1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እና አዲሱ ሁከት

ቅዳሜ፣ መስከረም 22 2008

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተቀሰቀሰው አዲሱ ሁከት ከጥቂት ጊዚያት በኋላ አጠቃላይ ምርጫ ልታካሂድ በዝግጅት ላይ የነበረችውን ሃገር እአአ በ2013 ዓም ወደተካሄደው ዓይነቱ የርስበርስ ጦርነት እንዳይመልሳት አስግቶዋል።

https://p.dw.com/p/1GhrP
Zentralafrikanische Republik Proteste und Gewalt in Bangui
ምስል picture-alliance/AA/H.C. Serefio

ትኩረት በአፍሪቃ፤ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እና አዲሱ ሁከት

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መዲና ባንጊን አዲስ የጥቃት ማዕበል አስጨንቋታል። በሙስሊሞች እና በክርስትያኖች መካከል በተነሳው አዲሱ ሁከት ቢያንስ 40 ሰዎች ሞተዋል፣ በብዙ ሺህ የሚገመቱም ተፈናቅለዋል። ሁከቱ የተቀሰቀሰው በባንጊ በብዛት ሙስሊሞች በሚኖሩበት « ፒ ኬ 5 » በሚል መጠሪያ በሚታወቀው ሰፈር ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ አንድ ሙስሊም የታክሲ ሾፌር አንገቱ ታርዶ በተገኘበት እና ሙስሊሞቹ በመዲናይቱ የክርስትያኖች ሰፈሮች ላይ አፀፋ ጥቃት በወሰዱበት፣ እንዲሁም፣ ክርስትያኖች የፀረ ባላካ ሚሊሺያዎችም ሕዝቡን ለዓመፅ በቀሰቀሱበት ጊዜ ነው።  

ይህን ተከትሎ የሃገሪቱ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚደንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛ ለተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ለመሳተፍ ከሄዱባት ኒው ዮርክ፣ ዩኤስ አሜሪካ ጉዟቸውን አቋርጠው መመለስ ግድ ሆኖባቸዋል። በመዲናይቱ ባለፈው ሰኞ ሰልፈኞች ፕሬዚደንቷ ስልጣናቸውን እንዲለቁ በመጠየቅ አደባባይ ወጥተዋል። በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ አጠቃላይ ምርጫ እአአ በጥቅምት እና በህዳር ወር እንዲካሄድ ታቅዶ ነበር፣ ይሁንና፣ አሁን በቀጠለው ሁከት የተነሳ ምርጫው ወደ ሌላ ጊዜ እንደሚተላለፍ ነው የሃገሪቱ ባለስልጣናት እና በዚያ የተሰማራው በምሕፃሩ «ሚኑስካ» የተባለው የተመድ ጓድ ሰላም አስከባሪ ጓድ መሪ ኤርቬ ላድሱ ያስታወቁት። በሙስሊሞች እና በክርስትያኖች መካከል በሃገሪቱ ይህን መሳይ ግጭት ሲነሳ ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም፣ አዲሱ ሁከት በሃገሪቱ እርቀ ሰላም ለማውረድ የተጀመረውን ጥረት መና እንዳያስቀረው ማስጋቱን ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው ለውዝግቦች የመፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርበው በምህፃሩ «አይ ሲ ጂ» በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ድርጅት ተንታኝ ቲቦ ለሱወር ገልጸዋል።

Catherine Samba-Panza
ምስል Reuters

« ባለፉት ቀናት የተከሰቱት ግጭቶች ሁሉ ያካባቢ ውጥረቶች መዲናይቱ ባንጊ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ አካባቢዎችም አሁንም እንደተካረሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ። ይህም ባንድ ወቅት በ«ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ» ውጥረቱ ረግቦዋል ብሎ አስቦ ለነበረው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠንካራ መልዕክት ነው የሚያስተላልፈው። ይህ በጣም አሳዛኝ ማስታወሻ ነው። »

በሃገሪቱ በተቀናቃኞቹ ሙስሊም የሴሌካ ዓማፅያንን እና በክርስትያኖቹ ፀረ ባላካ ሚሊሺያ መካከል ግጭቱ ከቀጠለ ወዲህ ሙስሊሞቹን እና ክርስትያኖች ለመለያየት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ሰሞኑን ከታየው ግድያ ብዙው የተፈፀመው ግን በተለይ በባንጊ በብዛት ሙስሊሞች በሚኖሩበት « ፒ ኬ 5 » በሚል መጠሪያ በሚታወቀው ሰፈር ነው። በሃገሪቱ የፀጥታው ሁኔታ መረጋጋት እስካልተረጋጋ ድረስ ይህ ዓይነቱ ግድያ ማቆሙ አጠራጣሪ መሆኑንን ቲቦ ለሱወር አስታውቀዋል።

« እንደምታውቀው፣ ፀጥታ እስከሌለ ድረስ እርቀ ሰላም ሊወርድ አይችልም። እና በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተሰማሩት የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ወታደሮች በዋነኝነት ሊወስዱት የሚገባው ርምጃ ሲቭሉን ሕዝብ መከላከል እንደሚችሉ በግልጽ የሚያሳዩበት ድርጊት መሆን አለበት ብየ አስባለሁ። በተለይም፣ በባንጊ በተበታተኑ ሰፈሮች የሚኖሩትን እና በሰላም አስከባሪው ጓድ ወታደሮች በቂ ከለላ እንዳልተደረገላቸው የሚሰማቸውን ሙስሊሞች መከላከል ይኖርባቸዋል። ሰላም አስከባሪዎቹ የስልጣኑን ሚዛን በመቀየር ልንከላከላችሁ እንችላለን የሚለውን ስሜት ሊፈጥሩ ይገባል። »

Zentralafrikanische Republik Christliche Militzen in Nanga Boguila
ምስል SIA KAMBOU/AFP/Getty Images

በባንጊ ሁለቱን ተቀናቃኝ ወገኖች ለመለያየት የሚደረገው ጥረት ግን አዎንታዊነቱ አሁንም እንዳጠያየቀ ነው። በዚሁ ጉዳይ ትክክለኛ መሆን አለመሆን ላይ በሃገሪቱ መንግሥት እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መካከል ባንድ ወቅት ብዙ ክርክር እንደተካሄደ ይታወሳል። የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መንግሥት የሙስሊሙን ህብረተሰብ በባንጊ ማቆየት ቢከራከርም፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰው ሕይወት ማትረፍ እንደሚበልጥ ነው ያስታወቀው። እና በ«ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ» የተሰማሩት ከ10,000 የሚበልጡ ሰላም አሰከባሪዎች የሙስሊሙን ህብረተሰብ አባላት በተለያዩ ሰፈሮች በማስፈር የደህንነቱን ዋስትና ማረጋገጥ ለምችሉበት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ለውዝግቦች መፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርበው የዓለም አቀፍ ድርጅት ተንታኝ ቲቦ ለሱወር ጠቁመዋል። እንደ ለሱወር አስተያየት፣ የሃገሪቱ መንግሥት እአአ የ2013 የርስበርስ ጦርነትን ተከትሎ የፀጥታውን ሁኔታ እስካሁን አስተማማኝ ያላደረገበት ሁኔታ አንዳንድ የ«ማአሬ» ዜጎች የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት ስልጣናቸውን እንዲለቁ በመጠየቅ አደባባይ እንዲወጡ መገፋፋቱ የተጠበቀ ነው።

« እንደማስበው፣ የአለመረጋጋቱ ሁኔታ አሁንም መቀጠሉን መኖሩን ሊረዱት ያልቻሉ አንዳንድ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጣቸው ገንፍሎ አደባባይ ቢወጡ አያስገርምም። ግን፣ እዚህ ላይ የአደባባዩን ተቃውሞ የመሩት አንዳንዶቹ ሰዎች የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ እንዳላቸው ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው። እነዚሁ ግለሰቦች ከአንዳንዶቹ የታጠቁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው። እና ፕሬዚደንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛ ለተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ኒው ዮርክ በነበሩበት ጊዜ ከስልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ ተቃውሞ መካሄዱ እንዲያው ያጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። የፖለቲካ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ይችሉ ዘንድ በባለስልጣናቱ ላይ ግፊት ለማሳረፍ የተጠቀሙበት ስልት ነው። »

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መዲና ባንጊ ባለፈው ሰኞ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት በ«ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ» የተሰማራው በምሕፃሩ «ሚኑስካ» የተባለው የተመድ ጓድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ የሶስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በጓዱ ላይ ብርቱ ወቀሳ ከማሰንዘሩን ከማስወቀሱ ሌላ ተልዕኮውን እንዳያከሽፈው የሃገሪቱ ዜጎች ሰግተዋል፣ ቲቦ ለሱወር ይህንኑ አባባል ባይጋሩትም፣ ሰላም አስከባሪዎቹ የሕዝቡን እምነት ለማግኘት ብዙ መስራት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።

Zentralafrikanische Republik UN Friedenstruppe in Bangui
ምስል picture-alliance/AA/H.C. Serefio

« የ«ሚኑስካ» ተልዕኮ የሚከሽፍ አይመስልኝም። ግን፣ ሰላም አስከባሪዎቹ ሕዝብ ላይ ተኩስ ከመክፈት በመቆጠብ፣ ወንጀለኞቹን፣ የኃይሉን ተግባር የሚያስፋፉትን ሚሊሺያዎች ማሰር ይኖርባቸዋል። ይህን ካላደረጉ ፣ ሕዝቡን ከታጣቂ ቡድኖች ጥቃት መከላከል እንደሚችሉ ካላሳዩ፣ ሕዝቡ በአንፃራቸው ጥላቻ ያድርበታል። በባንጊ የሚኖሩ የ«ማአሬ» ዜጎች በሃገሪቱ እጅግ ብዙ ገንዘብ ወጥቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የተመድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ቢሰማሩም ፣ በገሃድ አንዳችም ለውጥ እንዳላዩ ነው የሚነግሩህ። »

«ሚኑስካ» ወታደሮቹ በተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ ከፍቶ ሕይወት አጠፋ መባሉን ሀሰት ሲል አስተባብሎዋል። በ«ማአሬ» መዲና ባንጊ እንዳዲስ የተከሰተው ግጭት ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን «ሚኑስካ» ከኃይሉ ተግባር በመቆጠብ የፀጥታ ጥበቃ አቅሙን እንዲያጠናክር የሃገሪቱ ባለስልጣናት ጠይቀዋል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ