1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያ፥ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ

ሰኞ፣ ነሐሴ 7 2004

ከአርባ ዓመታት በላይ በአንድ ግለሰብ አምባገነናዊ አገዛዝ ስር የቆዩት ሊቢያውያን በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር ላይ ይገኛሉ። በነፃ ሂደትም የምክር ቤቱን ፕሬዚዳንት ሾሞዋል። በቅርቡ ዲሞክራሲያዊ ሕገ-መንግስት ተረቆ ሂደቱ እንደሚፋጠን የመነገሩን ያህል፤ ሊቢያን የፀጥታ እና የእስላም አክራሪነት ችግርም ያሰጋታል እየተባለ ነው።

https://p.dw.com/p/15p18
ምስል Reuters

ከአርባ ዓመታት በላይ በአንድ ግለሰብ አምባገነናዊ አገዛዝ ስር የቆዩት ሊቢያውያን በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር ላይ ይገኛሉ። በነፃ ሂደትም የምክር ቤቱን ፕሬዚዳንት ሾሞዋል። በቅርቡ ዲሞክራሲያዊ ሕገ-መንግስት ተረቆ ሂደቱ እንደሚፋጠን የመነገሩን ያህል፤ ሊቢያን የፀጥታ እና የእስላም አክራሪነት ችግርም ያሰጋታል እየተባለ ነው። የዛሬው ማኅደረዜና ክፍለጊዜ ያተኩርበታል።

ሊቢያውያን አርባ ዓመታትን አስቆጥረውም ቢሆን የማይታሰብ ይመስል የነበረውን ክስተት ዕውን አድርገዋል። የኮሎኔል ሙኣማር አል ጋዳፊ የአንድ ሰው ጨቋኝ አገዛዝን ገርስሰው የዲሞክራሲን አቡጊዳ ቢያንስ ለሶስተኛውም ትውልድ ቢሆን ማስቆጠር ይዘዋል። ያ ሁሉ ሲከናወን ታዲያ መላ ሊቢያ ዘመኑን ሙሉ አንቀላፍቶ ነበር ለማለት አያስደፍርም።

በነፃ ምርጫው ሕዝቡ ተደስቶ
በነፃ ምርጫው ሕዝቡ ተደስቶምስል picture-alliance/dpa

የማይሆን የመሰለው እውነት መሆን መቻሉን አሳይቶ በሊቢያውያን ታሪክ ተመዝግቦ አልፏል። እስከዚያው ድረስ ግን ሊቢያዊው ጨቅላ የወጣትነት ዘመኑን አሟጦ ሌላ ወጣት ሊቢያዊ በእግሩ ተክቷል። የጎልማሳነት ዘመኑንም እስኪያስቆጥር ድረስ በዚያች ሀገር የሚያውቀው አንድ ሰው እና ግብራቸውን ብቻ ነበር። የዘመናት መሪው ሙኣማር አል ጋዳፊን እና ፈላጭ ቆራጭ፣ አምባገነን የ40 ዓመቱን አስተዳደር። ዛሬ ግን ሊቢያውያን ከአራት አስርት ዓመት በኋላም ቢሆን ለሶስተኛው ትውልድ ሌላ ሰው እና ሌላ አስተዳደር ይዘው ብቅ ብለዋል። ብዙዎች ሂደቱን ዲሞክራሲያዊ ሲሉም አሞካሽተውታል። በተለይ ውድ ልጃቸውን በጋዳፊ ጦር ላጡት ለእኚህ ባልቴት ሂደቱ አልደርቅ ያለ እምባቸው ማበሻ ሆኗል።

«ዛሬ የልጄን በቀል ተወጥቻለሁ። ምንም እንኳን ልጄ በጋዳፊ ጦርነት ቢገደልብኝም ዛሬ በጣም ደስ ብሎኛል። ለዚህች ሀገር ያለኝን እጅግ ውድ ነገር ለግሼያለሁ። ደስተኛ ሆኜ በሠማዕታት አደባባይ ቆሜያለሁ። ለሊቢያ ሠላምታ እያቀረብኩ ነው።»

የሊቢያ ምክር ቤት ስልጣን ሲረከብ እንደባልቴቷ ሁሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያን ዲሞክራሲ ናፋቂዎች በሠማዕታት አደባባይ ተሰባስበው ደስታቸውን ሲገልፁ ነበር ያመሹት። ያች ልዩ ቀን ላይ ለመገኘት ብዙዎቹ ተገድለዋል፣ በርካቶቹ ተሰቃይተዋል፣ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል። የባልቴቷ እንባ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያን እናቶች እምባ ማሳያ ነበር። ታዲያ የእነዚያ እናቶች እንባ እንደዘበት ፈሶ እንደማይቀር አዲሱ የሊቢያ መንግስት ስልጣን በያዘበት ምሽት ነበር ማስተማመኛ የሰጠው። የብሔራዊ ሽግግር ሸንጎው ሃላፊ ሙስጣፋ አብዱል ጃሊል፥

«ልጆቻችን ህይወታቸውን መስዋዕት ላቀረቡበት ዓላማ ስኬት በቆራጥነት ለመቆማችን በፈጣሪ ስም ቃል እንገባለን። ሕዝባችን ያነቃቃውን መነሳሳት ስኬታማ ለማድረግ፤ እንዲሁም የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና አንድነት ለማስጠበቅ በፈጣሪ ርዳታ ወደፊት እንቀጥላለን።»

በምርጫው ምሽት
በምርጫው ምሽትምስል Reuters

ይህ ዲሞክራሲያዊ ሂደትን የተከተለ ነው በሚል የተወደሰው የሊቢያ የስልጣን ሽግግር ባሳለፍነው ረቡዕ የምክር ቤቱን ፕሬዚዳንት በመምረጥ በሊቢያ አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን አብስሯል። ዶክተር ማህሪ ታደለ ማሩ በደህንነት ጥናት ተቋም በእንግሊዘኛ ምህፃሩ ISS በተለይ በአፍሪቃ ግጭት ማስወገድን በተመለከተ የፕሮግራም ሃላፊ ናቸው። ሊቢያ በእርግጥም እንደተባለው ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እያቀናች ነው ይላሉ።

የሊቢያ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር የመወደሱን ያህል በብዙዎች ዘንድ ስጋት ማጫሩ አልቀረም። በመጀመሪያው የሊቢያ የምክር ቤት ምርጫ በአሸናፊነት የወጣው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ማህሙድ ጂብሪል የሚመሩት ለዘብተኛ እስላማዊ ጥምር ሀይል ነው። በእርግጥ 200 መቀመጫዎች ባሉት ምክር ቤት ውስጥ 120ው አባላት ከየትኛውም ፓርቲ ያልወገኑ ነፃ ተመራጮች እንደሆኑ ተገልጿል። ያም ቢሆን እስልምናን የሚያጠብቁ ሀይላት በምክር ቤቱ የበላይ ለመሆን መጣራቸው አይቀርም ሲሉ ደራሲና የሊቢያ ጠበብቱ ጀርመናዊው ኩርት ፔልዳ ለዶቸ ቬለ ገልፀዋል።

«እስልምናን የሚያጠብቁት በብሔራዊ ምክር ቤቱ አብላጫውን ቁጥር ለመያዝ፤ ያ እንኳን ባይቻል ዋነኛውን ሚና ለመጫወት በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ ያለምንም ጥርጥር ነፃ የሆኑትን የምክር ቤት አባላት ከጎናቸው ሊያሰልፉ ይችላሉ።»

በብሔራዊ ጉባኤው ከተሰባሰቡት 200 የምክር ቤት አባላት መካከል 113ቱ የኮሎኔል ጋዳፊ የረዥም ዘመን ተቃዋሚ የነበሩ ፖለቲከኛን የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሲሉ ሰይመዋል። ከሶስት ሳምንታት ግድም በኋላ ደግሞ ይኸው ምክር ቤት ጠቅላይ ሚንስትሩን እንደሚመርጥ ይጠበቃል። ጊዜ ሳይፈጅም ዲሞክራሲያዊ ሕገ-መንግስት በሊቢያ ተረቆ ይፀድቃል ተብሏል። እንዲያም ሆኖ ታዲያ እንደጀርመናዊው ተንታኝ ሁሉ ኢትዮጵያዊው ምሁር ዶክተር መሃሪ የእስላም አክራሪነት በሊቢያ ዲሞክራሲ ላይ ስጋት ፈጥሯል ይላሉ።

በምርጫው ዕለት ወታደር በጥበቃ ላይ
በምርጫው ዕለት ወታደር በጥበቃ ላይምስል DW/E.Zuber

ከእስላም አክራሪነት ስጋት ባሻገር በሊቢያ የአካባቢያዊ እና የጎሳ ችግርም አንዱ መሰናክል ሊሆን ይችላል ተብሎ ተሰግቷል። ሊቢያ ከጣሊያን ቅኝ ግዛት በፊት ራሳቸውን በቻሉ ሶስት ግዛቶች በተናጠል ነበር የምትተዳደረው። ሲሬናይካ፣ ፌሳን እና ትሪፖሊ የተባሉት ነፃ ግዛቶች ራሳቸውን የአብዮታዊው መሪ ብለው በሾሙት ኮሎኔል ሙኣማር ጋዳፊ ነው ተጠቃለው በአንድ ሊቢያ ስር የሆኑት። ይህ አካባባያዊ እና ሀይማኖታዊ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል ይላሉ ዶክተር መሀሪ።

ሊቢያ ቀደም ሲል ከነበራት ታሪክ አንፃር ፌዴራላዊ አስተዳደርን ልትከተል ትችላለች ሲሉ ምሁሩ አክለው ገልፀዋል። በእርግጥም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር እስከ 1963 ድረስ ንጉስ ኢድሪስ ሀገሪቱን በፌዴራላዊ አስተዳደር ነበር ሲመሩ የቆዩት። በሊቢያ ዲሞክራሲ የወደፊት ዕጣ ወሳኝ ከሆኑት እውነቶች መካከል በጦርነቱ ወቅት በምዕራባውያኑ የጦር ጀቶች ፍርስርሱ የወጣው መሰረተ-ልማት ዋነኛው ነው። ይህ መሰረተ ልማት በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በምስራቁ ቤንጋዚ በጋዳፊ ዘመን ፍፁም ተረስቶ ነበር።

«በጋዳፊ ዘመን ተዘንግቶ የቆየው መሠረተ-ልማት በራሱ አንድ ከፍተኛ ችግር ነው። የነዳጅ ማውጣት እንቅስቃሴው በሽግግር ዘመኑ በጥሩ ሁኔታ በመከናወን ላይ ይገኛል። ሆኖም የወደፊት ስኬቱ በመዋዕለ-ንዋይ ፍሰቱ እና በነዳጅ ማውጫ ማሽኖቹ ወጪ ላይ የሚመሰረት ይሆናል። እዚያ አካባቢ አንድ ነገር መደረግ አለበት፤ አለበለዚያ የሊቢያ የነዳጅ ዘይት እንቅስቃሴ በድጋሚ ቀውስ ሊከተለው ይችላል።»

በርካታ አካባቢዎች ሚሊሺያዎች ትጥቅ ያለመፍታቸው ጉዳይም ለሊቢያ ፖለቲከኞች ሌላው ራስ ምታት ነው። አብዛኛው ህብረተሰብ መሳሪያ የታጠቀ መሆኑ ማዕከላዊው አስተዳደር ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እንዳይችል ሳያደርገው አልቀረም። በሲሬናይካ የቤንጋዚ አካባቢ የሚገኙ ሚሊሺያዎች ከወዲሁ ነፃ ሆነው የመተዳደር ስልጣን እንዲኖራቸው ጥያቄ እያነሱ ነው። ይህ በእርግጥም የትሪፖሊ መንግስት ወደፊት መልስ ሊያዘጋጅበት የሚገባው ጉዳይ ነው።

በእነዚህ ሁሉ አሳሳቢ ጉዳዮች መሀል ግን ሊቢያውያን የመጀመሪያውን የስልጣን ሽግግር በሠላም አከናውነዋል። ባሳለፍነው ሐሙስ በምክር ቤቱ የተመረጡት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አል ሜጋሪፍ አርብ ዕለት በምክር ቤቱ ተገኝተው የኔ ተግባር ከፖለቲካዊው፣ ከአካባቢያዊው እና ከጎሳዊው ውዥንብር ራቅ ብሎ መንቀሳቀስ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ምናልባትም የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ቃል ወደፊት እንደተጠበቀ የሚቀጥል ከሆነ ውጤቱ በአምባጋነን አገዛዝ ለዘመናት ሲማቅቁ ለቆዩት ሊቢያውያን ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ጭቁን ሕዝቦች ጭምር ተስፋ መሆኑ አይቀርም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ