1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሊ የአፍሪቃዋ አፍጋኒስታን

ሰኞ፣ ግንቦት 27 2004

እነቲምቡክቱን ያህል ጥንታዊ ከተሞችን በውስጧ አቅፋ የእስልምና አምባነቷ የሚጀምረው ገና በ13ኛው ክፍለ ዘመን አጥቢያ ላይ ነው። በረሃማዪቱ የቱሪስት መስህብ፤ ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ማሊ። የቱዋሬግ አማፂያን እና የእስልምና ሃይማኖት አክራሪዎች ሰሜናዊ ግዛቷን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ግን ማሊ ከመስህብነት ስጋት ወደዋጠው ሐገርነት እየተሸጋገረች ነው።

https://p.dw.com/p/157rc
ምስል picture alliance/Ferhat Bouda

እነቲምቡክቱን ያህል ጥንታዊ ከተሞችን በውስጧ አቅፋ የእስልምና አምባነቷ የሚጀምረው ገና በ13ኛው ክፍለ ዘመን አጥቢያ ላይ ነው፤ በረሃማዪቱ የቱሪስት መስህብ፤ ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ማሊ።  የቱዋሬግ አማፂያን እና የእስልምና ሃይማኖት አክራሪዎች ሰሜናዊ ግዛቷን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ግን ማሊ ከመስህብነት ስጋት ወደዋጠው ሐገርነት እየተሸጋገረች  ነው። 

በሠላሙ ዘመን የእስልምና ሊቃውንት ልሂቃን እስኪሰኙ ድረስ በረሃውን ያለ አንዳች ስጋት ከሰሜን ደቡብ ተመላልሰውበታል። ሲራራ ነጋዴዎች ሸቀጦቻቸውን በግመሎቻቸው ሸክፈው አሸዋውን ተመውበታል። ዛሬ ደግሞ በዛው በረሃ እየተጥመለመለ የሚያልፈው ሃያል ቡዋሒት ከሚበትነው አሸዋ ጋር የሚስተካከሉ የቱዋሬግ አማፂያን እና የእስልምና ሃይማኖት አክራሪ አንሳር ዲኔዎች ሰሜኑን ክፍል ሽብር ለቀውበታል። ዳግማዊቷ አፍጋኒስታን አፍሪቃ ውስጥ እያጎነቆለች ነው ሲልም ዓለም ከወዲሁ ስጋት ገብቶታል።

የማሊ ሴት
የማሊ ሴትምስል picture alliance/Godong

በሰሜን ማሊ እስላማዊ የሻሪኣ ህግ ፀንቶ ቡና ቤቶች እና የሙዚቃ ዝግጅቶች እገዳ ተጥሎባቸዋል። ሴቶች በአደባባይ ፊታቸውን ሊሸፍኑ፣ የእጅ አመል ያለበት ደግሞ ቀኝ እጅ አልባ እንዲሆን በአክራሪዎቹ ታውጇል። ከሁሉም የከፋ የተባለለት የእስልምና ሃይማኖት አክራሪዎቹ አንሳር ዲኔዎች ከቱዋሬግ አማፂያን በምህፃሩ  MNL ጋር ለመዋሃድ ዳር ዳር የማለታቸው ጉዳይ ነው።   የ MNL ተወካይ ኮሎኔል አግ ቦና፥

«የቀረን MNL የማይቀበለው የአንድ ሰነድ ጉዳይ ብቻ ነበር። MNL ዲሞክራሲያዊ ሐገር መመስረት ሲፈልግ አንሳር ዲኔዎች እስላማዊ መንግስት ማቆም ነው የሚሹት። በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ንቅናቄዎች አንድ የሚያደርጋቸውን  መንገድ እያፈላለጉ ነው።»

ሰሜን ማሊ በቱዋሬጎች እና አንሳር ዲኔዎች ቁጥጥር ስር ብትወድቅም ማሊን በወቅቱ በበላይነት የሚያስተዳድራት ግን ማን እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚንስትር ይሁን መንግስት ገልባጮቹ አለያም ፓሪስ ለህክምና የሚገኙት የሐገሪቱ ርዕሰ-ብሔር ለብዙዎች ግልፅ አልሆነም።  አዛውንቱ ርዕሰ-ብሔር ቤተ-መንግስቱን ሰብረው በገቡ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው  መዘገቡ የሚታወስ ነው።  ሐምቡርግ በሚገኘው የላይብኒትስ ተቋም የማሊ አዋቂ የሆኑት ቻርሎቴ ሄይል የምዕራብ አፍሪቃ ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ገልፀዋል።

«ማሊ ከምን ጊዜውም በከፋ ሁኔታ ቀውስ ውስጥ ነው የምትገኘው፤  በእርግጠኝነት  ደግሞ ከአስቸጋሪው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ወዲህ ማለት ነው። ከባማኮ አሁንም ድረስ ግልፅ የሆነ አመራር ባለመኖሩ ሁኔታው በጣም አደገኛ ይመስላል።»

አካባቢው ወደ ባሰ ቀውስ ከማምራቱ በፊት የምዕራብ አፍሪቃ መንግስታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ኤኮዋስ  ርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ የአካባቢው አዋቂዎች እየወተወቱ ነው። እንደ ቻርሎቴ ገለፃ በኢኮዋስ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ከመፈፀሙ በፊት የማሊ መንግስት ሰሜኑን ከተቆጣጠሩት ሃይላት ጋር በቅድሚያ መደራደር ይኖርበታል። «ለኧንዲፔንዶን» በተሰኘው የማሊ ዕለታዊ ጋዜጣ የፖለቲካ ተንታኙ ኦላሳን ዲያራ የማሊ መንግስት ድርድር ማድረግ ካለበትም ድርድሩ ከቱዋሬጎች ይልቅ ከአንሳር ዲኔዎች ጋር መሆን እንዳለበት ይጠቅሳል።

ቀውስ በማሊ
የቱዋሬግ ተዋጊዎችምስል picture-alliance/Ferhat Bouda

«በኢኮዋስ የሚታገዘው  መንግስት መደራደር ያለበት  ከአንሳር ዲኔዎች ጋር ነው።  ምክንያቱም እነሱ ስለመገንጠል አያነሱምና። ይልቁንስ  MNL ዎች የራሳቸውን ባንዲራ ሲያውለበልቡ አንሳር ዲኔዎች ከፍ ያደረጉት የማሊን ሠንደቅ ዓላማ ነው።»

MNL በሚል ምህፃር የሚታወቁት ቱዋሬጎች ነፃ መንግስት የማቆም ዓላማቸው አደገኛነት ለአጠቃላይ ቃጣናው እንደሆነ ብዙዎች ይጠቅሳሉ።  MNL  በሙሉ መጠሪያው «የአዛዋድ ነፃ አውጪ ብሔራዊ ንቅናቄ» ይሰኛል። ይህ ንቅናቄ ዋነኛ ህልሙ አዛዋድ የተሰኘችውን ነፃ ሐገር መፍጠር ነው። ያን ደግሞ ለማሳካት አንሳር ዲኔ ከተሰኘው እስላማዊ ቡድን ጋር መቀየጥ  ሳያስፈልገው አልቀረም። አንሳር ዲኔ በማግሬቡ የአልቃይዳው የሰሜን አፍሪቃ ህዋስ  የቅርብ ድጋፍ የሚደረግለት ተዋጊ ቡድን ነው። ታዲያ በቱዋሬግ እና አንሳር ዲኔ ሃይላት መካከል የነበረው የውህደት ንግግር መቋጫ ያለማግኘቱ ጉዳይ ለጊዜውም ቢሆን ብዙዎችን እፎይ አሰኝቷል። በእርግጥ ሁለቱም እስላማዊ መንግስትን ማቋቋም ቢሹም ያለመስማማታቸው መሰረቱ የሻሪኣ ሕግ ይግዛን ወይንስ ሌላ ስርዓት የሚለው አብይ ነጥብ ነበር። በዚህም አለ በዚያ ነፃ የአዛዋድ መንግስትን በአካባቢው ማቆም እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም ሲል ማሊያዊው ጋዜጠኛ እንዲህ ያስረግጣል።

ቱዋሬጎች የሚያልሙት የአዛዋድ ግዛት
ቱዋሬጎች የሚያልሙት የአዛዋድ ግዛትምስል DW

« MNL ዎች የሚሹት አዛዋድ የሚሏቸውን  በአካባቢው የሚገኙትን አጠቃላይ ሕዝቦች ይዘው ሐገር መፍጠር ነው። ይህ አካባቢ ደግሞ ማሊ ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ እና አልጀሪያንም ያጠቃልላል።»

በእርግጥም የቱዋሬግ አዛዋዶች ከማሊ ውጪ በሰሜን ምዕራብ ኒጀርም ይገኛሉ። የሞሪሺየስ አዛዋዶች ደግሞ ነዋሪነታቸው በምዕራብ ኒጀር ነው፣ እንዲሁም የኒጀር አዛዋዶች ወንዞችን ተከትለው ከሰፈሩ ዘመናት ተቆጥሯል። ያም በመሆኑ ነው ሰሜን ማሊን ጠቅልለው ከአጎራባች ሀገራት ሕዝቦች ጋር የአዛዋድ መንግስትን መመስረት የሚመኙት ቱዋሬጎች ሀሳብ ለአካባቢው ጠንቅ ሊሆን ይችላል የተባለለት። በአንድ ወቅት የተረጋጋች ሐገር ሆና በቱሪስት መስህብነቷ የምትታወቀው ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ማሊ ገና ከወዲሁ የወንጀለኞች፣ አደንዛዥ ዕፅ እና ሕገወጥ የጦር መሳሪያ አዟሪዎች እንዲሁም  የአሸባሪዎች መናኸሪያ ወደ መሆን እየተቀየረች ነው። የቱዋሬጎች እና የአንሳር ዲኔዎችም የውህደት ድርድር ዛሬም በሂደት ላይ እንዳለ ታውቋል። ማሊ ለሁለት ተከፍላ የቱዋሬጎቹ አዛዋድም ሐገር ሆና ትቀጥል አለያም እንደተፈራው ሁሉ አካባቢው ማብቂያ ወደሌለው ትርምስ  ያምራ ከወዲሁ መተንበይ ይከብዳል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ