1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሊና ቱዓሬጎች፣

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2005

ማሊ ውስጥ ፣ባለፈው ዓመት መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ፣ ሰሜናዊውን የአገሪቱን ከፊል በመጀመሪያ ቱዓሬጎች፤ ቀጥሎም አክራሪ የሚሰኙ ሙስሊም ታጣቂዎች ተቆጣጥረውት እንደበረ አይዘነጋም። ከዚያን ጊዜም አንስቶ ነው ታዲያ፣ የመዲናይቱ የባማኮ

https://p.dw.com/p/18tPf
ምስል DW

ኑዋሪዎች የአገራቸው ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ጽኑ ፍላጎታቸውን ሲያንጸባርቁ የቆዩት።  አሁንም ቢሆን የባማኮ አስተዳደር አገሪቱን በመላ ከዳር እስከዳር መቆጣጠር አልቻለም። ይሁን እንጂ አሁን በተፈረመው የሰላም ውል መሠረት ሁሉም የሚሠምር መስሏል። የማሊ መንግሥት ተወካዮችና የተለያዩ የቱዓሬግ ቡድኖች ትናንት ማታ ዋጋዱጉ ፣ ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ውሉን ተፈራርመዋል። በመሆኑም የማሊ መንግሥትበአቅዱ መሠረት በመጪው ሐምሌ እንዲካሄድ የታቀደውን  ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ አይሳነውም።

ከፊሉን ሰሜን ማሊን  በፈረንሳይ  ወታደሮችና በአፍሪቃ አህጉር ሰላም አስከባሪ ኃይል የባማኮ መንግሥት መልሶ መቆጣጠር ቢችልም ፣ MNLA በሚል የፈረንሳይኛ ምህጻር የሚታወቀው የአዛዋድ ብሔራዊ ነጻ አውጪ ንቅናቄ  አሁንም  ቢሆን በሰሜን ማሊ አንዳንድ ከተሞችንና መንደሮችን በመቆጣጠር ላይ ነው የሚገኘው። በቁጥጥሩ ሥር ከዋሉት መካከል ቱዓሬጎች ተጠናክረው የሚገኙባት ኺዳል አንዷ ናት። MNLA እና ተጓዳኞቹ፤ ከአንግዲህ ሌሎች ቦታዎችን በቁጥጥራቸው ሥር እንደማያውሉ ቃል ገብተዋል።  በምትኩ፤ ትጥቃቸውን ለመፍታት እንደማይገደዱ ቃል ተገብቶላቸዋል።

Burkina Faso Mali-Abkommen in Ouagadougou
ምስል AHMED OUOBA/AFP/Getty Images

የማሊ የሀገር አስተዳደር ሚንስትር ሙሳ ሲንኮ ኩሊባሊ፣ የመንዽሥት ወታደሮች፤ ኪዳል ውስጥ እንዲሠፍሩ ንቅናቄው መፍቀዱ ወሳኝነት አለው ባይ ናቸው። ውሉ፣ በዋጋዱጉ ከተፈረመ በኋላ፣ ኩሊባሊ ለዶቸ ቨለ እንዲህ ብለዋል።

«የሰላሙ  ውል ፣ሰሜን ማሊን ለማረጋጋትና ጸጥታውን ለማስከበር አንድ ወሳኝነት ያለው እርምጃ ነው። ውሉ፤ በሐምሌ እንዲካሄድ የታቀደውን የምርጫ  ጊዜ ሰሌዳ እንዲጸና ለማድረግም ይበጃል። »

ይህም ሲሆን ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ወዲህ እንደገና በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ማሊ ውስጥ ይቋቋማል ማለት ነው። ዓለም አቀፍ ተጽእኖ በተለይም ከፈረንሳይ በኩል በማየሉ፣ማሊ ምርጫውን በሐምሌ ወር ማካሄድ ግዴታ አድርጋዋለች። የሰላሙ ውል ፤ የባማኮ  መንግሥት ወታደሮች፣ በኪዳልም  ምርጫውን እንዲታዘቡ  ያስችላቸዋል። ጀርመን  ውስጥ በባይሮይት ዩኒቨርስቲ የጎሳዎች  ጉዳይ ተመራማሪና ስለማሊ  ጥናት ያደረጉት  ፕሮፌሰር  ጊዖርግ ክሉተ፣ ስለሃገሪቱ መጻዔ ዕድል ለዶቸ ቨለ ሲያብራሩ--

«በመጀመሪያ በመንደር፤ ከዚያ በክፍለ- ግዛት ፣ ቀጥሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ወሳኝነት ባለቸው ጉዳዮች ውይይት እንዲካሄድ ማድረጉ ይበጃል። ምን ዓይነት የአስተዳደር ሥርዓት ይበጀናል? የሞራል መሠረታችን ምን ይሆናል? ለሃይማኖት የማይወግን ሥርዓት ሊኖረን ይገባል? የወደፊቷ ማሊ ምን መምሰል አለባት?»

Symbolbild Mali MNLA Verhandlungen mit Regierung
ምስል picture-alliance/Ferhat Bouda

የማሊ ተወላጆች ምን እንደሚፈልጉ ውሳኔ ህዝብ ያሻል። አካባቢዎችን ክፍላታ ሀገርንና ማዕከላዊውን አስተዳደር የሚያስተሣሥር ሥርዓት ያስፈልጋል። ይህም ሲሆን እያንዳንዱ የአገሪቱ ክፍለ ግዛት ራስ ገዝ መስተዳድር ሊኖረው ይችላል።

የቱዓሬጎች ተወካይና ተደራዳሪ ማሐማዱ ጀሪ ሜይጋ---

«በእግዚአብሔር ፈቃድ የተቻለንን  ሁሉ በማድረግ፣ ይህ ውል ተፈጻሚ እንዲሆን፣ ቃል በተግባር እንዲተረጎም  እንጥራለን።  የጥላቻ ምዕራፍ ተዘግቶ፣ በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል የፍቅርና የትብብር  ምዕራፍ እንዲከፈት እናደርጋለን።»

ውሉ ከተፈረመ ወዲህ ፣ ምርጫውን በሚገባ ማዘጋጀት እንዲሁም ቀሪውን መሰናክል ማስወግድ የግድ ይላል። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በደቡብ ማሊ የሠፈሩ ሲሆን፤ ወደ ጎረቤት ሃገራት የተሰደዱ ዜጎችም አሉ። እነዚህ ወገኖች ሁሉ የሚሳተፉበትን ምርጫ በመጪው ወር ማካሄድ መቻሉ በጣሙን ነው የሚያጠራጥረው።

ከሰኔ 24,2005 አንስቶ ፣ የተባበሩት መንግሥታት የመደባቸው 12,600 ሰላም አስከባሪዎች የማሊን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋጋት ይሠማራሉ። ካለፈው ሚያዝያ ወር አንስቶ የአውሮፓው ኅብረት፣ የማሊን ወታደሮች በማሠልጠን ላይ ነው። 180 ወታደሮቿን የላከችው ጀርመን፣ የዚሁ አሠልጣኝ ቡድን አካል ናት። ከዚህም ሌላ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፤ በመጪው ዓመት ከ 3 ቢሊዮን ዩውሮ በላይ እርዳታ ለማቅረብ ቃል ገብቷል። አሁንም ማሕማዱ ጀሪ ሜጋ---

Burkina Faso Mali-Abkommen in Ouagadougou
ምስል AHMED OUOBA/AFP/Getty Images

«ወደፊትም ቢሆን፤ ከምዕራብ አፍሪቃው የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ፤ (ኤኮዋስ)፣ ከአፍሪቃ ኅብረት፣ እንዲሁም በአጠቃላይ  ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርዳታ እንዲደርሰን፣ መጠየቃችን አይቀርም። ድጋፉ ፣ ይህን የተስማማንበትን ውል ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል። »

የሰላሙ ውል ምርጫ እስኪካሄድ ነው የሚጸናው። በህዝብ የተመረጠ ፕሬዚዳንት ሥልጣን ካገኘ በኋላ ወሳኝነት ያለው ለዘለቄታው የሚበጅ ድርድር እንደሚያሂድ ነው የሚጠበቀው።   በአዲሱ ተመራጭ መንግሥትና በቱዓሬግ አማጽያን ተወካዮች መካከል፤ ውይይት የሚከፈተው ምርጫው ከተካሄደ ከ 2 ወራት በኋላ እንደሚሆን ስምምነት ተደርጓል። «አዛዋድ» የተባለው ሰሜናዊው ማሊ ፣ ወደፊት ምን ያህል ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን እንደሚያገኝ ፤ በቀጣዩ ውይይትና ድርድር ይሆናል የሚወሰነው።

ተክሌ የኋላ

አርያም  ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ