1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙስና እየተባባሰ መጥቷል ተባለ

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2009

ሙስና  እየተባባሰ መምጣቱን ዓለማቀፉ  የጸረ ሙስና ተቋም ይፋ አደረገ። ተቋሙ ከሰሞኑ ባወጣዉ  የሀገሮች  የጸረ ሙስና  ደረጃ ዝርዝር  እንዳመለከተዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአፍሪቃ ሙስና ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል። በዘንድሮዉ የጸረ ሙስና ደረጃ በዝርዝር ከ176 ሀገራት ኢትዮጵያ 108ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

https://p.dw.com/p/2Wi16
Infografik Karte Korruptionsindex ENG

 

176 ሀገሮችን ያካተተዉ  አዲሱ የዓለም አቀፉ የጸረ ሙስና ተቋም የመረጃ ጠቋሚ ዝርዝር ፤ ከአምናዉ ጋር ሲነጻጸር  አብዛኛወቹ  ሀገራት ደረጃቸዉን  ከማሻሻል ይልቅ እያሽቆለቆሉ መምጣታቸዉን አመልክቷል። በድህነትና  በሙስና ስሟ ተደጋግሞ የሚጠቀሰዉ  አፍሪቃም ፤በዘንድሮዉ የተቋሙ የጸረ ሙስና ደረጃ ጠቋሚ ዝርዝር  አብዛኛወቹ   ሀገሮቿ  ደረጃቸዉ ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በአዲሱ የድርጅቱ   የሀገሮች የጸረ ሙስና  መረጃ ጠቋሚ ሰንጠረዥ  መሰረት የአፍሪቃ ሃገራት ከ50 እስከ 176 ባሉት ደረጃዎች ዉስጥ የተቀመጡ ሲሆን ኢትዮጵያ  108ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።  ከአምናዉ ጋር ሲነጻጸር  ደረጃዋ መዉረዱንና ሙስና በሀገሪቱ አሁንም ትልቅ ችግር ሆኖ መቀጠሉን ያሳያል ተብሏል። መንግስታትት ለጸረ ሙስና  ትግሉ የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን ለሙስና መባባስ አብይ ምክንያት መሆኑንም ተጠቁሟል። ትራንስፓረንት ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ተመራማሪና ዳይሬክተር ፊን ሃይንሪሽ  ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የዘንድሮዉ የሃገራቱ የጸረሙስና ዝርዝር ከመሻሻል ይልቅ ማሽቆልቆሉ የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል ብለዋል።

«ስመለከተዉ የአሁኑ  አመት  ከአምናዉ ጋር ሲነጻጸር  ብዙ ሃገሮች በመረጃ ጠቋሚዉ ዝርዝር  ወደ ላይ ከመዉጣት ይልቅ ደረጃቸዉ ወደታች ወርዷል። ቢያንስ ይህ አሳሳቢ ምልክት ይመስለኛል።»

በአፍሪቃ ለእርዳታ በየዓመቱ ከሚገባዉ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ዉስጥ  ከግማሽ በላይ የሚሆነዉ በሙስና እንደሚመዘበርና ተመልሶ ወደተለያዩ ሀገራት እንደሚወጣ መረጃወች ያመለክታሉ። በዚህም የተነሳ  ሙስና አብዛኛዉ የአህጉሪቱ ህዝብ  የኑሮ ደረጃ ከመሻሻል ይልቅ የእለት ጉርስ ማግኜት እንኳ አስቸጋሪ የሆነበት የድህነት ህይወት እንዲገፉ  እያደረገ ይገኛል። በድሃዉ ህዝብና በሙሰኞች መካካልም ማህበራዊ  ልዩነት እያሰፋ መምጣቱ እየተገለጸ ነዉ። ዓለም አቀፉን የጸረ ሙስና ተቋም የመረጃ ዝርዝር ላይ ግምገማ ያካያሄዱት ፊን ሀይንሪሽ  ሙስና ማህበራዊ ልዩነትን እያሰፋ የመጣ መጥፎ ኡደት ነዉ ይሉታል።

Karte Äthiopien englisch

« እንደ ተመራማሪ ተዛምዷቸዉን፣እርስ በእርስ ያላቸዉን ትስስስርና   እንቅስቃሴያቸዉ ምን ያህል እንደሆነ ማየት አስገራሚ ነበር። የሙስና  መባባስ  ልዩነትን  የሚያባብስ መጥፎ ኡደት ነዉ።»

ይሁን እንጅ ሙስና በባህሪዉ በሚስጥርና በድብቅ የሚካሄድ ስለሆነ ምስክርና ማስረጃ ማግኔት አስቸጋሪ በመሆኑ የሙስና ትግል ቀላል እንዳልሆነ የሚናገሩት ደግሞ  በጀርመን ሀገር  የሽሌስቪግ ሆልሽታይን ፌደራል ግዛት የጸረ ሙስና ኮሚሽነር የሆኑት ሃንስ ቬርነር ሮገ ናቸዉ።

«በሙስና ወንጀል ዉስጥ  ያልተገባ ጥቅም ለማግኜት ገንዘብ የሚሰጡና  የሚቀበሉ  ተዋናዮች አሉ። ሁለቱም  ጥፋተኞች ናቸዉ።ያ ማለት ለፓሊስ ቅሬታ የሚያቀርብ  ተጎጅ የለም ማለት ነዉ።»

ተመራማሪዉ ፊን ሀይንሪሽ ግን ሙስና የቱንም ያህል ሚስጥራዊና አስቸጋሪም ቢሆን ከህዝብ አይንና ጆሮ ተደብቆ የሚቀር የለም ባይ ናቸዉ። ስለሆነም ሙስናን ለመከላከል ህዝብና ነጻ መገናኛ ብዙሃን ጥሩ መሳሪያወች መሆናቸዉን አሰምረዉበታል። ያ ካልሆነ ግን  ሙስና  አዉዳሚ የህዝብ ችግር ሆኖ ይቀጥላል ይላሉ።

«እናዉቃለን ሙስና  አዉዳሚ ነዉ። ሙስና በተለያዩ ቦታወች  ተቋማትን  በመመዝበር  ለህዝብ ጥቅም የሚያስፈልገዉን  ሀብት ያወድማል። ስለዚህ በእርግጠኝነት ሙስና  በዓለም ዙሪያ ካሉ ከፍተኛ አዉዳሚ የህዝብ ችግሮች ዉስጥ  አንዱ ነዉ።»

በዘንድሮዉ የአለም አቀፉ የጸረ ሙስና ተቋም የደረጃ ዝርዝር አዉሮጳዊቷ ሀገር ዴንማርክ 1ኛ ስትሆን አፍሪቃዊቷ ሃገር ሶማሊያ ደግሞ 176ኛ ላይ በመቀመጥ የመጨረሻዉን ደረጃ ይዛለች።

 

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ