሥት ዉስጥ ጉባኤያቸዉን ጀመሩት ሰባቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሃገራት መሪዎች ዛሬ በሁለተኛዉ ቀን ጉባኤያቸዉ ላይ ከአፍሪቃ የኢትዮጵያዉን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ አምስት መሪዎችን ጋብዘዋል።
የቡድን ሰባት የወቅቱ ሊቀ-መንበር የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኢትዮጵያዉን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በዚህ ጉባኤ መጋበዛቸዉ እጅግ አሳዝናል ያለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ «ሰማያዊ ፓርቲ» ለመራሂተ መንግሥትዋ ግልፅ ደብዳቤን ጽፎአል። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት እንደሚሉት ግብዣዉ በኢትዮጵያ ያለዉን ሁኔታ ግምት ዉስጥ ያላስገባ ነዉ።
በሃገሪቱ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ አልተካሄደም፤ ለ 24 ዓመታት ስልጣን ላይ የሚገኘዉ መንግሥት አሁንም በርካቶችን በእስር በመያዙ ለከፍተኛ ባለስልጣናቱ በዚህ ደብዳቤ ጥያቄያችንን አቅርበናል ሲሉ ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት ተናግረዋል።
ሰማያዊ ፓርቲ ለጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት ከላከዉ ደብዳቤ መልስ ይገኛል ብሎ ይጠብቅ ይሆን፤ ይህ በነሱ በኩል የሚታይ ይሆናል። እዉነታዉ ሁሉ ነገር መሸፋፈን በማይቻልበት አኳን ይፋ ወጥቷል ሲሉ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት መልስ ሰጥተዋል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ