1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አክባር አሊ ሃሼሚ ራፍሳጃኒ የኢራን አብዮት መሰሶ ከሚባሉት ጎራ ይመደባሉ

ሰኞ፣ ጥር 8 2009

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን በተሒራን ዩኒቨርሲቲ በተካሔደው የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር ተሰናብተዋቸዋል። በዕለቱ የተሒራን አደባባዮች በሰዎች ተጨናንቀው ታይተዋል። የሥንብቱን ልዩ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የመሩት የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አሊ ኻሜይኒ ነበሩ።  አሊ ሃሼሚ ራፍሳጃኒ ታኅሳስ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በ82 ዓመታቸው አርፈዋል።

https://p.dw.com/p/2VrjQ
Iran Rafsanjani
ምስል Borna

ራፍሳንጃኒ -የለውጥ ፈላጊዎቹ ጠበቃ

ከቀድሞው የኢራን ልዕለ መሪ አያቶላህ ሩሖላህ ኾሜይኒ የተቃውሞ ትግል እስከ ዕለተ-ሞታቸው ድረስ ተደማጭ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግን ደግሞ አወዛጋቢ ሰው ነበሩ-አሊ አክባር ሐሼሚ ራፍሳንጃኒ። ደማምነታቸው እና ሐብታቸው ጥቂት ኢራናውያን ብቻ የታደሉትን ፖለቲካዊ ጉልበት ሰጥቷቸው እንደነበር ይነገራል። በ82 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ራፍሳንጃኒ የኢራን እስልማዊ አብዮት ምሰሶ፤የተራማጆች ጠበቃ ናቸው ይሏቸዋል ደጋፊዎቻቸው። የቀድሞው የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ሩሖላህ ኾሚኒ ረዳት ሆነው ፖለቲካን የጀመሩት ራፍሳንጃኒ ወግ-አባቂነታቸውን እርግፍ አድርገው የተዉ የመሐል ሰው ነበሩ። ራፍሳንጃኒ አገራቸው ከምዕራባውያን ጋር ያላትን ወዳጅነት እንድታለሳልስ በሯንም እንድትከፍት በመወትወታቸው ባላንጣም ወዳጅም አፍርተዋል። ኢራናዊቷ የዶይቼ ቬለ ጋዜጠኛ ሾራ አዛርኖሽ እንደምትለው ኢራናውያን ራፍሳንጃኒ አንድም በበጎ አሊያም በመጥፎ ያወሷቸዋል።

«ሐሼሚ ራፍሳንጃኒ በኢራን የሚታወሱበት መንገድ የአንደኛው ቡድን ከሌላው ይለያል ብዬ አስባለሁ። ሁለቱ ቡድኖች ራፍሳንጃኒን በተመለከተ ሁለት አይነት አዝማሚያዎች አሏቸው። አንደኛው ወገን በራፍሳንጃኒ ያለፈ ታሪክ ላይ የማተኮር ዝንባሌ ይታይበታል። በትክክል ለመናገር የ1979ኙን የኢራን አብዮት ተከትሎ ያለውን ጊዜ ማለት ነው። በጊዜው ለመንፈሳዊ መሪው አያቶላህ ኾሜይኒ ቅርብ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ነበሩ። የአገሪቱ ምክር ቤት ሊቀ-መንበርም ሆነው አገልግለዋል። ከአያቶላህ ኾሜይኒ ቀጥሎ በመንግስቱ ውስጥ ሁለተኛ ሰው ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። በኢራን አበይት ጉዳዮች የውሳኔ አሰጣጥ ውስጥ እጃቸው ነበረበት። ካሳለፏቸው ውሳኔዎች መካከል አስከፊ የነበሩም ይገኙበታል። ከእነዚህ መካከል የ1988ቱ ግድያ አንዱ ነው።»

Iran Beerdigung Rafsandschani
ምስል picture-alliance/AP Photo/V. Salemi

ራፍሳንጃኒ አብዝተው በሚወቀሱበት የጎርጎሮሳዊው 1988 ዓ.ም. ግድያ አያቶላህ ሩሖላህ ኾሜይኒ ባስተላለፉት ትዕዛዝ ወደ 5,000 የሚጠጉ የፖለቲካ እስረኞች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይነገራል። በኢራን እስላማዊ አብዮት አስረኛ አመት ዋዜማ ሴቶች እና ታዳጊዎች በስቅላት ተቀጥተዋል። ሌሎች ደግሞ በአልሞ ተኳሾች ጥይት ተደብድበዋል፤ሕይወታቸው የተረፈው ግርፋት እና እንግልት ደርሶባቸዋል። አብዛኞቹ የኢራን ልሒቃን፤ተማሪዎች፤ግራ ዘመም ፖለቲከኞች እና የኢራን ሞጃሒዲን ድርጅት አባላት ነበሩ። የተቃውሞ ፖለቲካ አመራሮች እና የጎሳ መሪዎችም ነበሩበት። ዓለም በሌሎች ጉዳዮች ተጠምዶ ችላ ብሎታል የሚባለው የኢራን ግድያ ዒላማዎች ጋዜጣ በመበተን፤በተቃውሞ ሰልፎች በመካፈል እና ለእስረኞች እና ቤተሰቦቻቸው የድጎማ ገንዘብ በማከፋፈል የተከሰሱ እንደነበሩ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዶሴ ይጠቁማል።

የኢራንን ፖለቲካ በትኩረት የሚከታተሉ ምዕራባውያን የጸጥታ ተንታኞችም ራፍሳንጃኒ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው በተሰማ ማግስት መንግስታቸው በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ በፈጸማቸው ግድያዎች ውስጥ እጃቸው ነበረበት ሲሉ ፅፈዋል። ራፍሳንጃኒ የአጥፍቶ ማጥፋት የቦምብ ጥቃቶች እና በስደት የሚገኙ ተቃዋሚዎች ግድያዎች እንዲፈጸሙ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል እየተባሉም ይወቀሳሉ። በጎርጎሮሳዊው 1990 ዓ.ም. በስዊዘርላንዷ የጄኔቫ ከተማ አደባባይ  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመጀመሪያው የኢራን አምባሳደር እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዶ.ር ካዜም ራጃቪ ሲገደሉ ራፍሳንጃኒ በፕሬዝዳንትነት መንበረ ሥልጣኑ ላይ ነበሩ። ዶክተር ካዜም ራጃቪ በተገደሉበት ጊዜ በግል ፈቃዳቸው ከአምባሳደርነታቸው ለቀው የኢራን መንግሥት ይፈፅመዋል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያወግዙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኋላም የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ ነበሩ።

ኢራን ራፍሳንጃኒ በተመኙት ልክም ባይሆን ከምዕራቡ ጋር የገባችበትን ዲፕሎማሲያዊ አጣብቂኝ አላልታ በኑክሌር ማብለያዋ ላይ ሥምምነት ፈርማለች። የኢራን መንፈሳዊ መሪ ከምዕራባውያኑ ጋር የተፈጸመውን ውል እንዲፈርሙ በማግባባት ቀዳሚውን ሚና የተጫወቱት ራፍሳንጃኒ እንደሆኑ ይነገራል። የኢራን ወግ-አጥባቂዎችን ይገዳደሩ የነበሩት ራፍሳንጃኒ በሌሉበት በዩናይትድ ስቴትስ ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በመምጣታቸው  የሥምምነቱ እጣ-ፈንታ አልየለትም። አያቶላሕ የሚለውን ከፍተኛ የኢራን ማዕረግ የተጎናፀፉት አሊ አክባር ሐሼሚ ራፍሳንጃኒ የለውጥ አቀንቃኝ ናቸው የሚባሉት ሓሳን ሮሓኒ በፕሬዚደንትነት እንዲመረጡ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ይነገራል። ጋዜጠኛ ሾራ አዛርኖሽ መሰል ስኬታቸውን እየቆጠሩ የሚያሞግሷቸው መኖራቸውን ትናገራለች።

Tehran Präsident Akbar Hashemi Rafsanjani und Recep Tayyip Erdogan
ምስል picture alliance/dpa/AA/abaca/H. Sahin

«ሁለተኛው ወገን የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ሕይወታቸው ላይ የሚያተኩር ነው። አረንጓዴውን አብዮት መቀላቀላቸውንና በኢራን ውስጥ ላለው የለውጥ ፈላጊዎች ያደረጉት ድጋፍ እንቅስቃሴዎች በአብነት ይጠቅስላቸዋል።»

ባለፉት 10 አመታት ራፍሳንጃኒ የፖለቲካ ኃይላቸው ደክሞ ከሃዲ የሚል ሥም ተለጥፎባቸው በወግ-አጥባቂዎቹ አድኃሪ ተደርገው ቢሳሉም በሥንብታቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገኘታቸው አስደናቂ ተብሏል። ኢራን ከኢራቅ ጦር በተማዘዘችባቸው ዓመታት የአገሪቱ ጦር አዛዥ የነበሩት ራፍሳንጃኒ በስተመጨረሻ የህይወት ዘመናቸው ከፊት ለፊት ፖለቲካው ገለል ተደርገው ነበር። ከበስተጀርባ ግን ከመንፈሳዊው መሪ ጋር ባላቸው ቅርበት በበርካታ ፍላጎቶች መካከል ያለውን ቅራኔ የሚያስታርቁ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ። አብረዋቸው የሰሩ ተባባሪ፤ሰላም ወዳድ እና ምክንያታዊ ይሏቸዋል። ማግባባት እና ማስተባበርም ይችሉበታል።

ራፍሳንጃኒ ከጎርጎሮሳዊው 1980-88 ዓ.ም. ኢራን ከጎረቤታቸው ኢራቅ ጋር የገባችበትን ጦርነት ለማብቃት ጉልህ አስተዋፅዖ ማበርከታቸው ይነገራል። ኢራን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ እንድትቀበል ራፍሳንጃኒ የጎላ ሚና ነበራቸው። ከ1989 እስከ 1997 ዓ.ም. በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ራፍሳንጃኒ  ለአገራቸው ነፃ ኤኮኖሚን የሚያበረታቱ ነበሩ። ከኢራን አብዮት በፊትም ይሁን በኋላ ከፍ ያለ ሚና የነበራቸው ራፍሳንጃኒ በወግ አጥባቂዎቹ ክፉኛ ተፈትነዋል። ኢራንን የሚከታተሉ የጸጥታ ተንታኞች በአዲሱ ትውልድ ዘንድ ሳይቀር የቀድሞውን ልዕለ መሪ አብዮት የሚያቀነቅኑ ወግ አጥባቂዎች መኖራቸው ይነገራል።

ራፍሳንጃኒ ከጎናቸው ባይኖሩ ኖሮ የዛሬው ፕሬዝዳንት ሮሓኒ ወደ ሥልጣን መምጣት ስለመቻላቸው በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው። ራፍሳንጃኒ  በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተጣሉ ገደቦችን በአደባባይ የሚተቹ የሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ አቀንቃኞችን የሚያባርረውን መንግሥት የሚሸነቁጡ ተናጋሪ ሆነውም ነበር። ሁለት ጊዜ ለዳግም የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ተወዳድረው ያልተሳካላቸው ሰው ዓላማቸውን በማሳካቱም ረግድ ሁለት መልክ ነበራቸው።«ከፍ ያለ ሥልጣን በነበራቸው የመጀመሪያው አካባቢ ፖለቲካዊ ለውጥ እና ነፃነትን ያላስቀደመ የኤኮኖሚ ሞዴል ይከተሉ ነበር። በሒደት ግን ወደ የለውጥ ኃሳቦች መቅረብ ጀመሩ። በምንከተለው የፖለቲካ መርሕ ሙሉ በሙሉ ከዓለም ልንገለል አንችልም የሚል አቋም ያራምዱ ጀመር። እንደ አለመታደል ሆኖ ወደዚህ አቋም ሲደርሱ እጅግ ዘግይተው ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የፖለቲካ ኅይሉ አልነበራቸውም።»

ራፍሳንጃኒ ኃይለኛ ፖለቲከኛ ብቻ አልነበሩም። በኢራኗ የኬርማን ግዛት ከራፍሳንጃን ከተማ በጎርጎሮሳዊው 1934 ዓ.ም. ከባለጠጋ ገበሬ ቤተሰቦች የተወለዱት ራፍሳንጃኒ የግል ኃብት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። የኢራን ለውጥ ፈላጊዎች ራፍሳንጃኒን የሚወቅሱት በተቺዎቻቸው ላይ በወሰዷቸው እርምጃዎች ብቻ ሳይሆን ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር በነበራቸው የጠበቀ ግንኙነት ባካበቱት ኃብት ጭምር ነበር። ራፍሳናጃኒ ወግ-አጥባቂ ሆነው ከለውጥ ፈላጊዎቹ፤ የለውጥ ጠበቃ ሆነው ከወግ-አጥባቂዎቹ ሲቆራቆሱ ያረፉ ፖለቲከኛ ናቸው። ከአገሪቱ ልዕለ መሪ ጋር ሳይቀር ቅራኔ ውስጥ ገብተው ያውቃሉ። ወግ አጥባቂው ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አህመዲን ነጃድ የኢራን ፕሬዝዳንት በሆኑበት በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. የአገሪቱ ልዕለ መሪ ራፍሳንጃኒን ገሸሽ ያደረጉበት ጊዜ ነበር። በጊዜው የኢራን ልዕለ መሪ አሊ ኻሚኒ ለአህመዲን ነጃድ መወገናቸውን እንዲህ በግልጥ ተናግረው ነበር።

Tehran Präsident Akbar Hashemi Rafsanjani und Recep Tayyip Erdogan
ምስል picture alliance/dpa/AA/abaca/H. Sahin

«ራፍሳንጃኒን ሁሉም ያዉቁዋቸዋል።አብዮቱን ለራሳቸዉ የግል ጥቅም ማካበቻ አዉለዉታል ለመባሉ ምንም ማረጋገጪያ የለም።እኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከሳቸዉ ጋር የሐሳብ ልዩነት አለኝ።ይሕ ደግሞ እንግዳ አይደለም።ይሁንና ይሕን ልዩነት ሰዎች አጓጉል ሊተረጉሙት አይገባም።ከ2005 ምርጫ ጀምሮ ባሁኑ ፕሬዝዳትና በራፍሳንጃኒ መካካልም የአመለካከት ልዩነት አለ።ይሕ ያለ ነገር ነዉ።እነዚሕ ያመለካከት ልዩነቶች በተለያዩ መስኮች ይገለጣሉ።በዉጪ መርሕ፤ በማሕበራዊና በፍትሐዊ ጉዳዮች አፈፃፀም፥ እንዲሁም በባሕላዊ ጉዳዮችም ሊንፀባረቁ ይችላሉ።የአሕመዲነጃድ አስተሳሰብ እኔ ካለኝ ጋር ይቀራረባል።»

ምዕራባውያን ተንታኞች እና መገናኛ ብዙኃን የራፍሳንጃኒ ሞት የሚፈጥረው ክፍተት ግዙፍ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ኢራን ከሌሎች አገራት ጋር ያላት በወግ-አጥባቂዎቹ መርኅ እና አብዮታዊ ውጥን ብቻ እንዳይሆን እንደ ራፍሳንጃኒ የሚሞግት የለውጥ ጠበቃ አሊያም ለውጥ ፈላጊ በቅርብ ስለመኖሩ ጋዜጠኛዋ ሾራ አዛርኖሽ እንኳ እርግጠኛ አይደለችም።

«ብዙዎቹ ኢራናውያን ራፍሳንጃኒ በአንድ ሰው ብቻ አይተኩም የሚል እምነት አላቸው። ኢራን በኤኮኖሚ እና ፖለቲካው ዘርፍ ከሌሎች አገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማሻሻል የጀመሩት ጥረት ነበር። በአንድ ሰው ብቻ የሚተኩ አይመስልም። ምን አልባት በወቅቱ የኢራን ፕሬዝዳንት ዙሪያ በሚገኙ ሰዎች በቡድን ሊተኩ ይችላሉ።»

በ82 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ራፍሳንጃኒ ከቀድሞው የኢራን ልዕለ መሪ አያቶላህ ሩሖላህ ኾሜይኒ አጠገብ ለክብራቸው በተገነባ የመታሰቢያ አዳራሽ ውስጥ አርፈዋል። ሁለቱ የኢራን ፖለቲከኞች ታሪካቸው ስኬት እና ውድቀታቸው እንደ ማረፊያቸው ሁሉ ሲዘከርም ሆነ ሲብጠለጠል አብሮ ይሆናል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ