1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መካከለኛው አፍሪቃ በምርጫ መዳረሻ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14 2008

መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮችን እና ዕጩ ፕሬዚዳንቶችን አወዳድራ ለመምረጥ የቀራት በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ነው። ሀገሪቱ በቅርቡ ያሻሻለችውን አዲስ ሕገመንግሥትም በአብላጫ ድምጽ አጽድቃለች። የመካከከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ የወደፊት ፕሬዚዳንት ማን ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ተወዳዳሪ የለም።

https://p.dw.com/p/1HTRf
Zentralafrikanische Republik Wahlkampf
ምስል Getty Images/AFP/M. Longari

[No title]

መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ፦ ነፃነቷን ከፈረንሣይ ከተቀዳጀች ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ተቆጥሯል። ሆኖም ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሀገሪቱ ከምርጫ ይልቅ ብጥብጥና ኹከትን ይበልጡኑ ስታስተናግድ ቆይታለች። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1960 ዓም ነፃነቷን ባገኘችው መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ከጥቂት ቀናት በኋላ፤ ታኅሣሥ 17 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ ምርጫ ይከናወናል። የመዲናይቱ ባንጉዊ ከንቲባ ሲልቬስተር በምርጫው የለውጥ ተስፋ ሰንቀዋል።

«እዚህ በተደጋጋሚ ያየነው ተመሳሳይ ነገር ነው። የሀገሪቱ ኹኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ መጥቷል። እናም አሁን ፍጹም ምኞታችን ለዚህች ሀገር ጥሩ መሥራት የሚችል የሆነ ሰውን መምረጥ ነው።»

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፍራንሲስ ቦዚዜ
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፍራንሲስ ቦዚዜምስል picture-alliance/AP Photo/B. Curtis

ይኽ «የሆነ ሰው» የተባለው ማን ሊሆን እንደሚችል ግን ለአብዛኛው የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ነዋሪ ግራ የሚያጋባ ይመስላል። ለፕሬዚዳንትነት ምርጫ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ሰዎች 30 መድረሳቸው ተጠቅሷል። እናም አዲሱ ፕሬዚዳንት ማን ሊሆን እንደሚችል በውል ባይታወቅም፤ ሀገሪቱ ግን አንድ ነገር ላይ እርግጠኛ ናት። በመፈንቅለ-መንግሥት ከሥልጣናቸው የተነሱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፍራንሲስ ቦዚዜ ለፕሬዚዳንትነት ፈጽመው መወዳደር አይችሉም። ይኽን የሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በግልጽ አስቀምጦታል። ሀገሪቱን ለ10 ዓመታት የገዙት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ድርጊቱን ኮንነውታል።

«ይኼ የነበረኝን የሥልጣን ክብር የሚጋፋ የክፋት ውሳኔ ነው። የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ኹኜ ለ10 ዓመታት አገልግያለሁ። አሁን ግን ማንም ሊያውቀኝ አይችልም። በቃ እንደ አልባሌ ነገር ተጥያለሁ።»

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፍራንሲስ ቦዚዜ ከሥልጣናቸው የተነሱት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም. የያኔዎቹ ዓማፂያን ሀገሪቱንr በመቆጣጠራቸው ነበር። ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ የሚገኘው የዓለም አቀፍ እና የአካባቢ ጥናት ተቋም በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ (GIGA) ተመራማሪው ቲም ግላቪዮን የቀድሞው ፕሬዚዳንት እንዳይወዳደሩ መወሰኑ ትክክለኛ ነው ይላሉ።

«ፍራንሲስ ቦዚዜ የተናገሩት የሚገርም ነው። እንደውም እንደሚመስለኝ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን ግፍ የተፈፀመባቸው አንዳን ዜጎች የሳቸውን አገዛዝ የክፋት እያሉ ነው የሚገልጹት።»

ምርጫ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ
ምርጫ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክምስል picture-alliance/dpa/J.-M. Issa

ፍራንሲስ ቦዚዜ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፀረ-ባላካ የተሰኘው የክርስቲያን ሚሊሺያ ቡድን ሙስሊሞችን በጭካኔ እንዲገድል እና እንዲያሳድድ ነገሮችን አባብሰዋል በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀብ ጥሎባቸዋል። ካለፉት ሦስት ዓመታት አንስቶ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ሙስሊም አማፂያን እና ክርስቲያን ሚሊሺያዎች እርስ በእርስ ይፋለማሉ። ዓማፂያኑ ርእሰ-ከተማ ባንጊን ከተቆጣጠሩ ከ2013 ዓ.ም. ወዲህ በሀገሪቱ ተደጋጋሚ ደም አፋሳሽ ግጭት ሲከሰት ቆይቷል። ግጭቱን በመፍራትም ወደ 4, 7 ሚሊዮን ነዋሪ ቤት ንብረት ቀዬውን ጣጥሎ ስደት መግባቱም ይነገራል።

ከጥቂት ቀናት በኋላ በሀገሪቱ በሚከናወነው ምርጫ የሚሳተፉ የምክር ቤት ተወካዮች እና የፕሬዚዳንቶች ዕጩዎች ሠላም አስፍነን ሀገሪቱን ዳግም በመገንባት እናበለፅጋታለን ሲሉ ቃል ገብተዋል። ይኽ ቃል በሁሉም ተመራጮች ሊባል በሚችል መልኩ ተደጋግሟል። በእርግጥ ማን ምርጫውን እንደሚያሸንፍ፤ ምርጫውም በሠላም ተከናውኖ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛን የሚተካው ማን እንደሆነም ከወዲሁ መናገር ይከብዳል። ለሁሉም በጣት የሚቆጠሩ ቀናት መጠበቅ ግድ ነው።

ክርስቲኔ ሀሪዬስ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ