1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለንደን፥ ከሽብር ጥቃቱ ጋር በተያያዘ 12 ሰዎች ታሰሩ

እሑድ፣ ግንቦት 27 2009

ከለንደኑ የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ፖሊስ 12 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ። ትናንት ምሽት ለንደን ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የገበያ ሥፍራ በአነስተኛ ተሽከርካሪ በመግባት በስለት በደረሰ የሽብር ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ40 በላይ የሚሆኑት ቆስለዋል።

https://p.dw.com/p/2e7BW
Britannien London - Terroranschlag
ምስል Getty Images/D. Kitwood

MMT Q/A London Terror - MP3-Stereo

ለንደን ድልድይ ላይ በአነስተኛ ተሽከርካሪ በመጓዝ በአቅራቢያው በሚገኘው ቦሮው ገበያ ውስጥ ትናንት ምሽት በስለት ጥቃት ያደረሱት ሦስት አሸባሪዎች በፖሊስ ጥይት ተተኩሶባቸው መገደላቸው ተዘግቧል።  የትናንቱ ጥቃት የደረሰው በብሪታንያ ብሔራዊ ምርጫ ሊኪያሄድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ሲቀሩት ነው። ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎም በሰሜናዊ የማንቸስተር ከተማ የሙዚቃ ድግስ ላይ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ባደረሰው ጥቃት 22 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። የለንድን አምቡላንስ አገልግሎት ትናንት ምሽት 48 ሰዎችን መዲናዪቱ ውስጥ ወደሚገኙ  አምስት ሐኪም ቤቶች ማጓጓዙን አስታውቋል። ከቁስለኞቹ መካከል ሽብርተኞቹን በቆመጥ ብቻ ለመገዳደር የሞከረ የከተማዋ ፖሊስም ይገኝበታል። ፖሊሱ ፊቱ፣ እግሩ እና ጭንቅላቱ ላይ በጽኑዕ መቁሰሉ ተገልጧል። ቀደም ሲል የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንሥትሪት ቴሬሳ ሜይ  ሽብርተኝነትን አጥብቀው ለመታገል ጥሪ አቅርበው ነበር። ሽብርተኝነትን ለመዋጋት አዲስ ሕግ እንደሚያስፈልግ፤ አነስተኛ ለሆኑ ወንጀሎችም እንደሁኔታው ጠበቅ ያለ ቅጣት ሊኖር እንደሚችል በቴሌቪዥን ባሰሙት ንግግር አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚንሥትሯ ብሪታንያውያን በጋራ ጽንፈኝነትን እንዲታገሉም ጥሪ አስተላልፈዋል። 

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ