1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢራቅ የርዳታ ማሰባሰቢያ ጉባኤ በማድሪድ

ዓርብ፣ ጥቅምት 13 1996

በስፓኝ ማድሪድ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የኢራቅ መልሶ ግንባታ የለጋሾች ጉባኤ ቀጥሏል ። ዛሬ ማርፈጃው ላይ ጉባኤው ሲጀመር ንግግር ያደረጉት የኢራቅ ጊዚያዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አያድ አላዊ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮለን ፓውል ባሰሙት ንግግር ለጋሽ ሀገራት አንባገነን አስተዳደሯን ለገረሰሰችው ኢራቅ እገዛቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ። ለኢራቅ የሚያስፈልገው 36 ቢሊዮን ዶላር ነው ቢባልም የሚለገሰው የገንዘብ መጠን ከግማሽ ያነሰ ነው የሚል ግም

https://p.dw.com/p/E0gB

ትም አለ ።


ለኢራቅ መልሶ ግንባታ ሰላሳ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ያስታወቁት የዓለም ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ናቸው ። ይህ ገንዘብ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ወጪ እንደሚሆንም ተጠቁሟል ። የዩናይትድ ስቴትስ መራሹ የኢራቅ ጥምር አስተዳደር ደግሞ ተጨማሪ ሃያ ቢሊዮን ያስፈልጋል ይላል ። ተጨማሪው ገንዘብ ለፀጥታ አጠባበቅ ፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለነዳጅ ኢንዱስትሪ መስክ የሚውል ነው ። ኢራቅ አንባገነን አስተዳደሯ በመገርሰሱ እፎይታን እንዳገኘች የጠቀሱት በዩናይትድ ስቴትስ የተሰየመው የኢራቅ ጊዚያዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አያድ አላዊ ዛሬ ጠዋት ባደረጉት ንግግር ርዳታው ባልተከፋፈለ ልብ እንዲለገስ ጠይቀዋል ። ይኸው የልመና ጥያቄ ጉባኤው ትላንት ሲጀመር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፀሃፊ ኮፊ አናን እና በስፓኝ ጠቅላይ ሚንስትር ዮሲ ማርያ አዝናር ቀርቦ ነበር ። አናን የኢራቅን ልዋላዊነት የሚያረጋግጥ መንግስት ባይመሰረትም ኢራቅን ካለችበት ችግር ውስጥ የሚያወጣ ርዳታ እንዲደረግ ሲጠይቁ ነጻነቷን በራሷ ህዝብ እእስከምታስተዳድር ድረስ እንዳይጠበቅም ተማፅነዋል ። አዝናር ደግሞ ሀገራቸው የምታስተናግደው ጉባኤ ለኢራቅ ተገቢውን ርዳታ እንደሚያሰባስብ ገልፀው ርዳታን መንፈግ ማለት ግድያን እና አሸባሪነትን የሚፈልጉ ወገኖች ማስደሰት ነው ብለዋል ። ይሁንና ጉባኤው ዛሬ ማምሻውን ሲጠናቀቅ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ገንዘብ ከግማሽ ያነሰ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ ። ምክንያቱም የሚሰነዘረው የርዳታ ክንድ ቁጥብ ሆኖ ታይቷልና ። ዛሬ ጠዋት በጉባኤው ንግግር ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮለን ፓውል የተፈለገው ገንዘብ ባይገኝም ፍላጎትን የማሳየቱ ተግባር በራሱ ሊደነቅ ይገባል ባይ ናቸው ። በርግጥም የሚገኘው መጠን አነስተኛ ቢሆንም ያለ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይሁንታ ኢራቅን የተቆጣጠረችው የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት በኢራቅ ጉዳይ የሌሎች ሀገሮች ተሳትፎ መኖሩ ሀገር ውስጥ ያለውን የፓለቲካ ውጥረት ሲያረግብላቸው ለደረሰው የአሜሪካ የኤኮኖሚ ቀውስ እገዛ ማድረጉ አይቀርም ። እስካሁን የታየው ድጋፍ አበረታች ነው ያሉት ፓውል ሀገራቱ እና ለጋሽ ድርጅቶች የተፈለገው ግብ እንዲመታ የርዳታ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ከመማፀን አልተቆጠቡም ። እስካሁን በተደረገው የርዳታ ልገሳ የአውሮጳ ህብረት ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር እንደሰጠ የወቅቱ የህብረቱ ፕሬዝዳንት ሀገር የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንኮ ፍራቲኒ ከሰጡት መግለጫ ታውቋል ። የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከቶኪዮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ተጨማሪ ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለኢራቅ እንደተመደበ ሲገልፅ ይህ የጃፓን ልገሳ ካለፈው ሳምንት ርዳታ ጋር ተደምሮ ወደ አምስት ቢሎዮን ደርሷል ። ጃፓን ተጨማሪ ርዳታ የመመደቧ ምክንያት ከኢራቅ የመልሶ ግንባታ በተጨማሪ ከብሄራዊ ጥቅም ጋር ይያዛል ። ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የወጣው መግለጫ እንዳለው ጃፓን የኢራቅ የደህንነት እና የመልሶ ግንባታን የምትፈልገው ዘጠና በመቶ የነዳጅ ምንጯ ኢራቅን ጨምሮ ከአካባቢው ሀገሮች በመሆኑ ነው ። እንደ ጃፓን በቀጥታ አይነገር እንጂ ሀገራቱ እና ለጋሽ ድርጅቶች ርዳታውን የሚሰጡት ከበስተጀርባው የሚያስገኝላቸውን ጥቅም በማየት ነው ። እንደ ጀርመን ያሉት ሀገራት ደግሞ የምንሰጠው ከአቅማችን ጋር መመጣጠን አለበት ይላሉ ። የኢራቅን ጦርነት አጥብቀው ይቃወሙ ከነበሩት ሀገሮች ውስጥ አንዷ የሆነችው የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዮሽካ ፊሸር ጀርመን የሰጠችው የሁለት ሚሊዮን ገደማ ያህል ርዳታ ሊታይ የሚገባው ሀገሪቱ ካላት የገንዘብ አቅም አኳያ ነው ሲሉ ሀገራቸው ጥቂት ሰጠች ለሚለው ቅሬታ ምላሽ ሰጥተዋል ። ዛሬ ከሰዓት በፊት ድረስ የአንድ ወቅት ጠላት የነበረችው የኢራቅ ጎረቤት ኢራን ሶሶት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የኤሌክትሪክና የጋዝ አቅርቦት ለማድረግ ቃል ስትገባ ስዑድ አረቢያ እና ኩዬት ደግሞ እያንዳንዳቸው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል ። የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ተኩል እንደሚሰጡ ሲጠበቅ ለጋሾቹ የሚሰጡት መጠን ዝርዝር ተጠቃሎ የሚገለፀው ስልሳ አንድ ሃገራት እና አስራ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተገኙበት ጉባኤ ማምሻውን ሲጠቃለል ነው ።