ሙርሲ እና የግብፅ የቱሪዝም ዘርፍ
ረቡዕ፣ ሰኔ 27 2004
አዲሱ የሀገሪቱ መንግሥት ለምሳሌ አለባበስን ወይም የአልክሆል መጠጥን በተመለከተ ሊያሳርፈው የሚችል ገደብን፡ ቱሪስቶችን ሊያስደነግጥ ስለሚችል፡ መሥሪያ ቤቱ እንደማይቀበለው አስታውቀዋል።
በግብፅ የቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘዋ የኤል ጉና ከተማ የሚኖሩት የጥልቀት ዋና መምህር የ 36 ዓመቱ ኤክራሚ ላቲፍ ሞሀመድ ሙርሲ ፕሬዚደንት ሆነው መመረጣቸው በይፋ በተነገረበት ዕለት ከሁለት ጥሩምባ እየነፉ ከተንቀሳቀሱ መኪኖች በስተቀር በከተማይቱ ፅጥታ ሰፍኖ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ የከተማይቱ መራጮች ድምፃቸውን የሰጡት ለሙርሲ ተፎካካሪና የቀድሞው መንግሥት ተወካይ ለአህመድ ሻፊቅ ነበር። በቱሪዝም የሚተዳደሩት የኤል ጉና ነዋሪዎች ሀገር ጎብኚዎቹ ከከተማይቱ እንዳይርቁ መስጋታቸውን ኤክራሚ ገልጸዋል።
« አዎ በርግጥ ሙርሲን እፈራለሁ። ቱሪስቶቹ ተመሳሳይ የአየር ፀባይ ወዳላት፡ ግን ይበልጥ እንግዳ ተቀባይ ወደሆነች ሌላ ሀገር ይሄዳሉ ብየ የስባለሁ። »
ኤል ጉና እንግዳ ተቃባይነት አይጎድላትም። ቱሪስቶች የሚዝናኑባት የተለያየ የውኃ ስፖርት የሚያካሂዱባት ተስማማ አየር ያላት ከተማ ናት። ግን፡ ይህ ሁሉ በቅርቡ ያከትምለታል ብለው ነው የሚያስቡት፤ ምክንያቱም አንዳንድ ከጥቂት ሣምንታት በፊት በተበተነው ምክር ቤት የተወከሉ የሙሥሊም ወንድማማችነት እንደራሴዎች ብዙ ሰውነት የሚያሳየውን የዋና ልብስ፡ ቢኪኒ እና የአልክሆል መጠጥ እንዲከለከል ሲወያዩ ነበር። ይህ ዕቅዳቸው ገሀድ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ለኤል ጉና እና ሌል ቱሪስት መስህብ ለሆኑ ከተሞጭ ሁሉ ውድቀት በሆነ ነበር። ቱሪዝም በብፅ ኤኮኖሚ ሦስተኛው ዋነኛ ምሰሶ እንደመሆኑ መጠን፡ የቱሪስቶች ቁጥር የሚቀንስበት ሁኔታ የወደቀውን የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ይበልጡን ይጎዳዋል።
በግብፅ አራት ጊዜ ዕረፍትዋን ያሳለፈችው የኔዘርላንድስ ዜጋ የሆነችው አነማሪ ቤከር ወደፊት ወደ ግብፅ ስትሄድ ምንም ዓይነት ገደብ እንዲያርፍባት እንደማትፈልግ ነው የገለጸችው።
« ቢኪኒ መልበስ ወይም አልክሆል መጠጥ መጠጣት ካልቻልኩ ተመልሼ አልመጣም። ግን፡ እዚህ ደስ ይለኛል። ይህ ገደብ ግን ከልክ ያለፈ ነው። »«
በወቅቱ እንደሚታየው ግን፡ ይህ ዓይነቱ ገደብ የሚያርፍ አይመስልም። የቱሪዝሙ ዘርፍ ለሀገራቸው ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን በሚገባ የሚያውቁት አዲሱ ፕሬዚደንት ሙርሲ ባለፈው የሣምንት መጨረሻ ሥልጣናቸውን በይፋ በተረከቡበት ጊዜ ባሰሙት ንግግራቸው የቱሪዝሙ ዘርፍ ከሕዝባዊው ዓብዮት በፊት እንደነበረው ለማጣናከር የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። በግብፅ ቱሪዝም ሚንስቴር ዘገባ መሠረት፡ ሀገሪቱ በ 2011ዓም ከዚሁ ዘርፍ ያገኘችው ገቢ በ 20101 ዓም ከነበረው 30 ከመቶ ቀንሶዋል። እና በመዲናይቱ ካይሮ ሁከት በተነሳ ቁጥር፡ ምንም እንኳን መዲናይቱየቱሪስት መስህብ ከሆኑት የባህር ዳር ከተሞች ብዙ ብትርቅም እና ኤል ጉናን የመሳሰሉት ከተሞች ከካይሮ በጣም የተለዩ ቢሆኑም፡ ቱሪስቶች ከሀገሪቱ እንደሚርቁ ነው የታየው።
ያም ቢሆን ግን፡ አዲሱ ፕሬዚደንት ቃላቸውን እንደሚጠብቁ በኤል ጉና የቱሪዝም መሥሪያ ቤት ተጠሪ አድሃም ማህሙድ እምነቱን ገልጾዋል። ሙርሲ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በኤል ጉና አንድም ሀገር ጎብኙ ጉዞውን አልሰረዘም። እንደ አድሀም ማህሙድ አስተሳሰብ፡ ሙርሲ ከእሥላማዊው ቀነኖ የበለጠ ትኩረሊሰጡት የሚገባ ብዙ ጉዳይ አለ።
« በመዘርዝሩ መጀመሪያ ላይ ስራ አጥነት፡ ድህነት እና ወዘተ ስታገኝ፡ እርግጠኛ ነኝ በሚገባ የሚንቀሳቀስ ኤኮኖሚን ልትነካ አትፈልግም፡ እንዲያውም ተጨማሪ ውጤት ላማግኘት ነው የምትፈልገው። »
የጥልቀት ዋና መምህሩ ኤራሚ ላቲፍ ግን እንደ ማህሙድ ብሩሕ አመለካከት የላቸውም። ፕሬዚደንት ሙርሲ ፖሊሲውን እንደወቅታዊው ሁኔታ የሚቀያይረው የሙሥሊም ወንድማማችነት አባል እንደመሆናቸው መጠን፡ ከአክራሪ ዎች ግፊት ቢያርፍባቸው ለቱሪስቶች የማይመቹ ሕጎችን ሊያወጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው አስታውቀዋል። ግማሹ የኤል ጉና ሕዝብ ልክ እንደ ላቲፍ የክርስትና እምነት ተከታይ ሲሆኑ፡ እስከዛሬ ክርስትያንና ሙሥሊም በሰላም ጎን ለጎን ይየሚኖሩበት ሁኔታም ይቀየር ይሆን በሚል ላቲፍ መስጋታቸው አልቀረም።
« በክርስትና እምነት ተከታዮች አንፃር ብዙ ሕጎችች፡ አብያተ ክርስትያን መገንባትን ወይም ክርስትያንና ሙሥሊሞች እንዲለያኡ የሚያዙ ደንቦች ይወጣሉ ብየ አስባለሁ። የምናውቀው ነገር የለም፡ ግን ፈርተናል። »
እንግዲህ ሁሉ ነገር ጥገኛ የሚሆነው ሙርሲ ቃላቸውን በተግባር በሚተረጉሙበት ሂደት ላይ ይሆናል።
ቪክቶርያ ክሌበር
አርያም ተክሌ
ሒሩት መለሠ