1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለገበሬዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያቀዱት ኢትዮጵያዊ

ረቡዕ፣ መጋቢት 9 2007

በዓለም አቀፉ የኃይል ተቋም (International Energy Agency) መሠረት 75 በመቶ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም። ይህ የኃይል ድህነት በገጠራማ አካባቢዎች ይበረታል። አቶ ዮሴፍ ብርሃነ የኤተርኑም ኢነርጂ ቬንቸርስ (Eternum Energy Ventures )የተባለ ኩባንያ መስራች እና ባለቤት ናቸው።

https://p.dw.com/p/1Esoi
Satelittenschüssel Solarnutzung
ምስል picture-alliance/dpa/Mujahid

ኩባንያቸው ከጸሃይ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ቁሳቁሶችን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ገበሬዎች የማቅረብ እቅድ ይዞ የተመሰረተ ነው። « በጸሃይ ብርሃን የሚሰራ ፋኖስ ከጀርመን በማስመጣት ለገበሬዎች በአነስተኛ ዋጋ እናከፋፍላለን። አምቦ አካባቢ አንድ ፕሮጀክት አለን። እስካሁን ወደ 78 የሚሆኑ ገበሬዎች ፋኖሱን አግኝተዋል።» የሚሉት አቶ ዮሴፍ የሚያስመጡት ፋኖስ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያስረዳሉ። «500 ብር አካባቢ ነው የምንሸጥላቸው። ሞባይል ቻርጅ ያደር ጉበታል። ማታ ለመብራት ይጠቀሙበታል። ነጭ ጋዝ ሲጠቀሙ የሚያወጡት ወጪ ይቀንሳል። እንደገና ደግሞ ከነጭ ጋዙ የሚወጣው ጭስ ለጤንነታቸው መጥፎ ስለሆነ ከእሱም ጤንነታቸው ይጠበቃል።» አቶ ዮሴፍ የገበሬው ልጆች ይህን ፋኖስ በመጠቀም ትምህርታቸው እንዲያጠኑ ያግዛቸዋል ብለው ያምናሉ።

በአለም አቀፉ የኃይል ተቋም (International Energy Agency) መሰረት 620 ሚሊዮን አፍሪቃውያን የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም።ከእነዚህ አፍሪቃውያን ውስጥ 80 በመቶው የገጠር ነዋሪዎች ናቸው። በተቋሙ መረጃ መሰረት 75 በመቶ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም። ይህ ቁጥር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2012 በኋላም ቢሆን መሻሻል አልታየበትም። በገጠር አካባቢ ለሚኖሩ አፍሪቃውያን ከእንጨት፤ከሰል እና የእንስሳት እዳሪን በማቃጠል የሚገኝ የሃይል ምንጭ ላይ ጥገኞች ናቸው። ይህ ደግሞ የቤት ውስጥ የአየር ብክለትን በማስከትል ለሚሊዮኖች ህመምና ሞት መዘዝ መሆኑን አለም አቀፉ የሃይል ተቋም ያትታል። ይህን ችግር የሃይል ድህነት (Energy Poverty) ሲሉ ይጠሩታል አቶ ዮሴፍ ብርሃነ። አቶ ዮሴፍ ለኢትዮጵያ ገበሬዎች በማቅረብ ላይ የሚገኙት በጸሃይ ሃይል የሚሞላ ፋኖስ ለአጠቃቀምም ቢሆን ቀላል መሆኑን ይናገራሉ።

« አምፖሏ ትንሽ ነች። እንደ ባትሪም ትጠቀምባታለህ። ለስድስት ሰዓታት በጸሃይ ሃይል ከተሞላ ማታ ከ12-5 ሰዓት መብራት ያገኛሉ።»

Solare Heimanlagen Afrika
ምስል FRES

ለአንድ ፋኖስ 500 ብር መክፈል ቀላል ነው? ይህን የገንዘብ መጠን መክፈል የሚችሉ የመኖራቸውን ያህል የሚከብዳቸውም መኖራቸውን አቶ ዮሴፍ ተናግረዋል። እናም በሁለት እና ሶስት ጊዜ ክፍያ ፋኖሱን የሚያገኙበትን መንገድም አመቻችተዋል። የግብርና ባለሙያዎች በፋኖሱ አጠቃቀም ላይ ለገበሬዎች እገዛ ያደርጋሉ። ይህን ከጸሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ፋኖስ ኢትዮጵያ ውስጥ የማምረትም እቅድ አላቸው። ነገር ግን ስራው አልጋ ባልጋ አልሆነም። የብድር አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ አለማግኘት ፈተና እንደሆነባቸው አቶ ዮሴፍ ይናገራሉ።

በአለም አቀፉ የኃይል ተቋም መሰረት ከአፍሪቃ ሃገራት መካከል ናይጄሪያ የከፋ የኃይል ድህነት የሚታይባት ተብላለች። 80 በመቶ ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይል አያገኙም። እየጨመረ ለመጣው የአፍሪቃውያን የሃይል ፍላጎት የአህጉሪቱ ወንዞች ተስፋ ናቸው የሚለው ተቋሙ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ዋንኛ ትኩረት ከተሞች በመሆናቸው ገጠራማ አካባቢዎች በሃይል እጥረት ውስጥ ለመኖር መገደዳቸውን ያትታል።

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ