1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መጾም ለጤና

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9 2005

መጾም መራብ ሳይሆን ተፈጥሯዊ የሆነ የአኗኗር ስልት ነዉ ይላሉ የዚህ ሃሳብ አራማጆች። ዓላማቸዉ በየደረጃዉ ተዘጋጅተዉ ለገበያ በሚቀርቡት የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምግቦች ምክንያት ወደአካላችን ገብቷል የሚሉት አላስፈላጊ ንጥረ ነገር እነሱ መርዝ የሚሉትን በተፈጥሯዊ ስልት ከሰዉነት ለማስወገድ ነዉ።

https://p.dw.com/p/198wg
ምስል st-fotograf/Fotolia

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ጾመ ሐዋርያትን በሳምንቱ መጨረሻ አጠናቀዋል፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ ሮመዳንን ከጀመሩ ሳምንት ሞላቸዉ። ይህ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ እንዳለዉ ግልጽ ነዉ። በተቃራኒዉ ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብ መከልከል ለጤና ፋይዳ አለዉ የሚሉ ወገኖች በምዕራቡ ዓለም መጾም ጀምረዋል። የጾም ማዕከሎች ሁሉ ተከፍተዉለትም የገቢ ማስገኛም ሆኗል።  ራስን ከምግብ የማቀቡ ርምጃ ዘዎትር በግል ብቻ የሚደረግ አይደለም። እዚህ ጀርመን አገር ይህን የሚያካሂዱ የተለያዩ ማዕከሎች ይገኛሉ።  Fastenzentrale አንዱ ነዉ።

ክሪስቶፍ ሚኻኤል ቀደም ሲል የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ፓስተር ነበሩ፤ ላለፉት 30ዓመታት ደግሞ የተጠቀሰዉ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ናቸዉ። ሃይማኖታዊዉን ገጽታ በማወቄ ጾም ምን ማለት እንደሆነ እረዳለሁ የሚሉት ሚኻኤል ማዕከሉ የሚያካሂደዉ ግን መነሻዉም ሆነ መድረሻዉ ከዚያ የተለየ መሆኑን ነዉ ያመለከቱኝ። ስለሁኔታዉ ሳነጋግራቸዉ በቅድሚያ ወደማዕከሉ የሚመጡ ሰዎች ሶስት ዓይነት ችግሮች እንዳሏቸዉ ገለጹልኝ፤

«ወደእኛ የሚመጡት ሰዎች አንድም ክብደት መቀነስ በመፈለግ፤ ወይም በጤና እክል አንዳንዶች ደግሞ ከስነልቦና ችግር ወይም ጭንቀት ጋ በተያያዙ በሶስት ምክንያቶች ነዉ።»

በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት ወደማዕከሉ ከሚሄዱት አብዛኞቹ አንድ ሳምንት አንዳንዶች ደግሞ እስከ ሁለት ሳምንት ማለትም ለ14ቀናት ይጾማሉ።  በእነዚህ ጊዜያት ታዲያ አይመገቡም። ራስን ከምግብ ከማቀቡ በተጨማሪም በየዕለቱ የማይታጎል እንቅስቃሴም ይኖራል፤ ሂደቱም እግረ መንገዱን ነፍስን አድሶ መንፈስን ያጠነክራል ባዮች ናቸዉ።

Wasser Wasserhahn Glas
ምስል Fotolia/Elenathewise

 «ሰዎቹ ምንም አይበሉም ግን ይጠጣሉ። የሚጠጡትም ባብዛኛዉ የተለያየ ሻይ ነዉ። ማታ ሲመለሱም የተለያዩ አትክልቶች ተቀቅለዉ በመፍጨት የሚዘጋጀ ሾርባ ይጠጣሉ። ቀኑን ሙሉ ወይም በትንሹ ለስድስት ሰዓታት ያህል እንጓዛለን። ይህ ለጤና ጥሩ ነዉ፤ አንድ ሰዉ በቀን ቢያንስ ከ15 እስከ 20 ኮሎ ሜትር በእግሩ መጓዝ ይኖርበታል። ይህም ሰዉነት መንቀሳቀስን እንዲላመድ ያደርጋል።»

በእሳቸዉ እምነትም እንዲህ ያለዉ ከምግብ ተአቅቦ በሰዉነት ዉስጥ የተጠራቀመና እዚያ ሊኖር የማይገባዉ ማንኛዉም ነገር ያለ መድሃኒት ርዳታ እንዲወገድ ይረዳል።

«ሰዉነታችን በዚህ ጊዜ ራሱን ያጸዳል፤ ያም ማለት ሰዉነታችን ዉስጥ መጠራቀም ሳይገባዉ የተሰባሰበ ነገር ሁሉ መወገድ አለበት። ለዚህም መጾም አንዱ አማራጭ ነዉ፤ ከአመጋገብ፤ ከአየር፤ እንዲሁም ብዙዎች ከሚወስዱት መድሃኒት ሰዉነት ዉስጥ መቆየት የማይገባቸዉ ነገሮች ይኖራሉ፤ እነዚህ መዉጣት አለባቸዉ። አንድ ሰዉ ምንም በማይመገብበት ጊዜ ሰዉነታችን ወዲያዉ ራሱን ለማጽዳት ይጀምራል።»

መቼም አማርጦና እንደተገኘዉ ብዙ መመገብ በተለመደበት ሁኔታ ካለ ምግብ ለቀናት መቆየት ሳይከብድ የሚቀር አይመስልም። እሳቸዉም ብዙዎች እንደማይደፍሩት ነዉ የገለጹልን፤ ወደእነሱ የሚሄዱት አብዛኞቹም ከ35ዓመት በላይ የሆናቸዉ ናቸዉ። እንዲያም ሆኖ በሚደረገዉ ቅድመ ዝግጅት ተበራተዉ ለቀናት የጀመሩትን እንደሚዘልቁበት ነዉ የሚናገሩት፤

 «የመጾም ልምድ ያላቸዉን ሰዎች  ወደእኛ ከመምጣታቸዉ በፊት በቤታቸዉ እንዲጀምሩ ነዉ የምመክራቸዉ፤ ማለትም በትንሹ እንዲመገቡ፤ እንዳያጨሱ፤ አልክሆል ሆነ ቡና እንዳይጠጡ፤ መምጫቸዉ ሲቃረብ ደግሞ ፍራፍሬ ብቻ እንዲበሉ እነግራለሁ፤ ያን ማድረግ ከቻሉ ወደዋናዉ ጾም ለመግባት ብዙ ተራምደዋል ማለት ነዉ። ልምድ የሌላቸዉ ከሆኑም እዚያ እንዲመጡና አካባቢዉን እንዲላመዱ አደፋፍራለሁ፤ እዚያ ምግብ የለም የሚበላም የለም፤ ይህ ማጭበርበርም ሆነ ምትሃት ሳይሆን ሰዉነት ፈቅዶ ራሱን የሚያላምድበት ነገር ነዉ። 

Frau und Hamburger
ምስል Fotolia/Gennadiy Poznyakov

ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የሰዎች አማካኝ እድሜ እየቀነሰ ለመሄዱ ዋናዉ ምክንያት ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ልማድ መሆኑን ሰሞኑን አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል። በዚህ ላይ ደግሞ ማጨስ፣ አልክሆል አብዝቶ መጠጣት ና የሰዉነት እንቅስቃሴ አለማድረግ ለከፍተኛ የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ከመዳረግ አልፎ እድሜን እንደሚያሳጥር ነዉ ጥናቱ ያሳሰበዉ። በአዳጊና ድሃ ሃገራት በምግብ እጥረት የሰዎች ህይወት ማለፍና የህጻናትም ለበሽታ መጋለጥ የየዕለት ክስተት ነዉ። በተቃራኒዉ በምዕራቡ ዓለም ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ ጤናቸዉ የተጓደለዉ አሜሪካዉያኑ ብቻ ሳይሆኑ በፋብሪካ የሚሰናዱና ለረዥም ጊዜ እንዲቆዩ ሲባል  ኬሚካል የሚደረግባቸዉን ምግቦች የሚመገቡ ሁሉ መሆናቸዉ ከዕለት ዕለት እየተገለጸ የመጣ ጉዳይ ሆኗል። ክርስቶፍ ሚኻኤልም ይህንኑ ነዉ የሚናገሩት፤

 «ሰዉነታችን ከማያስፈልጉት ነገሮች ነጻ ሆኖ ሲጸዳ መንፈሳችን ራሱም ይጸዳል፤ ይነቃል። በዛሬ ጊዜ በርካታ ችግሮችን ተሸክመን ነዉ የምንንቀሳቀሰዉ በዚህ ምክንያትም በትክክል ማሰብ ራሱ ይሳነናል። ጀርመንና አዉሮጳ የሚገኙ ወገኖቻችን ተፈጥሯዊነቱን በሳተ የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ ዉስጥ ነዉ የሚኖሩት፤ ይህ ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለዉ ይለያል ብዬ እገምታለሁ። ስለዚህ እነዚህ ወገኖች ወደእዉነተኛዉ ተፈጥሮ እንዲመለሱ ፤ ፀሐይዋንና ዝናቡን እንዲያጣጥሙ፤ የወራጅ ዉሃዉን ድምጽ እየሰሙ እንዲታደሱ፤ በዛፎቹ መካከል እንዲንቀሳቀሱ የእርግቦችን ዝማሬ እንዲያደምጡ እንፈልጋለን፤ እነዚህ ሁሉ ደግሞ መንፈስን ያድሳሉ።»

ከምንም በላይ ለሰዉነት እንቅስቃሴ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን የሚመክሩት የጾም ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ይህ ገንዘብ እንደማያስወጣ ነዉ የሚጠቁሙት። ማንም ሰዉ የሰዉነት እንቅስቃሴ ለማድረግ የግድ እየተከፈለ ይህን አገልግሎት በሚሰጥበት ስፍራ ማለትም ጂም መሄድ አያስፈልገዉም። ረዘም ያለ የእግር መንገድ የመሄድ ልምድ አካልን ብቻ ሳይሆን መንፈስንም እንደሚያድስ ነዉ ከራሳቸዉ ልምድ ተነስተዉ የሚመክሩት። እንደእሳቸዉ አገላለጽም አንድ ሰዉ ፈሳሽ እየወሰደ ካለ ምግብ 40 ቀናት መቆየት ይችላል፤

«ጀርመን ዉስጥ ከምግብ መከልከልን በሚመለከት ሰዎችን የማማከር ኃላፊነት ያላቸዉ ሃኪሞች አንድ ሰዉ አንድ ሳምንት መጾም እንደሚችል ይገልጻሉ፤ ከዚያ በላይ መቆየት የሚፈልግ ደግሞ የሃኪም ክትትል እየተደረገለት ካልሆነ እንዳይሞክረዉ ያሳስባሉ። እኔ ግን ከራሴ ልምድ ተነስቼ ያለ ሃኪም ክትትል 40ቀን ካለ ምግብ መቆየት እንደሚቻልና ችግር እንደማይገጥም እናገራለሁ። ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ እኛ ጋ የሚመጡት አንድ ሳምንት ወይም ሁለት እና ሶስት ሳምንታት በተከታታይ ይጾማሉ፤ አብዛኞቹም ተመልሰዉ በዓመት ዉስጥ ሁለቴና ሶስት ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ ይጾማሉ። ሴቶቹ እኛ ጋ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ቆይተዉ ወደቤታቸዉ ሲመለሱም ባሎቻቸዉ ካላቸዉ እድሜ ሃያ ዓመት ቀንስዉ ወጣት እንደሆኑ እንደሚገልጹላቸዉ ይነግሩናል፤ ያ ደግሞ ያበረታታቸዋል።»

ወደእነሱ ማዕከል ከሚሄዱት 70 በመቶ ያህሉም ሴቶች እንደሆኑ ይናገራሉ ክርስቶፍ ሚኻኢል። ራሳቸዉን ከምግብ ለተወሰኑ ጊዜያት ማቀብን ሰዎች ሲለምዱት ሰዉነታቸዉ ቅልል እንደሚለዉና እንደሚዝናና በዚያ ላይ መንፈሳቸዉ እንደሚታደስና ደስታ እንደሚሰማቸዉም ይገልጹላቸዋል። በአካላቸዉና መንፈሳቸዉ ላይ በሚፈጠረዉ ስሜትም ደጋግመዉ ወደማዕከሉ እንደሚሄዱም ይናገራሉ። ወደዚያ ባይሄዱም በየወሩ ለአንድ ሳምንት የሚጾሙ፤ አንዳንዶችም በሳምንት ዉስጥ የተወሱ ቀናትን ራሳቸዉን ከምግብ የሚከለክሉ አሉ ይላሉ፤ ያ ማለት ደግሞ ዘወትር ከእንቅስቃሴ ጋ የተጎዳኘ መሆኑንም ያስረዳሉ። ለመሆኑ ከፈሳሽ በቀር ምንም ሳይመገቡ በየቀኑ ከ15 እስከ 20 ኪሎ ሜትር በእግርም ሆነ በብስክሌት የሚጓዙ ከሆነ ድካም አይሰማቸዉ ይሆን?

Symbolbild Adipositas Fettleibigkeit
ምስል picture alliance/AP Photo

«አዎ ቀደም ሲል ሰዎች እንዲህ የሚጾሙ ከሆነ ተጋድመዉ ይዉሉ ነበር። አንድ ሰዉ የሚተኛ ከሆነ ጡንቻዉ ይዳከማል፤ ይህ በሚመለከት ስለጾም የሚያማክሩ ሃኪሞች ሰዉ ሲጾም ጡንቻዉ ይዳከማል፤ ሰዉ ሲጾም አቅም ያንሰዋል፤ የሚጾም መተኛት አለበት ሲሉ ይመክራሉ፤ እኔ  ግን ይህን ቀይሬዋለሁ፤ አንድ ሰዉ የሚጾም ከሆነ መንቀሳቀስ አለበት ነዉ የምለዉ፤ ለምሳሌ ወታደሮች አይበሉም ግን ይንቀሳቀሳሉ፤ እየጾመ የሚንቀሳቀስ ሰዉ ጡንቻዉ እንደማይዳከም፤ ወዲያ ወዲህ ባለ መጠን እንደሚጠነክር በተግባር አስረዳለሁ፤ እናም እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ኦ,,, ድጋሚ ለአንድ ሳምንት መጓዝ እችላለሁ፣ ማረፍ አልፈልግም ብለዉ ጥንካሬያቸዉን ይገልጹልናል።»

እኔም በአንድ ወቅት አሉ ክርስቶፍ ሚኻኢል ዉሃ ብቻ እየጠጣሁ ከሰሜን ጀርመን ተነስቼ ኦስትሪያ ድረስ ተጉዣለሁ፤

«አንድ ጊዜ እኔ ከሰሜን ባህር እስከ አልፕስ ተራሮች ድረስ ተጉዣለሁ፤ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ዉሃ ብቻ እየጠጣሁ። አልፕስ ቲገን ዜ ስደርስ ደከመኝ የነበረኝን ኃይል ሁሉ ጥቅም ላይ አዉዬ ጨርሻለሁ፤ እረፍት ማድረግ ነበረብኝ። እኛ ጋ ከሚመጡ አንዳንዶቹ ቀኑን ሲጓዙ ይዳከሙና ማታ ነገ በፍጹም አልነሳም ከእናተም ጋ አልጓዝም ይሉናል፤ ተኝተዉና እረፍት አድርገዉ ሲነሱ ሰዉነታቸዉ በራሱ መንገድ ኃይል አጠራቅሞ አቅም አግኝተዉ በማግስቱ ይነሳሉ።»

ሰዎች እንዲህ ያለዉን ጾም በሚጾሙበት ጊዜ በሶስተኛዉ ቀን ሰዉነታቸዉ ይዳከማል እንደሚባል የሚናገሩት የማዕከሉ ኃላፊ ያ የሚሆነዉ ሰዉነት ዉስጥ የተጠራቀመዉ ከምግብም ሆነ ከመድሃኒት የተገኘ መርዝ ሲወጣ ነዉ ብለዉ እንደሚያምኑም ይገልጻሉ። ያ ሲወጣ ደግሞ ሰዉነት ተመልሶ ጥንካሬ እንደሚኖረዉና እንደሚታደስም ከልምዳቸዉ በመነሳት ያስረዳሉ። ምክራቸዉም በተለይ ከጤናማ አመጋገብ ጉድለት በሚመጣ ዉፍረትና የተለያዩ የጤና እክሎች የሚጨነቁ በተቻላቸዉ በእግር በመጓዝና አትክልትና ፍራፍሬ በመመገብ ጤናቸዉን መጠበቅ የሚችሉበት አንዱ ስልት እንደሆነም ይመክራሉ።

ሰዎች አማርጠዉ የሚበሉት እያለ ለጤና ጠንቅ ከሆነባቸዉ አመጋገብ ሰዉነታቸዉን ለማጽዳት ጾምን ለመላመድ ስለመሞከራቸዉ ለሰጡን ማብራሪያ ክሪስቶፍ ሚኻኢልን ከልብ እናመሰግናለን። ሁኔታዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በአንዳንድ አካባቢዎችም ሆነ በሌሎች በምግብ ሰብል ራሳቸዉን ባልቻሉ ባዳገታቸዉ ሃገሮች የሚኖሩ ወገኖችን አይመለከትም። እዚያ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ሚከብዳቸዉ ሞልተዋልና።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ