1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙዚቃን ለመልሶ ግንባታ

ሐሙስ፣ ጥር 4 2009

ጦርነት ሰቆቃ እንግልትና ሞት የየለት ክስተት እየሆነ በመጣበት በዚህ ዓለም ለሠላም ማስፈን ሂደት ኪነ-ጥበብ በተለይም ሙዚቃ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል።

https://p.dw.com/p/2VitJ
Wiederaufbau von Gesellschaften mit Musik - Neue Graduiertenschule am Center für World Music
ምስል Borno Music Documentation Project

 

በናይጄርያ በሚንቀሳቀሰዉ ቦኮሃራም በተሰኘዉ አሸባሪ ቡድን ምክንያት የተፈናቀሉ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎችን  ወደ ቀድሞ ቀያቸዉ ለመመለስ ጥረት ተጀምሮአል።  ስደተኞቹ ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞ መኖርያ ቀያቸዉ እንዲመለሱና አካባቢዉ ላይ መረጋጋት እንዲሰፍን የናይጀርያ የጋና ምሁራን እንዲሁም በጀርመን ሄልድስ ሃይም ከሚገኘዉ ዓለም አቀፉ የሙዚቃ ምርምር ማዕከል ጋር በጋራ ባህላዊ እንቅስቃሴና ልማትን ለዘላቂ ክንዉን በሚል ጥናት ጀምረዋል። በሰሜናዊ ናይጄርያ የሚገኙ ስደተኞችን መልሶ በማቋቋም ሂደትና ኪነ-ጥበብ እና ባህላዊ እንቅስቃሴ በመልሶ ግንባታ ላይ ያለዉን ሚና እናያለን። ታዋቂዉን የከባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪ ዘለቀ ገሠሠንም በስደት ኑሮ የሙዚቃ ህይወቱን አጫዉቶናል። 

«በሰሜናዊ ምስራቅ ናይጀርያን የሚያገናኘዉ መስመር ማለትም ከአዉራጃዉ እስከ ገጠር ያሉ ቦታዎች ላይ ሁሉ በቦኮሃራም ከፍተኛ ጥፋት ደርሶበታል። በዚሁ አካባቢ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከቦኮሃራም ጥቃት በተጠበቁ ስደተኛ ጣብያ ዉስጥ ይኖራሉ። አሸባሪዉ ድርጅት ቦኮሃራም ያለፍላጎታቸዉ ከመኖርያ ቀያቸዉ ከባህላቸዉ እንዲነሱ ያደረጋቸዉ እነዚህ ሰዎች እዚህ ቦታ ላይ ሲኖሩ አምስት ስድስት ዓመት ሆኖዋቸዋል፤ አሁን ቀስ በቀስ ከተፈናቀሉበት ገጠራማ አካባቢ መመለስ ይኖርባቸዋል።» 

ይላሉ፤ የሙዚቃ ምሁርና በጀርመን ሄልድስ ሃይም ከተማ በሚገኘዉ የዓለም የሙዚቃ ማዕከል "Center for World Music" የተሰኘዉ የሙዚቃ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ራይሙንድ ፎግልስ። ራይሙንድ ፎግልስ በ 1980ዎቹ በናይጀርያ ማዱግሪ ከተማ ከሚገኘዉ ዩንቨርስቲ ጋር የምርምር ሥራን በማከናወናቸዉ በተለይ ሰሜናዊ ናይጀርያ አካባቢን በደንብ ያዉቃሉ።       

Nigeria Stadt Borno State Maiduguri
ምስል Getty Images/AFP/Stringer

አካባቢዉ ላይ በሚንቀሳቀሰዉ ቦኮ ሃራም ጽንፈኛ ቡድን የተነሳ ነዋሪዎቹ ከቤት ንብረታቸዉ ብቻም ሳይሆን ከለመዱት ከባህላዊ የገጠራማ አካባቢ ኑሮዋቸዉ ለመፈናቀል ተገደዋል። ሽብርተኛዉ ቡድን በተለይ ባህላዊ ክንዉኖችን በማጥፋት ከያኒያንያንና የሥነ-ጠበብት ሰዎችን ዒላማ በማድረግ በርካቶችን አፍኖ አስሮአል ገድሎአልም። ተፈናቃዮች ከአምስት ዓመት ጀምሮ በሰሜናዊ ናይጀርያ በሚገኘዉ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ መኖር ጀምረዋል።  እነዚህ ባህልና ቀያቸዉን የተነጠቁ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ወደነበሩበት መንደር ለመመለስና የቀድሞ ሕይወታቸዉን እንዲኖሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነዉ። ጀርመናዊዉ የሙዚቃ ጥናት ባለሞያ ራይሙንድ ፎግልስ እንደሚሉት ተፈናቃዮቹን መመለሱ ቀላል አይሆንም።

« ቀድሞ ይኖሩ በነበሩበት የገጠር መንደር ለመመለስና እንደቀድሞዉ ሁሉ በአንድ ተሰባስቦ የመኖሩ ሁኔታ ተመልሶ የሚመጣ አይሆንም ምክንያቱም በርካታ ሰዎች በመሞታቸዉ ነዉ። አሁን አዲስ ቀየ፤ አዳዲስ ጉርብትናን ነዉ የሚመሰርቱት»  

በዚህም ይላሉ የሙዚቃ ጉዳይ አዋቂዉ ራይሙን ፎግልስ ማኅበረሰቡን ዳግም ለማቋቋምና ባህላዊ ህይወቱን እንዲቀጥል ለማስቻል ሥነ-ጥበብ እና ሙዚቃ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል። ሙዚቃ በጦርነት በግጭት ሰበብ በከፍተኛ ስቃይና የአይምሮ ጭንቀት የተወጠረ አዕምሮን የሚጠግን ነዉ።

« ከዚህ ኃሳብ በስተጀርባ ያለዉ ዓላማ፤ ሙዚቃን በመጠቀም የሚታየዉን የጸብ ምክንያትና መነሻ እንጋገርበት የሚል  ነዉ። ይህ ደሞ በሙዚቃ ጥናት ያየነዉ ነዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ ስለጎረቤቴ ምን አስባለሁ የሚለዉ ይሆናል። በዚህም ባህላዊ እንቅስቃሴዎች ኪነ-ጥበብ ረዘም ያለ የግጭት መፍቻ ዘዴ ነዉ ብለን እናምናለን።»   

ይህን እንዴት ሊሳካ እንደሚችል ባህላዊ እንቅስቃሴና ልማትን ለዘላቂ ክንዉን በሚል ጥናት ከዝያዉ ከናይጀርያና ከጋና የመጡ ምሁራን የምርምር ሥራን ጀምረዋል። ከነዚሁ ምሁራን ጋር በመተባበር በጀርመን ሄልድስ ሃይም ከተማ የሚገኘዉ የሙዚቃ ምርምር ተቋም በናይጀርያ ማዱግሪ ከተማ ከሚገኘዉና በጋና ኬፕኮስታ ዩንቨርስቲ እየሰራ ነዉ። የጀርመን ኤኮኖሚና የልማት ትብብር ሚኒስቴር የተመድ ዘላቂታማ ብሎ ባስቀመጠዉ እቅድ መሠረት በጀርመን የሚገኘው የአካደሚ ልውውጥ በጀርመንኛው አኅጽሮት «DAAD» በመርኮዝ ለምርምር ስራዉ ድጋፍ ይሰጣል።

የዓለም የሙዚቃ ማዕከል በመባል የሚታወቀዉ በጀርመን ሂልድስ ሃይም ከተማ የሚገኘዉ የሙዚቃ ምርምር ተቋም በተለያዩ የዓለም ሙዚቃዎች ላይ የምርምር ሥራን መስራት የጀመረዉ በጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓ,ም ነዉ። በዚህ ማዕከል የምርምር ሥራ ብቻ ሳይሆን የሙዚቃ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምም ነዉ።  ተቋሙ ከዓለም ዙርያ የተሰበሰቡ ከ 4500 በላይ የሙዚቃ መሳርያ እንዲሁም ወደ 45 ሺህ የሙዚቃ አልበሞችን በማህደሩ በማስቀመጥ በአዉሮጳ ከፍተኛ የሙዚቃ ክምችት የሚገኝበት ተቋም እንደሆነም ይነገርለታል። በዚሁ ተቋም በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የተሰባሰቡ የሙዚቃ ምሁራን የመጀመርያዉን የአዝማሪ ጉባዔ ማዘጋጀታቸዉ ይታወሳል።

Studiengang musik.welt Universität Hildesheim
ምስል Isa Lange/Universität Hildesheim

ለ 35 ዓመት እኔ ራሴ ስደተና ነበርኩ ብሔራዊ ስሜትን ባህላዊ ጉዳዮች በኅብረተሰብ ለማስረጽ ሙዚቃ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል ያለን ታዋቂዉ ሙዚቀኛ ና የተፈጥሮ ጉዳይ ተቆርቋሪ ዘለቀ ገሠሠ እንደሚለዉ ሙዚቃ መፈወሻ፤ ሙዚቃ መልክት ማስተላለፍያ ግዙፍ መሳርያ ነዉ የሚለዉ ሙዚቀኛ ዘለቀ ገሠሠ ሙዚቃ በዓለም ላይ ጥሩ ለመስራት ኅብረት ለመፍጠርም ትልቅ ብሎም በአሁኑ በስልጣኔዉ ዘመን የሕክምና መሳርያም ሆንዋል ሲል ተናግሮአል።     

በሙዚቃ ስለዓለም ሰላም ሰብዓዊነት ስለመከበር ይዘመርበታል ያለን ዘለቀ ገሠሠ በምዕራቡ ዓለም ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር ይናገራል።

ሙዚቃን መልሶ መቋቋምያ በሚል በናይጀርያ ቦኮሃራም አሸባሪ ቡድን የተፈናቀሉና በስደተኞች መጠለያ የሚኖሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ማኅበረሰቦች ወደ ቀድሞ ቀያቸዉ እንዲመለሱ በስደት የተነጠቁት ጥንታዊ የአኗኗር ዘያቸዉና ባህላቸዉን መልሰዉ እንዲገነቡ ጥረት ስለመጀመሩ አስመክቶ ኪነ-ጥበብ ያለዉን ሚና እና ያየንበትን ከአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዉ ከዘለቀ ገሠሠ ጋር ያደረግነዉ ቃለ-ምልልስን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ