1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መጤዎች ወደ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብና ልማት

ሐሙስ፣ መስከረም 16 2000

ዛሬ በምዕራቡ ዓለም አያሌ የአፍሪቃ፣ የእሢያ፤ እንዲሁም የደቡብና የማዕከላዊ አሜሪካ ተወላጆች ይኖራሉ። ለተሻለ የኑሮ ሁኔታ ወይም በፖለቲካ ምክንያት የትውልድ ሥፍራቸውን እየለቀቁ በመፍለስ በውጭ የሚኖሩት መጤዎች ቤተሰብ ለመደገፍ የሚልኩት ገንዘብ በሰፊው ነው የጨመረው።

https://p.dw.com/p/E0cg
ምስል picture-alliance / OKAPIA KG, Ge

ገንዘቡ ለድሆች ቤተሰቦች ሕልውናና ለኤኮኖሚ ዕድገት ምን ያህል ጠቅሟል፤ ቢጓደልስ ተጽዕኖው እስከምን ድረስ ነው? ይህ ጥያቄ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዚህ በጀርመንና በሌሎች ምዕራባውያን አገሮችም ከልማትና ከልማት ፖሊሲ አቀራረጽ አንጻር ይበልጥ ክብደት እያገኘ መሄዱ አልቀረም። በበለጸገው የዓለም ክፍል በሰፊው ሰፍረው የሚገኙት መጤዎች ወደ ትውልድ አገሮቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ለብዙዎች ታዳጊ አገሮች ሁለተኛው ታላቅ የፊናንስ ምንጭ ነው።
በዓለም ባንክ ግምት ባለፈው 2006 ዓ.ም. ብቻ በዓለምአቀፍ ደረጃ በዚህ መልክ የተላከው ገንዘብ ከ 250 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል። የገንዘቡ መጠን በያመቱ 30 በመቶ እያደገ መምጠቱ ሲነገር ዓለምአቀፉን የልማት ዕርዳታ መብለጡም ሌላው ይፋ ሃቅ ነው። መጤው የሚያስተላልፈው ገንዘብ የትውልድ አገሩን ኤኮኖሚ በማሳደግና የችግረኛውን ተረጂ ሕዝብ ፍላጎት በማሟላት ጠቃሚ አስተዋጽኦ አለው። ላኪና ተቀባዩን ከባንክ አገልግሎት መረብ ጋር በማስተሳሰር የፊናንስና የማሕበራዊ ታቃፊነቱን የሚያረጋግጥም ነው።

በውጭው ዓለም የሰፈሩ መጤዎች ወደ አገር የሚልኩት ገንዘብ የእሢያን፣ የላቲን አሜሪካንና የካራይብን ያህል በአካባቢ ኤኮኖሚ ላይ ያለው ጠቃሚ ድርሻ በሌላ ቦታ ጎልቶ አይታይም። ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ላቲኑ አካባቢ የተሻገረው ገንዘብ ከ 60 ቢሊዮን ዶላር በልጦ ነበር። አብዛኛው፤ ማለት ሁለት ሶሥተኛው የመነጨውም ከዩ-ኤስ-አሜሪካ ሲሆን በጥቅሉ ቀጥተኛው የውጭ የመዋዕለ-ነዋይና መንግሥታዊው የልማት ዕርዳታ ተጣምሮ እንኳ አይደርስበትም። በስድሥት የላቲን አሜሪካና የካራይብ አገሮች መጤው የሚልከው ገንዘብ ከብሄራዊው አጠቃላይ ምርት ከአሥር በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ለመያዝ ሲበቃ የዶላሩ ፍሰት ከሞላ-ጎደል በሁሉም የአካባቢው ሃገራት ከውጭ ከሚገባው ምርት ሁሉ ትልቁ ሆኗል።

በገንዘቡ ላይ ያለው ጥገኝነት ማደግ

በጉዳዩ ጥናት በማካሄድ ቀደምቱ የሆነው የኢንተር-አሜሪካ የልማት ባንክ ዘርፍ በአካባቢው ቀደምቷ ወደሆነችው ወደ ሜክሢኮ በ 2006 የገባው ገንዘብ ብቻ 26 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቷል። እርግጥ የሜክሢኮ ፈላሾች በብዛት ሰፍረው የሚገኙት በዩ-ኤስ-አሜሪካ እንደመሆኑም መጠን 95 በመቶው ገንዘብ የፈሰሰው ከዚያው ነው። ከአሜሪካ በዚህ መልክ የተሻገረው አብዛኛው ገንዘብ ያመራው ደግሞ ወደ እሢያ ነው። ለምሳሌ 26 ቢሊዮን ወደ ሕንድ፣ 14 ቢሊዮን ወደ ፊሊፒን፣ 23 ወደ ቻይና! በገንዘብ ማሸጋገሩ ተግባር ይበልጥ የታወቀው የፊናንስ አገልግሎት ተቋም ዌስተርን ዩኒየን ሲሆን ኢንተርኔት ከተስፋፋ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ኦን-ላይን የገንዘብ ሽግግርም አማራጭ እየሆነ መጥቷል።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለምም ቢሆን ቤተስንና ወገንን ለመደገፍ ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በፍጥነት እያደገ ነው የመጣው። ለብዙዎች የሕልውና መሠረት ከሆነ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው። እንደ አብነት ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ ባለሃብት አገሮች የሚኖረው የአገሪቱ ተወላጅ የሚልከው ገንዘብ ባይኖር ብዙዎች ጾም አዳሪ በሆኑ፤ አያሌ ሕጻናትም ትምሕርቤት ለመሄድ ባልቻሉ ነበር። ይህ ገንዘብ በተመሳሳይ ሁኔታ በሚገኙ አገሮች ኤኮኖሚ ላይም አነሰም-በዛ ተጽዕኖ እንዳለው አያጠራጥርም። እርግጥ በዚህ በጀርመን የሚገኝ የልማትና የሙያ ሃይል የሥራ ቡድን ባልደረባ ካሪን ሉትሰ እንደሚሉት የቤተሰብ ሕልውና ነው ዛሬም ዓበይቱን ድርሻ ይዞ የሚገኘው።

መጤዎች ወደየአገሩ የሚያሻግሩት ገንዘብ ለብዙዎች የሕልውና መሠረትና ለብሄራዊው የኤኮኖሚ ዕድገትም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጠቃሚ ይሁን እንጂ በሌላ በኩል በሆነ ምክንያት ቢሰናከል ወይም ቢተጓጎል ከባድ ችግር ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ ነው። የተቀባዩ ጥገኝነት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። ከውጭ የሚላከው ገንዘብ ብዙዎች ቤተሰቦችን በመደገፍ የሕብረተሰብ ችግርን ማቃለሉ ግልጽ ቢሆንም አንዳንድ ዜጎችን ጥገኛ በማድረግ አምራች እንዳይሆኑ አድርጓል ባዮችም አልታጡም። ይሁንና ድጋፉን የሚተካ አማራጭ አለመኖሩ ትችቱን ብዙም ክብረት አይሰጠውም።

በልማት መስኮች የማተኮሩ አስፈላጊነት

እርግጥ አብዛኛው የሚላከው ገንዘብ በንግድ ወይም በሌላ የኤኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ በሥራ ላይ ከመዋል ይልቅ ቤተሰብን በመደገፍ የተወሰነ በመሆኑ ለኤኮኖሚ ዕድገት ያለው ድርሻ ከግዙፍ መጠኑ አይነጻጸርም። እናም ይህ ቢለወጥ ይበጃል የሚለው ድምጽ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በውጭው ዓለም ጠበብትና ፖለቲከኞች ዘንድ ይበልጥ ትኩረት እያገኘ መሄዱ አልቀረም። በዓለም ላይ ዛሬ 200 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉ የታዳጊው ዓለም ፈላሾች እንደሚኖሩ ይገመታል። እነዚህ ሁሉ በአንድ ቦታ ተሰብስበው ቢኖሩ ስፍራው በምድር ላይ አምሥተኛ ትልቅ አገር ሊሆን በቻለ ነበር። በቀላሉ የማይታይ ምንጭ ነው።

የዚህን ሃያል ጠቀሜታ በሚገባ ያጤኑ በልማት ፖሊሲው ዘርፍ የሚገኙ ምዕራባውያን ፖለቲከኞች ገንዘቡ ለአገር ግንባታም ቢውል ምንኛ በጠቀመ ባዮች ናቸው። በዚህ በጀርመን በታላቋ ፌደራል ክፍለ-ሐገር በኖርድራይን ቬስትፋሊያ የመጤዎች ከሕብረተሰብ መቀላቀል ጉዳይ ሚኒስትር አርሚን ላሼት እንደሚሉት ወደ ትውልድ አገር የሚሻገረው ገንዘብ ከግል ፍጆት ባሻገር በከፊል እንደ ካፒታል ሥራ ላይ ቢውል ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ገንዘብ ላኪው ከቤተሰቡ ዓባላት ለአንዱ በራሱ መቋቋም እንዲችል ብድር ወይም የፊናንስ ድጋፍ ቢሰጥ፤ ከገንዘቡ ጋርም ዕውቀቱን ቢያሸጋግር ይበልጥ የሚመረጥ ነው። እርግጥ ተግባሩ የስኬት ዕድል አለው-የለውም በቅድሚያ ጠንቅቆ ሊጤን ይገባዋል።

የመንግሥታቱ ትኩርት ጎልቶ አለመታየት

በሌላ በኩል አገሩን በሥራ ፍለጋና ሌላ ምክንያት የለቀቀው የታዳጊው ዓለም ተወላጅና ተከታይ ትውልዱ የሚልከው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ይሁን እንጂ ነዋዩ በሚደርስባቸው አገሮች ጉዳዩ በፖለቲካ ደረጃ የሚገባውን ያህል ትኩረት ተሰጥቶታል ለማለት አይቻልም። ይሄው ለምሳሌ በሌሶቶ ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አንጻር 14 በመቶ ድርሻ አለው። በፊሊፒንና በሊባኖስም ከሞላ-ጎደል የሚመሳሰል ነው። የሆነው ሆኖ የየሃገራቱ መንግሥታት ቸልታ ያስገረማቸው የጀርመኗን ፌደራል የኤኮኖሚ ተራድኦ ሚኒስቴር ምክትል ባለሥልጣን ካሪን ኮርትማንን የመሰሉ የምዕራቡ ዓለም ፖለቲከኞች አልታጡም።

“በታዳጊዎቹ ሃገራት ከመንግሥታት፣ ከፓርላማ ወይም ከእንደራሴዎች ጋር እስካሁን ባደረግኩት ንግግር ለመሆኑ ወደ አገርዎ የፈለሱ ዜጎቻችን ምን እየሰሩ ነው? ሁኔታቸው እንዴት ነው? ግንኙነትስ አለዎት? እንዴት ነው በልማት ትብብራችን ልናሳትፋቸው የምንችለው? ብሎ የጠየቀኝ አንድም አላጋጠመኝም። እኛ ግን እነርሱን የምንመለከተው ለምንተራበራቸው ታዳጊ ሃገራት እጅግ አስፈላጊ የልማት ሃይልና በመካከላችንም ድልድይ ዘርጊዎች አድርገን ነው። ሆኖም ግን እስሳሁን ልብ ያላቸው የለም”ይላሉ።

እርግጥ ከገንዘብ ላኪዎች በኩል መዋዕለ-ነዋይን በሥራ በማዋል ለልማት ድርሻ ከማድረግ ቆጠብ እንዲሉ መንስዔ የሆኑ ብዙ ምክንያቶች አሉ። የየአገሩ የፖለቲካና የባንክ ስርዓት አለማስተማመን አንዱ ችግር ነው። ይህም የታዳጊ ሃገራት የባንኮች ስርዓትና የብድር ዘይቤ ዓመኔታ ሊሰጠው በሚችል መጠን መለወጡን ይጠይቃል። ዛሬ የላኪውንም ሆነ የተቀባዩን ያለማወቅ ድክመት በመጠቀም ትርፍ የሚያጋብሱት የፊናንስ አማካዮች ብዙዎች ናቸው። ላኪው ግብር ከፍሎ ያሻገረው ገንዘብ በተቀባዩ ዘንድ እንደገና የሚቀረጥበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ይህ መሻሻልን የሚጠይቅ ራሱን የቻለ ችግር ነው። ለማንኛውም አንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ ከዚህ ሻገር በማለት እንደ አማራጭ መጤዎች የሚፈልጓቸውን ጭብጥ ፕሮዤዎች ለማራመድ ገንዘብ የሚያስገቡበት ተቋም ቢቋቋም ይበጃል ይላሉ። ግን እንደ ካሪን ኮርትማን ከሆነ ሃሣቡን ገቢር ማድረጉ ቀላል ነገር አይደለም።

እኔ በበኩሌ ድጋፉ የሚያስፈልገው ዘመድ ካለኝ ገንዘቡን ወደዚህ መሰሉ ተቋም አላስተላልፍም፤ ይህን ሰብዓዊ ግምት ለመረዳት ምንም አያዳግትም ባይ ናቸው። ግን ሌላ ነገር አለ። ለፊናንስ ሽግግሩ የሚከፈለው ግብር ቢቀንስ የሚላከውን ገንዘብ በጅምላ ለማሳደግ ይቻላል። እርግጥ ገንዘቡ በምን ተግባር እንደሚውል ግልጽ ከሆነ! ወሣኙ ነገር ይሁንና ድጋፉ ከቤተሰብ አልፎ በአገር ልማት ላይ መዋል መያዙ ነው። ኮርትማን እንደሚያስገነዝቡት። የወቅቱ ተጨባጭ ሃቅ በገንዘብ ሽግግሩ ረገድ ግልጽ የባንኮች ወይም ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች አሠራር አለመኖሩና የሚጠይቁት ግብርም ከፍተኛ መሆኑ ነው። ላኪው ከገንዘቡ አንጻር ከ 10 እስከ 13 በመቶውን ድርሻ መገበር ይኖርበታል። እንግዲህ የንግዱ ተጠቃሚዎች ዌስተርን ዩኒየንን የመሳሰሉት ባንኮች፣ ፖስታ ቤቶችና ሌሎች ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች መሆናቸው ነው።