1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 11 2006

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፣ የጀርመን ቡንደስ ሊጋ፣ የስፔን ላሊጋ እና የጣሊያን ሴሪ አ የእግር ኳስ ግጥሚያ በዛሬው የስፖርት ጥንቅራችን ሰፋ ያለ ቦታ ተሰጥቷቸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን በተመለከተ ከአድማጮች የደረሱን አስተያየቶችን አካተናል። የአትሌቲክስ ውድድር ውጤትም የዝግጅቱ አካል ነው።

https://p.dw.com/p/1A3eg
ምስል Getty Images

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሣምንቱ ማሳረጊያ የእግር ኳስ ፍልሚያ የደረጃ ሠንጠረዡን በአንደኛነት እና ሁለተኛነት የተቆናጠጡት ሁለቱ ኃያል ቡድናት በጎል ተንበሽብው አሳልፈዋል። ከትናንት በስተያ መሪው አርሴናል መከረኛውን ኖርዊች ሲቲ 4 ለ 1 በሆነ ውጤት የጎል ጎተራ አድርጎ ሸኝቶታል። 17 ነጥብ ይዞ አርሰናልን በሁለት ነጥብ ርቀት የሚከተለው ቸልሲ በበኩሉ ካርዲፍ ሲቲን በተመሳሳይ 4 ለ 1 ውጤት አንገት አስደፍቶታል። ሊቨርፑል ከኒውካስል ጋር 2 ለ 2 በመውጣት ነጥብ ቢጥልም ከቸልሲ ጋር ልዩነቱ የግብ ብቻ ነው። ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ ዌስት ሐም ዩናይትድን 3 ለ 1 በማሸነፍ 16 ነጥብ ይዞ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ዩናይትድ ግን አሁንም አልቀናውም። ኦልትራፎርድ ላይ፤ በገዛ ሜዳው ከሳውዝ ሐምፕተን ጋር 1 ለ1 በመውጣት ነጥብ ለመጋራት ግድ ሆኖበታል።

Geflicktes Tornetz 18.10.2013 in Sinsheim
ምስል picture-alliance/dpa

ለ26 ዓመታት ከመንፈቅ በኦልትራፎርድ ማንቸስተር ዩናይትድን በድል ጎዳና የመሩት ጡረተኛው ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ተተኪያቸው ዴቪድ ሞይስን እንደምንም ብለህ ዋንጫ መጨበጥ አለብህ ሲሉ ተደምጠዋል። በዘመናቸው ለማንቸስተር ዩናይትድ 13 የእንግሊዝ ሊግ እና ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ለደረደሩት የማን ዩናይትድ የቀድሞው አሰልጣኝ የቡድናቸው አካሄድ ስጋት ላይ ሳይጥላቸው አልቀረም። ተተኪያቸው ግን እንደምንም ብለው ዋንጫ መጨበጥ አይደለም እንደምንም ነጥብ መያዝ የተሳናቸው ይመስላል።

ጭራሽ ባለፈው በዌስት ብሮሚች በሜዳቸው የመሸነፋቸው ነገር ከእንግዲህ ወደ ኦልትራፎርድ ብቅ የሚሉ ቡድናት ማንቸስተርን በሜዳው ለመግጠም የፍርሃት አይነጥላቸው እንዲገፈፍ አድርጓል እየተባለ ነው። በእዚህም አለ በእዚያ ዘንድሮ ማንቸስተር ዩናይድ ባካሄዳቸው 8 ተከታታይ ግጥሚያዎች በ11 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 8ኛ የመሆኑ ጉዳይ ደጋፊዎቹን ሳያሳስባቸው አልቀረም። ሰንደርላን ከስምንት ጨዋታዎች እንዳይቀርበት 1 ነጥብ ብቻ ይዞ የወራጅ ቀጣናው ግርጌ ላይ ተጋድሟል።

ፕሬሚየር ሊጉን ከትናንት በስትያ በ72ኛው ደቂቃ ኒውካስል ላይ ያስቆጠራትን ግብ ጨምሮ ዳንኤል ስቱሪጅ በ7 ግቦች እየመራ ይገኛል። የማንቸስተር ሲቲው ሰርጂዮ አጉዌሮ በ 6 ከመረብ ባረፉ ግቦች ይከተለዋል። የአርሰናሉ አሮን ራምሴይ እና የኒውካስል ዩናይትዱ ሎይች ሬሚ እያንዳንዳቸው አምስት፣ አምስ ግቦችን ሲያስቆጥሩ፣ የአርሰናሉ ኦሊቨር ጊሮድ በ4 ግቦች ይከተላቸዋል።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ እጅግ የሚገርም ክስተት፤ ምናልባትም የኢትዮጵያ እና ናይጀሪያ ግጥሚያ ላይ እንደተከሰተው አይነት አወዛጋቢ ሆኖም አስቂኝ ክስተት መከሰቱ አልቀረም። ወደ በኋላ ላይ እንመለስበታልን መጀመሪያ እስኪ የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ ውጤቶችን በአጭሩ እንቃኛቸው።

FIFA WM 2014 Europa Qualifikation 21.10.2013
ምስል Fabrice Coffrini/AFP/Getty Images

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትናንት ሽቱትጋርት ከሐምቡርግ ጋር ሶስት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ዎልፍስቡርግ አውስቡርግን 2 ለ 1 አሸንፏል። ከትናንት በስቲያ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሐኖቨርን 1 ለ0 ሲረታ፤ ቬርደር ብሬመን ከፍራይቡርግ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ሻልካ አይንትራኽት ብራውንሽቫይግን 3 ለ2 ሲያሸንፍ፤ ኑረንበርግ ከአይንትራኽት ፍራንክፉርት 1 ለ1 በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ሄርታ ቢ ኤስ ሲ ቦሩሲያ ሞንሽንግላድባህን 1 ለባዶ ሸኝቷል። የአውሮጳ ኃላይሉ ባየርን ሙንሽን ማይንስን 4 ለ አንድ አንቀጥቅጦ ልኮታል። ምንም እንኳን ማይንስ በ44ኛው ደቂቃ ሻውን ፓርከር ባስቆጠራት ግብ እየመራ ቢቆይም፤ ከእረፍት መልስ ግን ባየሮች ታጥሮ የቆየውን የማይንስን ክልል እንዳልነበር ረምርመውታል።

ለባየርን በ50ኛው ደቂቃ ሆላንዳዊው አርየን ሮበን ግብ ሲያስቆጥር፤ በ52ኛው ደቂቃ ላይ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ቶማስ ሙለር ከመረብ በማሳረፍ የባየርን ድል እውን እንዲሆን አስችሏል። በ69ኛው ደቂቃ ላይ ማሪዮ ማንቹክ ሶስተኛውን ግብ ለባየርን ሲያስቆጥር ግብ አዳኙ ቶማስ ሙለር በ82ኛው ደቂቃ ላይ የምርቃት ማሳረጊያዋን የምርቃት ግብ አስቆጥሮ ባየርን 4 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት እንዲያሸንፍ አስችሎዋል። ከረፍት በፊት የነበረው የጨዋታ ሁናቴ ለቶማስ ሙለር ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነበር።

«አዎ፤ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ማይንዞች በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ከኋላ ግጥም አድርገው ዘግተው ሲበዛ አስቸግረውን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽም ዘግተው ለመጫወት ሳይፈልጉ የቀሩ አልመሰለኝም። ግን ድንገት እኛ ጋ ነገሮች ተስተካከሉ።»

Fußball Manchester United Adnan Januzaj
ምስል picture-alliance/dpa

በነገራችን ላይ ሆፈንሀይም ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር አርብ ዕለት ያከናወኑት ግጥሚያ አስቂኝ ክስተት ተስተውሎበታል። ጨዋታዋን በመምራት ላይ የነበረው ባየር ሌቨርኩሰን የማዕዘን ምት ይሰጠዋል። እናም ከተፎካካሪው ቡድን ግብ በስተቀኝ በኩል የተላከችውን ኳስ የባየር ሌቨርኩሰኑ ሽቴፋን ኪስሊንግ በጭንቅላቱ ገጭቶ ወደ ግቡ ይልካታል። ሆኖም ኳሷ በበረኛው በስተቀኝ ከውጭ በኩል ያለውን መረብ ታካ በተቀደደ መረብ ወደ ውስጥ ሾልካ ትገባለች። ዳኛው ኳሷ በጓሮ አሳብራ መረቡ ውስጥ ዘው ማለቷን አላስተዋሉም። እናም ግቧን ለሌቨርኩሰኖች ያፀድቃሉ። የሆፈንሐይም ተጫዋቾች ኳሷን ይዘው እየተሯሯጡ ለዳኛው ቢያስረዱ፣ የተቀደደውን መረብ ቢያሳዩ ዳኛው ከብይናቸው ውልፍት አልል አሉ። እናም ባይር ሌቨርኩሰን በዚህች አሳሳች ግብ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል።

ብዙዎች እዚህ ጀርመን ውስጥ በጨዋታ ወቅት አወዛጋቢ ግብ መግባት አለመግባቱን የሚያጣራ የካሜራ ወይንም የግብ መቆጣጠሪያ ስራ ላይ አይውልም ሲሉ በመሞገት ላይ ናቸው። በርካቶች ግቧትክክለኛ ስላልሆነች ጨዋታው ሊደገም ይገባል ሲሉ የጀርመን የእግር ኳስ ሕግን በማጣቀስ በመሞገት ላይ ናቸው። ይሁንና ግን የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ ሕግ አንድ ጨዋታ ሊደገም የሚችለው በአየር ንብረት ምክንያት ቸዋታውን መቀጠል ሳይቻል ሲቀር ወይንም ደግሞ ተጨዋች አለያም ዳኛ ቡሙስና ሲጠረጠሩ እንደሆነ ይጠቅሳል።

ይህች በሆፈንሐይም ላይ የደረሰች በደል ምናልባትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድ ን ናይጀሪያ ላይ አግብቶ የተከለከለውን ግብ ያስታውሳል። እስኪ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ከናይጀሪያ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ በተመለከተ ስልክ ደውለን እንድናነጋግራቸው በአጭር መልዕክት መቀበያ ስልካችን በ 49 17 22 66 69 44 የስልክ ቁጥራቸውን ከላኩልን አድማጮቻችን መካከል የሁለቱ አስተያየት።

አሁን አጠር አጠር አድርገን ስለ ስፔን ላሊጋ፣ ጣሊያን ሴሪ ኣ የእግር ኳስ ግጥሚያ ውጤቶች እና አትሌቲክስ እናቀርብላችኋለን። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ቅዳሜ ዕለት ከአሳሱና ጋር ባዶ ለባዶ ቢለያይም በ25 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን በመምራት ላይ ይገኛል። አትሌቲኮ ማድሪድ በኢስፓኞላ 1 ለምንም ተረትቶም ቢሆን በ24 ነጥብ ሁለተኛ ሲከተል፤ ማላጋን ቅዳሜ ዕለት 2 ለ ባዶ ያሰናበተው ሪያል ማድሪድ በ22 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን በሶስተኛነት ይዟል።

UEFA Champions League Fußballspiel Real Madrid vs. FC Kopenhagen
ምስል Denis Doyle/Getty Images

በጣሊያን ሴሪኣ ደግሞ ሮማ በ24 ነጥብ አንደኛ፣ ናፖሊ በ19 ነጥብ ደረጃ ሰንጠረዙ ላይ በሁለተኛነት ይገኛሉ። ጁቬንቱስ በተመሳሳይ 19 ነጥብ ሶስተና ሲሆን፤ ትናንት በፊዮሬንቲና 4 ለ 2 መሸነፉ አልቀረም። ትናንት አትላንታ ላሲዮን፣ ጄኖዋ ቺቮ ቬሮናን፣ እንዲሁም ሳምፕዶሪኢ ሊቮርኖን 2 ለ 1 አሸንፈዋል። ፓርማ በሄላስ 3 ለ 2 ተረትቷል። ሳሱሎ ቦሎኛን 2 ለ 1 ሊያሸንፍ ችሏል።

ነገ እና ከነገ ወዲያ በሚካሄዱት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች በተለይ የጀርመን ቡድኖች ከእንግሊዞቹ፤ እንዲሁም የስፔን ኃያላኖች ከጣሊያኖቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታዎች በጉጉት ይጠበቃሉ። በተለይ በነገው ዕለት የእንግሊዙን ፕሬሚየር ሊግ እየመራ በሚገኘው አርሰናል እና በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ቀደም ሲል ሁለተኛ ወጥቶ ባጠናቀቀው ዶርትሙንድ መካከል የሚከናወነው ግጥሚያ በእጅጉ ይጠበቃል። የቼልሲ እና ሻልካ ቀጠሮም በእንግሊዞች እና ጀርመኖች ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ ነው። የሁለቱም ጨዋታዎች ምሽት ለአራት ዕሩብ ጉዳይ ነው የሚካሄዱት። የስፔኑ ባርሴሎና ከጣልያኑ ኤሲ ሚላን እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ከጁቬንቱስ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቁ ናቸው።

ኢትዮጵያ ሐዋሳ ውስጥ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የማራቶን ውድድር ሲያሰናዳ፤ በቤጂንጉ ዓለም አቀፍ ማራቶን ኢትዮጵያዊው ታደሰ ቶላ ለ27 ዓመታት ተይዞ የቆየ ክብር ወሰን ሊሰብር ችሏል። ታደሰ ቶላ በጃፓናዊው ሯጭ ታይሱኬ ኮዳማ እጎአ በ1986 ተይዞ የቆየውን ክብር ወሰን በ19 ሰከንድ በማሻሻል ሊያሸንፍ ችሏል። ታደሰ 2 ሠዓት ከ 07 ደቂቃ ከ 16 ሰከንድ ነው ያስመዘገበው።

በፌስ ቡክ አድራሻችን የተለያዩ አስተያየቶቻችሁ ደርሰውናል። ለአብነት ያህል ምርጡ ቡድናችን ቢሸነፍም ምንም ማለት አይደለም፤ በቡድናችን ኮርተናል፣ ቡድናችን የላቀ ጨዋታ ነው ያሳየው ፣ የአዳነ መቀየር ናይጀሪያዎች ክፍተት እንዲያገኙና ግብ እንዲያስቆጥሩ አድርጎዋል፣ የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችን አስፍራችሁልናል። ለአስተያየታችሁ በጠቅላላ ከልብ እናመሠግናለን። አስተያየቶቻችሁን በአጭር መልዕክት መቀበያም ሆነ በመደበኛው ስልካችን፣ በፌስ ቡክ አድራሻችን፣ በኢሜል አለያም በደብዳቤ መላካችሁን ቀጥሉበት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ