1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሴቶች ትኩረት የሰጠዉ «ጉድ ሳማሪታን»

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2005

የሴቶችን የጤና ይዞታ የማሻሻልና የጤና አገልግሎትን ማዳረስ አዳጊ ሀገሮች የሚያዳግታቸዉ ዓይነተኛ የመሠረተ ልማት አካል ነዉ። እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች የህክምና አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚያደርገዉ ጥረት ቢኖርም፤

https://p.dw.com/p/180OI
ምስል Helge Bendl

በዋና ከተማ አዲስ አበባም ትኩረት የሚያስፈልጋቸዉ አካባቢዎች መኖራቸዉም ይታያል።በዓለማችን ከሴቶችና ወንዶች የእድሜ ጣሪያ ሲታይ ሴቶች ከስድስት እስከ ሰባት ተጨማሪ ዓመታት ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢገለፅም የጤና ይዞታቸዉ ሲታይ ደግሞ ከወንዶች ይልቅ ለጤና እክሎች የተዳረጉ መሆናቸዉን ነዉ መረጃዎች የሚያመለክቱት። ይህ ደግሞ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ሲታከልበት የሴቶች ጤና ድሃ በሚባሉት ሀገሮች ምን ያህል አሳሳቢ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።

ጉድ ሳማሪታን ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ ለሴቶች የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ የሚጥር አገር በቀል ድርጅት ነዉ። ድርጅቱ ከመነሻዉ የተመሠረተዉ በእንጦጦ አካባቢ እንጨት በመሸከም ኑሯቸዉን የሚገፉትን ጎስቋላ እናቶችና ቤተሰቦቻቸዉ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ነበር። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር እንደገለፁት በህክምና ባለሙያዎች ተነሳሽነት የተጀመረዉ ይህ ግብረ ሰናይ ድርጅት በህገወጥ ከአንድ ቦታ ወደሌላ በሚያሸጋግሩ ሰዎች ለስደት ተዳርገዉ ችግር የገጠማቸዉን ሴቶችም ለመርዳት እየተነቀሳቀሰ ነዉ። ሥራ አስኪያጇ ወ/ሮ ጥሩ ብርሃን ጌትነት፤ አሁን ወደእንጦጦ ማርያም አቅራቢያ ያቀናዉ የህክምና አገልግሎት መስጫ ከመነሻዉ ከዘጠኝ መቶ በላይ እንጨት ለእመዉ በመሸጥ ኑሯቸዉን የሚገፉ ሴቶችን ከነቤተሰባቸዉ መዝግቦ በሽሮ ሜዳ አካባቢ የነፃ አገልግሎቱን ይሰጥ እንደነበር ነዉ የጉድ ሳማሪታን ስራ አስኪያጅ የሚያስረዱት።

Ethiopian girls carrying water
ምስል CC/waterdotorg

የህክምና መስጫ ጣቢያዉ በተጠቀሰዉ አካባቢ በቀን ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ህሙማንን ያስተናግድ እንደነበር ነዉ የተረዳነዉ። ይሰጥ የነበረዉ አግልግሎት በአቅምና በተለያየ ምክንያት የሚስተጓጎል ከሆነ በርካታ ወገኖች ህክምና አገልግሎት አዲስ አበባ ዉስጥም እየኖሩ በአቅራቢያቸዉ ለማግኘት ሊኖራቸዉ የሚችለዉ አማራጭ አሳሳቢ ይመስላል።

ጉድ ሳማሪታን በሀገሪቱ ዋና ከተማ እየኖሩ በአቅማቸዉ ማነስ ምክንያት ህክምና ማግኘት ለማይችሉ በርካታ ምንዱባን አገልግሎት እያዳረሰ ከአስር ዓመታት በላይ ዘልቆ አሁን የሚገኝበት መስቀለኛ መንገድ ይመስላል። ምንም እንኳን ቀደም ሲል ዋና ስራ አስኪያጇ ወ/ሮ ጥሩ ብርሃን እየተሞከሩ የሚገኙ አቅም የማጠናከር ጥረቶች እንዳሉ ቢሆንም። እንዲህ በቋፍ የደረሰ የሚመስለዉ የግብረሰናይ ድርጅት ከዚህ ሌላ ደግሞ በተለያዩ የአረብ ሀገራት ለሥራ እየሄዱ ከገንዘብም ከጤናቸዉም ሳይሆኑ ህይወታቸዉ ተመሳቅሎ የሚመለሱ እህቶችን እየተቀበለ ህክምና የሚያገኙበትን ብሎም ከቤተሰብ የሚቀላቀሉበትን መንገድ ለማመቻቸትም እየሰራ ይገኛል።

ወርቅ አፍሰዉ ዶላር ተሸክመዉ ለመመለስ አልመዉ ቤተሰብ ያለ የሌለ ንብረቱን ሸጦ፤ ተበድሮና ተለቅቶ ልኳቸዉ፤ ተስፋቸዉ ጉም መጨበጥ ሆኖ ዙሪያዉ ገደል ሆኖባቸዉ ጤናቸዉ የሚታወክ ቁጥራቸዉ ቀላል እንዳልሆነ ነዉ ወ/ሮ ጥሩ ብርሃን የሚናገሩት።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ