1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቀን 500 ገደማ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ

ረቡዕ፣ ኅዳር 14 2009

በደቡብ ሱዳን ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት የሸሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸውን ተከትሎ በጋምቤላ አዲስ መጠለያ ጣቢያ ተከፍቷል። የአዲሱ ጣቢያ መከፈት በኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ስደተኞች የተከፈቱትን ጣቢያዎች ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ያደርገዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2T8XT
Äthiopien Flüchtlinge aus Südsudan
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

New camp open for South Sudanese refugess in Ethiopia - MP3-Stereo

ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ደቡብ ሱዳናውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ተከትሎ የተከፈተው አዲስ መጠለያ ጣቢያ በጋምቤላ ክልል ውስጥ ኝንጎዌል በተባለ አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡ መጠለያ ጣቢያው የተከፈተው በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን «UNHCR» እና በመንግስታዊው የስደተኞች እና ስደት ተመላሾች ጉዳዮች አስተዳደር አማካኝነት ነው፡፡

አዲሱ መጠለያ ጣቢያ አስቀድሞ ከተከፈተው እና 70 ሺህ ደቡብ ሱዳናውያን ከተጠለሉበት ቴርኬዲ ጣቢያ በቅርብ ርቀት ያለ ነው፡፡ ሰባተኛ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መጠለያ የሆነው የኝንጎዌል ጣቢያ 70 ሺህ ስደተኞች የመያዝ አቅም እንዳለው የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ክሱት ገብረእግዚያብሔር ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል ስለተመሰረቱት ጣቢያዎች እና ተጨማሪ ለምን መክፈት እንዳስፈለገ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡  

“አንደኛው ትንሽ ወጣ ያለ ነው፡፡ በጋምቤላ ክልል [ውስጥ] ሆኖ ለደቡብ ክልል የሚቀርብ ነው፡፡ በዚህ ላይ የጎሳ ልዩነቶች ስላሉ የተወሰኑ ስደተኞች ናቸው እዚያ ያሉት፡፡ ብዙም እዚያ መጨመር አልፈለግንም፡፡ ብዙዎቹ ወደ እኛ የሚመጡት የኑዌር ተወላጆች ናቸው፡፡ ኑዌር ዞን አካባቢ የመሰረትናቸው ጣቢያዎች ብዙዎቹ ሞልተዋል፡፡ ከክልሉ መንግስት እና ከኢትዮጵያ የፌደራል የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ጋር አብረን ሆነን አመቺ የሆነ ቦታ ፈለግን እና ቦታው ከኦክቶበር 20 ጀምሮ ተከፈተ፡፡ ስለዚህ ከዚያ ወዲህ ስደተኞችን ወደዚያ እያስገባን ነው ያለነው” ብለዋል፡፡ 

አዲሱ ጣቢያ በተከፈተ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ዘጠኝ ሺህ የሚደርሱ ስደተኞችን መቀበሉን አቶ ክሱት ይገልጻሉ፡፡ በዚሁ አካሄድ ከቀጠለ “ይህም የማይሞላበት ምክንያት አይኖርም” ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት ይጠቁማሉ፡፡

በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ሰላምን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ተስፋ አስቆራጭ በሆነበት በዚህ ወቅት ደቡብ ሱዳናውያን ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አጎራባች ሀገር እየጎረፉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ እየተሻገሩ እንደሆነ አቶ ክሱት ይናገራሉ፡፡  

UNHCR Flüchtlingslage in Gambella Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

“ቁጥሩ ማሻቀብ የጀመረው [እንደ ጎርጎርሳዊው አቆጣጠር] ከመስከረም መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ነው፡፡ በቀን እስከ ሁለት ሺህ የሚደርሱበት ወቅት ነበር፡፡ አሁን በቀን አማካዩ 500 አካባቢ ደርሷል” ይላሉ ቃል አቀባዩ፡፡

ከአዲስ መጤ ስደተኞች መካከል 64 በመቶው ያህል ህጻናት መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከህጻናት ስደተኞች መካካል ግማሽ ያህሉ ብቻቸውን ድንበር ያቋረጡ አሊያም በሽሽት ላይ ከቤተሰባቸው የተለያዩ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ 800 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊዎች እንዳሉ የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 40 በመቶው ደቡብ ሱዳናውያን ናቸው፡፡ በሁለተኛነት የሚከተሉት ሶማሊያውያን ስደተኞች ሲሆኑ ሃያ በመቶ የስደተኞችን ቁጥርን በመሸፈን ኤርትራውያን በሶስተኛነት ተቀምጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ ስደተኞች የተጠለሉባቸው 25 ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ