1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕዝባዊ ተቃውሞ በሊቢያ

ረቡዕ፣ የካቲት 9 2003

በሰሜን አፍሪቃ የተቀጣጠለዉ ህዝባዊ አብዮት ወደተለያዩ አገራትም እየተዛመተ በመሄድ ላይ ነዉ።

https://p.dw.com/p/R1ai
ቤንጋሺ ከተማምስል picture alliance/Lonely Planet Images

አመፁ ወደሊቢያም ዘልቆ ወደአምስት መቶ የተገመቱ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በመንግስት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት በመዉጣት በእስር ላይ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንዲለቀቁ ጠይቀዋል። በሊቢያ የቤንጋዚ ወደብ ከተማ መንግስትን በመቃወም ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ አደባባይ በወጡ ተቃዋሚዎች፡ በፖሊስ እና በመንግስት ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ አስራ አራት ሰዎች ቆሰሉ።በጋዜጠኞች ዘገባ መሰረት፡ ተቃውሞው የተጀመረው አንድ መንግስትን የተቸ የመብት ተሟጋች ላጭር ጊዜ ከታሰረ በኋላ ነበር። ፖሊስ ድንጋይ የወረወሩ ተቃዋሚዎችን በውኃ መርጫ፡ በሚያስለቅስ ጢስ እና በጎማ ጥይት በትኖዋል። አንድ የከተማይቱ ሀኪም ቤት ዋና አስተዳዳሪ እንዳስታወቁት፡ ከግጭቱ በኋላ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሰላሳ ስምንት ሰዎች፡ የፖሊስ መኮንኖች ጭምር ህክምና ተደረጎላቸዋል። የአውሮጳ ህብረት ሊቢያ ሀሳብን በነጻ መግለጽን እንድትፈቅድ አሳስቦዋል። በሌላይቱ ዐረባዊት ሀገር የመንም በመንግስቱ አንጻር ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሎ ውሎዋል። በመዲናቱ ሰንዓ የሀገሪቱን መንግስት በሚቃወሙ እና በፕሬዚደንት አሊ ሳላህ ደጋፊዎች መካከል ዛሬ ብርቱ ግጭት ተፈጠረ። በግጭቱ አራት ሰዎች ተጎድተዋል።