1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሊ ዳግም ጦርነት ተቀሰቀሰ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 12 2006

ሰሜን ማሊ ኪዳል ከተማ ውስጥ የማሊ መንግሥት ወታደሮች ከቱዋሬግ አማፂያን ጋር ከባድ ውጊያ ማካሄዳቸው ተነገረ። በመንግሥትና በቱዋሬግ መካከል ድርድር ለማካሄድ የሚቻል አይመስልም ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1C38c
ምስል Kenzo Tribouillard/AFP/Getty Images
(MNLA)የተባለው የቱዋሬግ ዓማፂ ቡድን
(MNLA)የተባለው የቱዋሬግ ዓማፂ ቡድንምስል picture-alliance/AP

በማሊ ሰሜናዊ የሰሐራ በረሃ ኪዳል ከተማ ውስጥ በመንግሥት ወታደሮች እና በቱዋሬግ አማፂያን መካከል ከባድ ውጊያ መቀስቀሱ ተነገረ። በተለይ ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው ውጊያ በአማፂያን ታግተው የነበሩ 28 የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ትናንት ነፃ መለቀቃቸውም ይፋ ሆኗል። በውጊያው ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውም ተነግሯል። «የአዛዋድ ነፃ አውጪ ብሔራዊ ንቅናቄ» በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (MNLA)የተባለው የቱዋሬግ ዓማፂ ቡድን ቃል-አቀባይ ሙሳ አግ አሳሪድ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ሰዎች ታጋቾች ሳይሆኑ «የፖለቲካ እስረኞች» ናቸው ብለዋል።

«እኛ ቃላችንን የመጠበቃችንን ያህል የማሊ መንግሥትም ቃሉን መጠበቅ አለበት። እስረኞቹ ታጋቾች አልነበሩም፤ የማስለቀቂያ ገንዘብም አልጠየቅንባቸውም። የምንፈልገው መብታችን እንዲከበር ብቻ ነው። እስረኖቻችንን ደግሞ ምንጊዜም የጄኔቫውን ስምምነት በጠበቀ መልኩ ነው የምንይዛቸው።»

የማሊው ጠቅላይ ሚንሥትር
የማሊው ጠቅላይ ሚንሥትርምስል Habibou Kouyate/AFP/Getty Images

እስረኞቹ ነጻ ከወጡ በኋላ በደኅና ሁናቴ እንደሚገኙ አንድ የተመድ ቃል-አቀባይ ለፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። የአማፂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በበኩላቸው እስረኞቹ «በሠብዓዊ ምክንያት» ነፃ ወጥተው ለቀይ መስቀል ተሰጥተዋል ብለዋል። እስረኞቹ በምን አይነት ስምምነት ነፃ እንደወጡ ግን ይፋ አልሆነም። ከማሊ መዲና ባማኮ 1500 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ወደ ምትገኘው አሸዋማዋ የኪዳል ከተማ ትናንት ወደ 1500 የሚጠጉ የማሊ ወታደሮች መግባታቸው በአይን እማኞች ተረጋግጧል።

ሰሜናዊ የማሊ ግዛት ዕጣ-ፈንታን በተመለከተ የማሊ መንግሥት ከአማፂያኑ ጋር መደራደር ከጀመረ ወራት ተቆጥሯል። የማሊ መንግሥት የሀገሪቷ አንድነት የተጠበቀ እንዲሆን ፅኑዕ ፍላጎት አለው። ከአማፂያኑ በተለይ(MNLA)ጥያቄው እስከ ራስ-ገዝ አስተዳደር የሚዘልቅ ነው። ሙስሊም አማፂያን ከእዚህችው ኪዳል ከተማ ተንደርድረው በሰሜን ማሊ ሰፊ ነፃ ግዛት ለማቋቋም ከሁለት ዓመታት በፊት በመንቀሳቀስ የሀገሪቱን ሁለት ሦስተኛ ተቆጣጥረው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ የማሊ ጦር ሠራዊት በፈረንሣይ ጦር ርዳታ ሀገሪቱን በድጋሚ መቆጣጠር የቻለው ከዓመት ግድም በኃላ ነበር።


በማሊ ጦርና በአማፂያኑ መካከል ሰሞኑን ግጭቱ በድጋሚ የተቀሰቀሰው የማሊው ጠቅላይ ሚንሥትር ሞሣ ማራ ሰሜናዊ የማሊ ግዛቶችን በመጎበኝት ላይ ሳሉ ነበር። ኪዳል ከተማ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሚጎበኟቸው ቦታዎች አንዷ ናት። በባይሩትስ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ሰብ ተመራማሪው ጌዖርግ ክሉተ ለግጭቱ ዋነኛ ምክንያት ያሉት ይኽንኑ የማሊው ጠቅላይ ሚንሥትር ጉብኝትን ነው።

«የማሊው ጠቅላይ ሚንሥትር ጉብኝት ለግጭቱ ከፍተኛ ተምሳሌታዊ ተፅዕኖ አለው። ቀደም ሲል የራስ-ገዝ አስተዳደር አለያም የፌዴራሊዝም መብትን በተመለከተ ፈፅሞ ድርድር ውስጥ የማይገባ ጉዳይ ነው ማለታቸው ብቻ ሳይሆን፤ እራሳቸው እግራቸውን ኪዳል ውስጥ ሲያስገቡ ማሊ ያን አካባቢ እንደምትፈልገው ማመላከታቸው ነው።»

ጠቅላይ ሚንሥትሩ ኪዳልን ሲጎበኙ አማፂያን በዓየር ማረፊያው አካባቢ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ አድርገው ስለነበር በአካባቢው ጥብቅ ቁጥጥር ነበር። መንግሥት ከአማፂያን ጋር የሚያደርገውን ድርድር በማጓተቱ የኪዳል ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እንደሚያሰሙ የስነ-ሰብ ተመራማሪው ክሉተ ገልጠዋል። ኪዳል በልዩ አስተዳደር ወረዳ የምትመራ ከተማ በመሆኗ በርካታ ተቃዋሚዎች ይገኙባታል። እጎአ በ1960ዎቹ እና 1990ዎቹ ውስጥ ቱዋሬግ በአካባቢው በርካታ ተጨማሪ መብቶቹ እንዲከበሩለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። አሁን በኪዳል የተቀሰቀሰውን ግጭት አስመልክቶ በርካታ የዶቸ ቬለ አድማጮች ማሊ ብዙም ተስፋ የላትም ሲሉ ተደምጠዋል።

አንድ አድማጭ በዶቸ ቬለ የፈረንሣይ ቋንቋ ፌስቡክ ገፅ ላይ ሀሳቡን ሲገልጥ፤ ሰብዓዊነት ከጎደላቸው አካላት ጋር እንዴት ድርድር ማድረግ ይቻላል ብሏል። ሌላ አድማጭ በበኩሉ ሀገሪቱ ብትከፋፈል ምን ይገጥመን ይሆን? ሲል አጠይቋል። መከፋፈሉ ለሱዳንም አልጠቀመ። ደቡብ ሱዳን እጎአ በ2011 ባካሄደችው ሕዝበ-ውሳኔ ነፃነቷን አውጃለች። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ይህችው ደቡብ ሱዳን በአስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ከመጠመድ አልተረፈችም ሲል አስተያየቱን አጠቃሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዓርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ