1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜልያ-የሶርያውያኑ እስር ቤት

ሐሙስ፣ ኅዳር 2 2008

ከሞሮኮ ጋር የምትዋሰነው እና በኢቤሪያን የባህር ወሽመጥ የምትገኘው ሜልያ በሰሜን አፍሪቃ ትገኝ እንጂ የስጳኝ ከተማ ነች። ከተማዋ ለስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ወደ አውሮጳ ለመግባት የምትመረጥ በርም ሆናለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በርካታ ሶርያውያን ወደ አውሮጳ ድንበር ለመድረስ ባህር ከማቋረጥ ይልቅ ሜልያን ይመርጣሉ።

https://p.dw.com/p/1H4qF
Spanien syrische Flüchtlinge in Melilla
ምስል DW/G. Hedgecoe

[No title]

ሜልያ ጥድፊያና ሁካታ የበረከተባት ሜልያ ለስጳኝና ሞሮኮ ብቻ ሳይሆን ለአውሮጳና አፍሪቃም የድንበር ከተማ ነች። በድንበሩ አቅራቢያ በሞሮኮ ግዛት ውስጥ በርካታ የሶርያ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ወደ አውሮጳ ለመሻገር በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ስሙን መናገር የማይፈልገው ሶርያዊ ወደ ሜልያ የተጓዘው ህገ-ወጥ ፓስፖር ከገዛ በኋላ ነበር። ባለቤቱና ልጁ ደግሞ በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሜልያ ደርሰዋል።
«ባለቤቴና ልጄ በመኪና ውስጥ ተደብቀው ነው እዚህ የደረሱት። ለመተንፈስ ተቸግረው ነበር። በርካታ ችግሮችን አሳልፈዋል። የአምስት አመቱ ልጃችን ከድንበር አቅራቢያ ነቅቶ እንዳያስቸግር የእንቅልፍ መድሃኒት ተሰጥቶት ተኝቶ ነበር። ባለቤቴ ደግሞ ከመንገደኞች መቀመጫው ላይ ከልጄ ጀርባ ተኝታ ነው የመጣችው።»

ሜልያ በፍጹም የስጳኝ ከተማ አትመስልም። በከተማዋ የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚናገሩት የአረብኛ ቋንቋ አብዝቶ ይሰማል። በከተማዋ የሚታዩት ሕንፃዎች ንድፍ እና ባህልም በፍጹም የተለየ ነው። ነገር ግን ከተማዋ የስጳኝ ግዛት ናት። የከተማዋ ልዩነት በርካታ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች መምጣታቸውን ይጠቁማል።

Spanien syrische Flüchtlinge in Melilla
ምስል DW/G. Hedgecoe

«እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ሶርያውያን በስጳኝ መቆየት እንፈልጋለን። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉን። የአየር ሁኔታው አንዱ ነው አገሪቱም ሶርያን ትመስላለች። እንደ ሶርያውያን ለእኛ የተሻለው ቦታ ስጳኝ ነው። ምን አልባት ወደ ማድሪድ ከተማ ስንደርስ አቋማችንን እንለውጥ ይሆናል። እናም ያንን ለማየት እየጠበኩ ነው።»

በየቀኑ ሁለት ወይም ሶስት ሶርያውያን ከሞሮኮ ወደ ስጳኝ ድንበር እንደሚያቋርጡ ይታመናል። ከልጁና ባለቤቱ ጋር እንደመጣው ሶርያዊ ሁሉ የአውሮጳ ህብረት ፓስፖርት ገዝተው አሊያም ተከራይተው ወደ ስጳኝ የሚሻገሩትን ሰዎች የሞሮኮ ፖሊሶች መለየት አይችሉም። ፕሮዲን የተሰኘው የስጳኝ የግብረ-ሰናይ ድርጅት ቃል አቀባይ ዮዜ ፓላዞን ሶርያውያኑ ወደ ስጳኝ የሚያቋርጡባቸው ሌሎች መንገዶች መኖራቸውን ይናገራሉ።

«ስጳኝ ህጋዊ ያልሆነ የድንበር ስምምነት ከሞሮኮ ጋር ደርሳለች። የተጻፈ ስምምነት አይደለም። ምክንያቱም ህገ-ወጥ ይሆናል። እናም ድንበር ማቋረጥ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ተወስኗል። በየቀኑ ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ሰዎች ተመርጠው ወደ ስጳኝ ይሻገራሉ። ምርጫው የሚካሄደው ሶርያውያኑ በሚከፍሉት የገንዘብ መጠን ነው።»

የሞሮኮ ፖሊስ ወደ ስጳኝ ማቋረጥ የሚፈልጉት ሶርያውያንን እስከ 3,000 ዩሮ እንደሚያስከፍሉ ይናገራሉ። ይሁንና አንድ ጊዜ በስጳኝ ከደረሱ በኋላ በርካታ ችግሮች ይገጥሟቸዋል። ሆዜ ፓላዞን«ሶርያዊ ብሆን ኖሮ በስጳኝ አልቆይም ነበር። የመጀመሪያው ምክንያት ስጳኝ አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ የላትም። የመኖሪያ ፈቃድ አሰጣጡም ዘገምተኛ ሲሆን እርዳታው አስከፊ ነው። የስደተኞች የእርዳታ አሰጣጥ ስርዓቱ ለረጅም አመታት ባለበት ተገትሮ ቀርቷል። በበርካታ የስጳኝ ከተሞች የሶርያ እና ፍልስጤም ስደተኞች በፓርኮች ውስ ነው የሚተኙት። ምንም አይነት እገዛ የሚያደርግላቸው የለም።» ሲሉ ይናገራሉ።

በሜልያ የስደተኞች ጣቢያ የመኖሪያ ወይም የመቆያ ፈቃዳቸው እስኪታይ ድረስ ለሁለት ወራት ስደተኞች ምግብና የመለያ እገዛ ያገኛሉ። መጠለያ ጣቢያው ለ500 ሰዎች ታቅዶ ቢገነባም አሁን ከሶስት እጥፍ የሚልቁ ስደተኞች ይኖሩበታል። ሁሉም ማለት ይቻላል ሶርያውያን ናቸው። የ23 አመቱ አሲፍ ዲዋራ ባለፈው አመት መገባደጃ ነበር ሶርያን ጥሎ የወጣው። ከሶስት ወራት በፊት ደግሞ በሞሮኮ ፓስፖርት አማካኝነት ወደ ሜልያ ተሻገረ።

Spanien syrische Flüchtlinge in Melilla
ምስል DW/G. Hedgecoe

«ቤተሰቦቼ ያሉት ጀርመን ነው። በዚያ ትምህርቴን መማር እፈልጋለሁ። እናቴ ያለችው እዚያ ነው። ቤተሰባችንን በሙሉ ከሶርያ ወደ ጀርመን ማምጣት እንሻለን። በዚህ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ካየሁትና ካሳለፍኩት አኳያ በዚህም ይሆን ስጳኝ ውስጥ በመሆኔ ደህንነት አይሰማኝም። ከእዚህ ይልቅ በሶርያ ደህንነት ይሰማኝ ነበር።

አሲፍ እንደ ሌሎች ሶርያውያን ሁሉ ጉዳዩ በመዘግየቱ ተሰላችቷል። አንድ ጊዜ ከስደተኞች መጠለያ ጣቢያው ከወጣ «ቀዩ -ወረቀት» ተብሎ የሚጠራ ማስረጃ ይሰጠውና በመላ ስጳኝ በነጻነት መንቀሳቀስ ይችላል። ይሁንና የስጳኝ ባለስልጣናት በህጋዊ መንገድ መምጣቱን እስኪያረጋግጡ ድረስ ከስጳኝ መውጣት አይፈቀድለትም። ያ ደግሞ ሌላ 18 ወራት ይወስዳል።


ጊ ሄጅኮ/ እሸቴ በቀለ


አርያም ተክሌ