1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማኅበረሰባዊ ሂስ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 27 2007

«ባርያዉ» በሚል መጠርያዉ የሚታወቀዉ ወጣት ሰመረ ካሳ በመድረክ በሚያቀርባቸዉ አዝናኝና አስተማሪ ቀልዶቹ ተወዳጅነቱ ታዋቂነቱ እየጎላ መጥቶአል። በዕለቱ ዝግጅታችን ባርያዉን ከነቀልዱ ይዘን «ሂስ የማኅበረሰብ አረም መንቀያ መሳርያ ነዉ» ያሉንን ምሑራን ጋብዘን የሂስን ምንነት ለማየት ቀርበናል።

https://p.dw.com/p/1DiaW
ምስል DW

ወጣት ሰመረ ካሳ «ባርያዉ» በመድረክ በሚያቀርባቸዉ አዝናኝና አስተማሪ ቀልዶቹ ተወዳጅነቱ ታዋቂነቱ እየጎላ መጥቶአል። በሕግ ሞያ ትምህርት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀዉ ሰመረ ካሳ በህግ ጎዳዮች ላይ በአማካሪነት እንዲሁም በትርጎም ሥራ ላይ ተሰማርቶም ይገኛል። ይህ የሂስ መድረክን ግን እንደ አንድ መዝናኛ ስራዉ እንደሚተገብረዉ ነዉ የሚናገረዉ። ማኅበረሰባዊ ሂሶችን በቀልድ መልኩ እያዋዛ በመድረክ ለተመልካች የሚያቀርበዉ ወጣት ሰመረ ካሳ በመድረክ የሚያቀርባቸዉ ቀልዶች ማኅበረሰቡ ዘንድ ከለት ዕለት የሚታዩ ግን በቁም ነገና ቁም ነገር አዘል መሆናቸዉን በርካታ ወጣት አፍቃሪዎቹ ይናገሩለታል፤ እንደ አንዳንዶች በዓይነቱ ለየት ያለ መሆኑም ይናገራሉ።
አዲስ አበባ ከተማ ላይ በትርጉም ሥራ የሚታወቀዉ ወጣት ሰመረ፤ ይኽን አይነት ቁም ነገር አዘል ቀልዶችን የማዉጋት ልምድን የጀመረዉ ከልጅነቱ መሆኑንም አጫዉቶናል።.
ማኅበራዊ ሂስም ሆነ ሥነ-ጽሑፋዊ ሂስ አስፈላጊ ነዉ ያሉን ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ፤ ሂስ በኛ በኢትዮጵያዉያን ማኅበረሰብ ዉስጥ ጠንካራና የተለመደ ማኅበረሰቡ በሥነ-ቃል በቅኔ ቃልን ቋጥሮ ይገስፃል ያስተምራል።
የቸኮለች አፍሳ ለቀመች፤ ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባም የመሳሰሉትን ዓይነት ተረቶች ማኅበራዊ ሂሶች ናቸዉ። ሂስ ባይኖር መተራረም አይኖርም መተራረም ከሌለ ደግሞ ከነአረሙ የተመረተ ምርት ማረት ነዉ። ምርቱ በአረም እንዳይዋጥ ጎልጓሎ ያስፈልጋል፤ ለማኅበረሰብም እንደዝያዉ በማኅበረሰብ ዘንድ ያለዉ ጎልጓሎ ደግሞ ሂስ ነዉ ሲሉ ምሑራኑ ይገልፃሉ። በትያትርም ቢሆን የሂስ አቀራረቡ ተመሳሳይ ነዉ ሲሉ ተባባሪ ፕሮፊሰር አቦነህ አሻግሬ ተናግረዋል። የወጣት ሰመረ ካሳን ወይም «የባርያዉን» ማኅበረሰባዊ እይታዎች ይዘን ከደራሲ አለማየሁ ገላጋይ እና ከተባባሪ ፕሮፊሰር አቦነህ አሻግሬ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገናል። ቀልድ አዘል ትችቶቹን በሲዲ አሰባስቦ ሰሞኑን ብቅ እንደሚል የነገረንን ወጣት ሰመረ ካሳን ተባባሪ ፕሮፊሰር አቦነህ አሻግሬንና ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በማመስገን። ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን eንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ