1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምሥራቅ አፍሪቃ፥ የዩርኤዥያ ዝርያ

ረቡዕ፣ የካቲት 16 2008

በምሥራቅ አፍሪቃ የሚገኙ የዘመኑ ነዋሪዎች ሩብ ያኽል ደማቸው ከ4000 ዓመታት በፊት ከአውሮጳና እስያ ወደ አፍሪቃ መምጣታቸው ከሚነገርላቸው ዩሬዥያ ገበሬዎች የተቀዳ ነው የሚል የተሻሻለ ጥናት ሰሞኑን ከወደ ኬምብሪጅ ወጥቷል። ጥናቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘ ጥንታዊ ቅሪተ-አካልን ከሌሎች አፍሪቃውያንና አውሮጳውያን ዘረ-መል ጋር አመሳክሯል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1I1If
Symbolbild Grundsatzurteil USA zur Patentierung menschlichen Erbguts
ምስል Fotolia/majcot

ምሥራቅ አፍሪቃ፥ የዩሮዥያ ዝርያ

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ ነዋሪዎች ዩሬዥያ የተባሉ ከሺህ ዓመታት በፊት ከአውሮጳ እና እስያ አካባቢ የፈለሱ ገበሬዎች ደም አለባቸው የሚል የተሻሻለ ጥናት ሰሞኑን ቀርቧል። ቀደም ሲል የነበረው ጥናት ከ3,000 ዓመት በፊት ወደ አፍሪቃ የፈለሱ የዩሬዥያ ገበሬዎች ዘረ-መል (genetics) አሻራ ከምሥራቅም አልፎ እስከ ምዕራቡ የአህጉሪቱ ክፍል ይደርሳል የሚል ነበር። ያ ትክክል አይደለም ተብሏል። ኾኖም ተሻሽሎ በቀረበው አዲስ ጥናት መሠረት የምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ ነዋሪዎች ሩብ ያኽል ምንጫቸው የተቀዳው ከዩሬዢያ ገበሬዎች ነው ሲሉ ከብሪታንያ የኬምብሪጅ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል። ጥናታቸው በዋናነት የተከናወነውም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሞጣ ዋሻ ውስጥ የተገኘ ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ ቅሪተ-አካል ላይ መኾኑ ተገልጧል።

ሞጣ ዋሻ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የጋሞ ከፍታማ ስፍራዎች ከባሕር ጠለል 1,963 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል። በዚህ አካባቢ ከብሪታንያ የመጡ የኬምብሪጅ ተመራማሪዎች ባሕል እና የእህል ዘሮች ላይ ጥናት ያከናውኑ ነበር። በጥናታቸው ሒደት ግን ድንገት አንድ አስደማሚ ነገር ያገኛሉ፤ 4,500 ዓመት ያስቆጠረ ያልፈራረሰ የራስ ቅል። ስለ ሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ አጥኚው ዶክተር ብርሃኔ አስፋው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጨንቻ የተባለው አካባቢ ሞጣ ዋሻ ውስጥ የተገኘው ቅሪተ-አካል ለየት የሚያደርገው የራስ ቅሉ ውስጥ ዘረ-መል ስላለበት ነው ብለዋል።

ቅሪተ-አካሉ የተገኘበት የሞጣ ዋሻ 14 ሜትር ስፋት እና 9 ሜትር ጥልቀት አለው። ዋሻው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ5295 ዓመተ-ዓለም ጀምሮ እስከ 300 ዓመተ ዓለም ድረስ በተለያዩ ሰዎች ጥቅም ላይ ውሎ እንደነበረም አጥኚዎቹ ደርሰንበታል ብለዋል። እውስጡ በሚገኝ መካነ-መቃብር የተገኘው የአንድ ሰው ቅሪተ-አካል በዋሻው ስም «ሞጣ» የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ቅሪተ-አካሉ ብሪታንያ ወደሚገኘው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተልኮ ሣይንሳዊ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ በግምት 5,500 ዓመት ዕድሜ እንዳለውም ተገልጧል።

የዘመናዊው ሰው ማለትም ሆሞሳፒየንስ ራስ ቅል
የዘመናዊው ሰው ማለትም ሆሞሳፒየንስ ራስ ቅልምስል picture-alliance/dpa/J. Kalaene

በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር አንድሪያ ማኒካ በበኩላቸው «ከአራት ሺህ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታ ይኖር የነበረውን የዚኽን ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ዘረ-መል ከሌሎች ሰዎች ዘረ-መል ጋር በማመሳከር ማጥናት» እንዳለባቸው መገንዘባቸውን ገልጠዋል። እናም ጥናታቸውን ያከናወኑት «ይኽን ዘረ-መል በአኹኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር፤ እንዲሁም ከሌሎች አፍሪቃ ውስጥ ካሉ ነዋሪዎች ጋር በማነፃጸር» ነበር። ከዚያም ባሻገር «ከዘመናዊ የዩሬዢያን ነዋሪዎች ጋር እንዲሁም ገበሬ ከመኾናቸው በፊት በአደን ተግባር ከተሠማሩ ጥንታዊ የአውሮጳውያን ዘረ-መል ጋርም» እንዳመሳከሩት ገልጠዋል።

በተደረገው ምርምርም «ሞጣ» የሚል ስያሜ ያገኘው ቅሪተ አካል በአኹኑ ዘመን በዛው ደቡባዊ ኢትዮጵያ አካባቢ ከሚገኙት አሪዎች ጋር ተቀራራቢነት አለው ተብሏል። የአፍሮ እስያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ውስጥ የሚመደቡት የናይሎ ሰሐራ ቤተሰብ የኾኑት ጉሙዞችም ከሞጣ ዘረ-መል ጋር ቅርርብ እንዳላቸው አጥኚዎቹ ተናግረዋል። ቅርርቡ አሪዎች ከሞጣ ጋር ያላቸውን ያኽል ግን አይደለም፤ እንደውም እጅግ ያንሳል ተብሏል። ሞጣ መካከለኛው ታንዛንያ ውስጥ ከሚኖሩት እና ቁጥራቸው 40.000 ከሚገመተው ሳንዳዌዎች ጋርም አነስ ያለ ግንኙነት እንዳለው ተደርሶበታል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል። ሞጣ ከአሪዎች ጋር ብቻ ሣይኾን ጀርመን እና ቱርክ አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር «የሚጋሩት የዘር ባሕርያት» መገኘቱን ዶክተር ብርሃኔ አስፋው ጠቅሰዋል።

የምርምሩ ሙሉ ዘገባ ሣይንሳዊ የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበት (sciencemag.org) የተሰኘው ድረ-ገጽ ላይ ይገኛል። ዘገባው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ነገዶች ዘረ-መል ከሞጣ ጋር ያለው መቀራረብ ምን ያኽል እንደኾነ በቁጥር እና በመሥመር አስፍሯል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪቃ ነዋሪዎች ከዩሬዥያዎች ጋር ያላቸው ዘረ-መል መመሳሰል አንዳንዴ ሩብ ያክል ይኾናል ተብሏል። ዩሬዢያዎች ከ70,000 ዓመት በፊት ከአፍሪቃ ወደ እስያ የፈለሱት ነዋሪዎች እንደኾኑም ተጠቅሷል። እነዚህ ዩሬዥያን ግን በርካታ ሺህ ዓመታት ቆይተው ወደ አፍሪቃ ተመልሰዋል እንደጥናቱ ዘገባ።

«እናም ከአራት ሺህ ዓመት በፊት ዩሬዢያዎች ከምሥራቅ አፍሪቃ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እየጨመረ በመሄዱ ከፍተኛ ዘረ-መል ፍሰት ሊከናወን ችሏል። ያም ማለት በአኹኑ ዘመን የሚገኙት የምሥራቅ አፍሪቃ ሰዎች ዘረ-መል ሩብ ያኽል መጠኑ ወደ አፍሪቃ ከተመለሱ ዩሬዥያዎች የተገኘ ነው።» ሲሉም የኬምብሪጁ ተመራማሪ ዶ/ር አንድሪያ ማኒካ።

ዘረ-መል ምርመራ በቤተ-ሙከራ ውስጥ
ዘረ-መል ምርመራ በቤተ-ሙከራ ውስጥምስል AP

ዘመናዊው ሰው ከምሥራቅ አፍሪቃ የወጣው ከ70,000 ዓመታት በፊት እንደኾነ ሣይንስ ይጠቅሳል። ግብርናን የጀመረውም ከ80 ሺህ ዓመታት በፊት ሲኾን፤ አናቶሊያ እና ኢራን በሚያካልለው ግዛት በተለይ ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ እንደኾነ ይነገራል። አናቶሊያ አብዛኛው የቱርክ ግዛትን የሚሸፍን አካባቢ መጠሪያ ነው። አካባቢው በኦቶማን ግዛት እና ቀደም ብሎ በሴልጁክ ሥርወ-መንግሥት ቁጥጥር ስር ከመውደቁ በፊት መግባቢያው የግሪክ ቋንቋ ነበር።

በእርግጥም የሰው ልጆች ከጥንት ጀምሮ ከአፍሪቃ ወጥተው ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንደተሰማሩ በሌላ ጊዜ ደግሞ ተመልሰው ወደ አፍሪቃ ይመለሱ እንደነበር ጥናቱ አመላክቷል። ለዚህ ደግሞ ከአራት ሺህ ዓመት በፊት ወደ አፍሪቃ የተመለሱት ዩሬዢያዎች ከሰባ ሺህ ዓመት በፊት ከአፍሪቃ የወጡ መኾናቸው መገለጡ ነው።

ዶ/ር አንድሪያ ማኒካ ሲያብራሩ፦ «በጥንታዊው ኢትዮጵያዊ ዘረ-መል ላይ የተደረገው ጥናት በሦስት እና አራት ሺህ ዓመታት ግድም የተከናወነ እጅግ በጣም የቅርብ ጊዜ ምርምር ነው። ከእኛ ዘመን ጋር ይበልጥ ቀረብ ይላል። እናም ዘረ-መል ጥናቱ ያመላከተን ዩሬዥያዎች ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ ባደረጉት እንቅስቃሴ ወይንም ደግሞ እጅግ በገፍ በመፍለሳቸው በዚያን ወቅት ጥሎት ያለፈው ዘረ-መል አሻራ ከፍተኛ መኾኑን ነው» ብለዋል። የኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጥናት እንደሚያመላክተው ከኾነ ከአራት ሺህ ዓመት በፊት ይኖር የነበረው «ሞጣ» ቡናማ ዐይኖች እና ጥቁር ጸጉር እንደነበረው ተደርሶበታል ተብሏል። ጥናቱ ከአፍሪቃ 40 ከአውሮጳ እና ከእስያ ደግሞ 81 ነገዶችን በጥቅሉ የ250,000 ሰዎችን ዘረ-መል ከሞጣ ጋር በማመሳከር የተቃኘ ነው።

ሞጣ ዋሻ ውስጥ ከጥንታዊው ቅሪተ-አካል በተጨማሪ ከድንጋይ ዘመን መገልገያ መሣሪያዎች ጋር ተመሳሳይ የኾኑ የድንጋይ ቁሶች ተገኝተዋል። መገልገያ መሣሪያዎቹ ከጥቁር እምነበረድ፣ በእሳተ-ጎመራ ቀልጦ ከረጋ አብረቅራቂ ድንጋይ፣ እንዲሁም ከጥቁር ድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩ ናቸው። ዘመናዊው ሰው ምንጩ ምሥራቅ አፍሪቃ እንደኾነ ተመራማሪዎች ዛሬም ይመሰክራሉ። «እንደሚመስለኝ በአኹኑ ወቅት የመጀመሪያው ዘመናዊው ሰው ቅሪተ-አካል የተገኘው ምሥራቅ አፍሪቃ ውስጥ ለመኾኑ ሁላችንም ሙሉ ለሙሉ እንስማማለን። እናም ያ የእኛ ምንጫችን ከእዚያ ሊኾን እንደሚችል አመላካች ነው» ሲሉም ዶ/ር አንድሪያ ማኒካ ተናግረዋል።

የዘመናዊው ሰው ማለትም ሆሞሳፒየንስ ራስ ቅልና አካል
የዘመናዊው ሰው ማለትም ሆሞሳፒየንስ ራስ ቅልና አካልምስል picture-alliance/dpa

ይኽ ጥናታዊ ግኝት ቀደም ሲል ይታመንበት የነበረውን ምዕራብ ዩሬዥያ ገበሬዎች ከምሥራቅ አፍሪቃም አልፈው እስከ ምዕራብ አፍሪቃ ድረስ ዘልቀዋል የሚለውን መላ ምት አፍርሶታል። በተለይ በምዕራብ አፍሪቃ የሚገኙ የዮሩባ ነገዶች እና ኮንጎ የሚገኙ ምቡቲዎች ላይ በተደረገው ዘረ-መል ጥናት መሰረት ምዕራብ ዩሬዥያ ዘር የላቸውም ተብሏል። ምቡቲዎች ኮንጎ ውስጥ የሚገኙ በቁመታቸው እጅግ አጫጭር የኾኑት ፒግሚዎች ነገድ መጠሪያ ነው። በዚህም አለ በዚያ ግን ይኽ ግኝት በዓለም ላይ የሚገኘው የሰው ልጆች ዘር ዞሮ ዞሮ አንድ መኾኑን አመላካች ነው ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ