ሩስያ 11 000 ዜጎቿን ከግብፅ አስወጣች
እሑድ፣ ጥቅምት 28 2008ማስታወቂያ
እንዲሁ 2000 የሚጠጉ የብሪታንያ ሀገር ጎብኚዎች ከግብፅ ሻርም ኤል ሼህ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ዛሬ ተዘግቧል።ግብፅ ውስጥ ከደረሰው የሩስያ የአውሮፕላን አደጋ በኋላ ሩስያ የግብፅ ሙሉ በሙሉ በራራዎችዋን ላልተወሰነ ጊዜ በመሰረዟ ምክንያት 80,000 የሚጠጉ ሀገር ጎብኚ ዜጎቿ መመለሻ አጥተው ግብፅ ውስጥ ነበሩ። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በደረሰው አደጋ በአይሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 224 ተሳፋሪዎች በጠቅላላ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ጀርመን እና ሌሎች የምዕራብ ሀገራት የአደጋው መንስኤ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ሲል በሚጠራው ቡድን የተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ነው ሲሉ ያምናሉ። ግብፅ ውስጥ የሚገኘው የአሸባሪው ቡድን ለደረሰው አደጋ ኃላፊነት ቢወስድም የግብፅ ባለስልጣናት ምንም ማረጋገጫ የለም በሚል ውድቅ አድርገውታል። ቡድኑ ጥቃቱን የፈፀመው ሩስያ ሶርያ ውስጥ ለምታካሂደው የአየር ጥቃት አፀፋ እንደሆነ ቢገልፅም፤ አደጋውን እንዴት እንዳደረሰ አላሳወቀም።
ልደት አበበ
እሸቴ በቀለ